Monday, 14 April 2014 10:20

“በሰይፉ ፋንታሁን ሾው” የቀረበው ግሩም ኤርሚያስ የተወነበት ቀረፃ ወደ ክስ ሊያመራ ይችላል

Written by  በአሲዮ ዳን
Rate this item
(7 votes)

ከአደገኛ አደንዛዥ ዕፆች ጋር ተያይዘው የሚደረጉ ወንጀሎችን በተመለከተ፣ በአሁን ሰዓት ከፍተኛ ቀውስ በማስከተላቸው ከአገርም አልፎ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕግ አወጣጥም ሆነ በክትትል ረገድ ትኩረት ሲስቡ ቢታይም
እነዚህ ወንጀሎች አሳሳቢ በሆኑበት ደረጃ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ በብቃት አልታቀፉም …” ይላል፡፡

   ከአንድ ሳምንት በፊት ከወዳጆቼ ጋር ምሳ በልተን ቡና እየጠጣን ሳለ የጀመርነው ጨዋታ ለዚህ ፅሑፍ መነሻ ሆነኝ፡፡ የጨዋታችን ርዕስ የነበረው እሁድ መጋቢት 14 ቀን 2006 ዓ.ም ምሽት  በኢ.ቢ.ኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ  የተላለፈው የ“ሰይፉ ፋንታሁን ሾው” ነው፡፡ በትዕይንቱ ላይ አርቲስት አለማየሁ ታደሰና ግሩም ኤርሚያስ እንዲሁም ኮሜዲያን ደረጄ ኃይሌ ተጋባዥ የነበሩ ሲሆን ወዳጃችን እነሱ የተናገሩትን ነገር እያስታወሰ ጥቂት አዝናናን፡፡ እጅግ የማደንቀው አርቲስት አለማየሁ ታደሰ ተጋባዥ የነበረበትን ይህንን አዝናኝ ትዕይንት አለመከታተሌ ቢቆጨኝም በድጋሚ የሚተላለፍብትን ቀን ጠብቄ ትርዒቱን ለመከታተል እንድወስን ያደረገኝ ግን ወዳጄ ስለአርቲስት ግሩም ኤርሚያስ ያወጋን ነገር ነበር፡፡ እናም መጋቢት 18 ቀን 2006 ዓ.ም ምሽት ትዕይንቱ በድጋሚ ሲተላለፍ ተመለከትኩት፡፡ አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ ወደፊልም ኢንዱስትሪው ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮ እያሳየ የመጣውን የትወና ብቃት ለትህትና ፍጆታ ሳይሆን እጅግ ከልብ የማደንቅ መሆኔን እየገለፅኩኝ ትዝብቴን እነሆ ላካፍላችሁ፡፡
አርቲስቱ የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ የሆነ ሰውን ገፀ-ባህሪ ወክሎ ስለተወነበት “በጭስ ተደብቄ” የሚል ርዕስ ያለው አዲስ የቪዲዮ ፊልም ከሰይፉ ፋንታሁን ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው መልስ እሱ የሚከተለው የትወና ዘዴ “ሜተድ አክቲንግ” (method acting) የሚባለውን እንደሆነ ገልጿል፡፡ አክሎም በዚህ የትወና ዘዴ መሰረት ተዋናዩ የተሰጠውን ገፀ-ባሕሪ መስሎ ሳይሆን ሆኖ መገኘት ያለበት በመሆኑ፣ እሱም ገፀ-ባሕሪውን ለመሆን ብሎ ካናቢስ የተሰኘውን አደንዛዥ ዕፅ በፊልሙ ቀረፃ ወቅት ደጋግሞ እንደተጠቀመና በዕፁ ደንዝዞ አቅሉን በመሳቱ ትወናውን ለተወሰነ ደቂቃ ማከናወን እንዳልቻለ አጠር ያለ ማብራሪያ ሰጠ፡፡ አርቲስቱ ካናቢስ ዕፅ አጭሶ መተወኑን በመግለፅ ብቻ አልተቆጠበም። በፊልሙ ቀረፃ ወቅት አርቲስቱ በዕፁ ደንዝዞ ከገባበት ሰመመን ሲነቃ፣ ከፊልሙ ባለሙያዎች ጋር ያደረገውን ንግግር ጭምር የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል አሳየን፡፡ አርቲስቱ ይህንን ማድረጉን መግለፅ በጀመረባት ቅፅበት አርቲስት አለማየሁ ታደሰ ራሱን በመነቅነቅ ካሳየው አድንቆት ጀምሮ ተቀንጭቦ የታየው ፊልም ሲጠናቀቅ በስቱዲዮ ተመልካቾች እስከተቸረው ደማቅ የአድንቆት ጭብጨባ ድረስ ሙገሳን ሲቸረው አየሁ፡፡ የትወና ብቃቱን፣ ጥረቱን እና ቁርጠኝነቱን ደግሜ ባደንቀውም ይሄን ድርጊቱን ግን ለማሞካሸት እቸገራለሁ፡፡ ምክንያቱም የአርቲስቱ ድርጊት ለተሳካ ትወና ከተደረገ ጥረት ባሻገር፣ በአገራችን የወንጀል ሕግ ቀላል የማይባል የእስራት ቅጣትን ሊያስከትል የሚችል የወንጀል ድርጊት ነው፡፡   
በተለየ ሁኔታ ካልገለፅኩት በቀር ከዚህ በኋላ የምጠቅሰው ሕግም ሆነ አናቅፆች አሁን በስራ ላይ ያለውን የ1996 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግን እና በውስጡ የተካተቱትን አናቅፆች እንደሆነ እየገለፅኩ፣ የአርቲስቱ ድርጊት ወንጀል ነው ያልኩበትን ምክንያት ልተንትን፡፡ የ1949ኙ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ከተሻሻለበት ምክንያቶች አንዱን ሕጉ በመግቢያው ላይ ሲገልፅ “… ከአደገኛ አደንዛዥ ዕፆች ጋር ተያይዘው የሚደረጉ ወንጀሎችን በተመለከተ፣ በአሁን ሰዓት ከፍተኛ ቀውስ በማስከተላቸው ከአገርም አልፎ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕግ አወጣጥም ሆነ በክትትል ረገድ ትኩረት ሲስቡ ቢታይም እነዚህ ወንጀሎች አሳሳቢ በሆኑበት ደረጃ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ በብቃት አልታቀፉም …” ይላል፡፡ በመሆኑም አሁን በስራ ላይ ያለው የወንጀል ሕግ፣ አደንዛዥ ዕፆች እያስከተሉት ያለውን ከፍተኛ ቀውስ ታሳቢ አድርጎ የወጣ ነው፡፡ በአንቀፅ 1 ሥር እንደተገለፀው የወንጀል ሕጉ ዓላማ ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የአገሪቱን መንግስት፣ የህዝቦቿን፣ የነዋሪዎቿን ሰላም፣ ደህንነት፣ ስርዓት፣ መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ በመሆኑ፣ የወንጀል ሕጉ በአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች ላይ ጠበቅ ያለ ድንጋጌን ይዟል፡፡
አንድን በሕግ የተከለከለ ድርጊት ማድረግ ወይም በህግ የታዘዘውን አለማድረግ የሚያስቀጣው ሕገወጥነቱና አስቀጪነቱ በሕግ ሲደነገግ እንደሆነ አንቀፅ 23(1) ይደነግጋል፡፡ ለምሳሌ ጉቦ አልቀበልም ማለት ወንጀል ነው የሚል ድንጋጌ በወንጀል ሕጉም ይሁን በሌሎች ሕግጋት ወንጀል ነው ተብሎ የተደነገገ ባለመሆኑ፣ አንድ ሰው ጉቦ አልቀበልም ቢል አይቀጣም፡፡ አንቀፅ 23 (2) ደግሞ አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባለው ደግሞ ወንጀሉን የሚያቋቁሙት ሕጋዊ፣ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተው ሲገኙ ብቻ እንደሆነ ደንግጓል፡፡ በዚህ አንቀፅ አነጋገር ሕጋዊ ፍሬ ነገር የሚባሉት ለጉዳዩ አግባብነት ባለው አንቀፅ የተጠቀሱትን ዝርዝር ፍሬ ነገሮች መሟላት፣ ግዙፋዊ ፍሬ ነገር የሚባለው በሕጉ እንዳይፈፀም የተከለከለን ድርጊት መፈፀም ወይም እንዲደረግ የታዘዘን ድርጊት አለመፈፀም እና ሞራላዊ ፍሬ ነገር የሚባለው ድርጊቱን የፈፀመው ሰው ድርጊቱን ሲፈጽም የነበረው የሃሳብ ክፍል መሟላቱ ማለትም በአንቀፅ 57 እንደተብራራው ድርጊቱን የፈፀመው አውቆ ወይም እንደሁኔታው በቸልተኝነት መሆኑ ነው፡፡ አንቀፅ 57(2) አንድ ሰው የወንጀል ድርጊት ቢፈፅምም ጥፋተኛ የማይሆነበትን ምክንያት ሲገልፅ “ማንም ሰው የፈፀመው ድርጊት በሕግ የሚያስቀጣ ቢሆንም ምንም ጥፋት ሳያደርግ ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ኃይል ምክንያት ወይም ድንገተኛ አጋጣሚ ነገር የተፈፀመ ወይም የደረሰ ሆኖ ሲገኝ በወንጀል ሕግ ሊፈረድበት አይገባውም” ይላል፡፡
ከዚህ በላይ የተገለፁትን የሕግ ድንጋጌዎች እንደመንደርደሪያ ይዤ ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስ፡፡ ሕጉ በርዕስ ስምንት ሥር በጤና ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን የዘረዘረ ሲሆን በዚሁ ርዕስ ምዕራፍ አንድ ክፍል ሁለት ስር፣ በሰውና በእንስሳ ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ነገሮችን በማምረትና በማሰራጨት የሚደረጉ ወንጀሎች ተዘርዝረዋል፡፡ በአንቀፅ 525 ሥር የተደነገገው መርዛማ ወይም የናርኮቲክና ሳይኮትሮፒክ መድሐኒቶችን ወይም ዕፆችን ማምረት፣ መስራት፣ ማዘዋወር ወይም መጠቀም ከእነዚህ የወንጀል ድርጊቶች አንዱ ሲሆን አሁን ለያዝነው ጉዳይ ተገቢነት አለው፡፡ አንቀፅ 525 ስድስት ንዑሳን አንቀፆችን የያዘ ሲሆን በንዑስ አንቀፅ (4)(ለ) ሥር የሚከተለው ተደንግጓል፡-
“ማንም ሰው…ከእነዚህ ነገሮች በአንዱ ያለሐኪም ፈቃድ ወይም በማናቸውም ሌላ ሕገወጥ መንገድ የተጠቀመ ወይም ሌላ ሰው እንዲጠቀምባቸው ያደረገ፤ እንደሆነ ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና ከሃምሳ ሺህ በማይበልጥ መቀጫ ይቀጣል።” (ያሰመርኩባቸውን ቃላት ልብ ይበሉ)
ሕጉ “ከእነዚህ ነገሮች” የሚለው በንዑስ አንቀፅ 1 የተገለፁትን መርዛማ ወይም የናርኮቲክና ሳይኮትሮፒክ መድሐኒቶችን ወይም ዕፆችን መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
የካናቢስ ዕፅ ይዘው፣ ሲሸጡ፣ ሲጠቀሙ ወዘተ ተይዘዋል ተብለው በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ የወንጀል ምርመራ ሲጣራ ከሚፈፀሙ ነገሮች አንዱ የካናቢስ ዕፅ የተባለውን ነገር በላብራቶሪ ማስመርመር ነው። በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የፎረንሲክ ምርመራ ዳይሬክቶሬት ለሚመለከታቸው አካላት በሚሰጠው የላብራቶሪ ምርመራ ውጤት የሚከተለውን ውጤት ይገልፃል፡፡ “የካናቢስ ዕፅ ሰዎችን ሱስ በማስያዝ ለተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች መንስኤ እንዲሆኑ ስለሚገፋፋ እንዳይመረት፣ እንዳይዘዋወር እና በጥቅም ላይ እንዳይውል የታገደ ዕፅ ነው፡፡” ይህ የውጤት መግለጫ እና የአንቀፅ 525(1) እና (4) አገላለፅ የካናቢስ ዕፅ ማንም ሰው እንዲጠቀምበት የማይፈቀድ እና ጥቅም ላይ ከዋለም ተጠቃሚውን የሚያስቀጣው እንደሆነ ለመደምድም ያስችለናል፡፡
ካናቢሱን ማጨሱ “የተጠቀመ” የሚለውን እና ካናቢስን መጠቀም በሕግ የተከለከለ መሆኑና ዕፁን የተጠቀመው ለሕክምና ዓላማ አለመሆኑ “ያለሐኪም ፈቃድ” ወይም “በማናቸውም ሌላ ሕገወጥ መንገድ” የሚለውን የሕጉን ፍሬ ነገሮች የተሟሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ካናቢሱ አደንዛዥ መሆኑን እያወቀ ይህንኑ ውጤት ለማግኘት ፈልጎ መጠቀሙ የህጉን ሞራላዊ ፍሬ ነገር የተሟላ ያደርገዋል፡፡ ካናቢስ ማጨሱ ደግሞ ግዙፋዊ ፍሬ ነገር ያሟላል። ዕፁን የተጠቀመው ምንም ጥፋት ሳያደርግ ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ኃይል ምክንያት ወይም ድንገተኛ አጋጣሚ ባለመሆኑ የአንቀፅ 23(1) እና (2) እና 525(4)(ለ) አነጋገር የአርቲስቱን ድርጊት በሕግ የሚያስቀጣ የወንጀል ድርጊት ያደርገዋል፡፡
እዚህ ጋር አንባቢያን ሊያነሱት ከሚችሉት ዋነኛ ጥያቄ አንዱ አርቲስቱ ካናቢስ ያጨሰው ለሥነ-ጥበብ ሥራ እንጂ ሌሎች የዕፁ ተጠቃሚዎች እንደሚያደርጉት በዕፁ ለመደሰት ስላልሆነ እንዴት ወንጀል ይሆናል? የሚል እንደሚሆን እገምታለው። ሕጉ ለሥነ-ጥበብ ዓላማ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀምን ይፈቅዳል ወይ? ወደ መልሱ ከመሄዴ በፊት አንድ የሕግ አቀራረፅ ሥርዓትን ላንሳ፡፡ ሕጎች ጠቅላላ ድንጋጌ እና ልዩ ድንጋጌ በሚል ሥርዓት ሊቀረፁ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ከአንቀፅ 546 እስከ 549 ባሉት ድንጋጌዎች መሰረት ፅንስ ማቋረጥ ወንጀል መሆኑ ጠቅላላ ድንጋጌ ነው፡፡ ነገር ግን በአንቀፅ 55 1(1) (ሀ) መሰረት በመደፈሯ ምክንያት ወይም ከዘመዷ ጋር በተደረገ የግብረ ስጋ ግንኙነት የፀነሰች ሴት ፅንስ ብታቋርጥ በወንጀል እንደማያስቀጣት መደንገጉ ልዩ ድንጋጌ ነው፡፡ ስለዚህ ልዩ ድንጋጌው የተሟላ ከሆነ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ከዚህ የሕግ አቀራረፅ ሥርዓት አንፃር የያዝነውን ጉዳይ ሥንመለከተው፣ ከሕክምና ዓላማ ውጪ መርዛማ ወይም የናርኮቲክና ሳይኮትሮፒክ መድሐኒቶችን ወይም ዕፆችን ለመጠቀም የሚቻልበት አንዳችም ልዩ ሁኔታ በሕጉ ባለመቀመጡ ካናቢስን ለፊልም ቀረፃ በሚል ሰበብ ማጨስ ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ወንጀል ከመሆን የሚያግደው ነገር የለም፡፡
ድርጊቱ በወንጀልነት ከተፈረጀ በስተመጨረሻ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ ይህ የወንጀል ድርጊት በማን እና እንዴት ምርመራ ይካሄድበታል? የሚለው ነው፡፡ ማንም ሰው ወንጀል ሲሰራ ያየ ወይም ያላየም ቢሆን የወንጀል ክስ እንዲቀርብ ወንጀሉን ለማስታወቅ መብት እንዳለውና ጠቋሚው ሳይታወቅ (በስልክ፣ በፖስታ ወዘተ) ለፖሊስ ጥቆማ ከደረሰ ደግሞ ፖሊስ ወንጀል ስለመሰራቱ በአካባቢ ሁኔታ የተደገፈና የሚታመን ሆኖ ከተገኘ፣ በፖሊስ ምርመራ እንደሚደረግ በ1954 ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀፅ 11(1) እና 12 ሥር ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም አርቲስቱ የወንጀል ድርጊት መፈፀሙን በአደባባይ በመግለፁ፣ ወንጀል ስለመሰራቱ እንዲታመን የሚያስችል በመሆኑ፣ ፖሊስ በራሱ ተነሳሽነት አልያም የወንጀል ድርጊቱ ስለመፈፀሙ አውቃለው የሚል ሰው ጥቆማ ካቀረበ፣ ጥቆማውን መሰረት አድርጎ የምርመራ ሥራውን ለመጀመር ሥልጣን አለው፡፡ በዚህም መሰረት የተከሳሹ እና የፊልም ሥራውን የሰራው ድርጅት የመኖሪያ አድራሻ አዲስ አበባ ከመሆኑ አንፃር የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተከሳሹን በሕግ አግባብ ይዞ ምርመራ መጀመር ይችላል፡፡ የምርመራ መዝገብ የሚጣራው ወንጀሉ በተፈፀመበት ሥፍራ ባለ ፖሊስ በመሆኑ የፊልም ቀረፃው የተካሄደበትን ቦታ በምርመራ ለይቶ፣ የፊልሙ ቀረፃ የተካሄደበት ቦታ ለሚገኘው የፖሊስ ተቋም ጅምር የምርመራ መዝገቡን በመላክ ጉዳዩን በጥልቀት አጣርቶ፣ የቴሌቪዥኑን ሥርጭት ጨምሮ ወንጀሉ ስለመፈፀሙ የሚያስረዱ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ፣ ጉዳዩን ለሚመለከተው ለፌደራል ዓቃቤ ሕግ በማቅረብ በምርመራ መዝገቡ ላይ ለማስወሰን ስልጣን አለው፡፡
አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ በትዕይንቱ ላይ እንደገለፀልን “በጭስ ተደብቄ” በሚለው ፊልሙ አደንዛዥ ዕፅ በተጠቃሚዎቹ ላይ የሚያደርሰውን ሁለገብ ቀውስ፣ የሱሰኞቹን ሕይወት ቁልጭ አድርጎ በመተወን ሊያሳውቀንና ሊያስተምረን የተነሳ መሆኑ እጅጉን ሊያስመሰግነው የሚገባ ቢሆንም የፈፀመውን ድርጊት ወንጀልነት ባለማወቅ፣ ባለማስተዋል ወይም በመዘንጋት ጉዳዩን በድፍረት ለአደባባይ ማቅረቡ ግን አንድ ትምህርት የሚሰጠን ይመስለኛል፡፡ ይህም በሕጉ አንቀፅ 81(1) የተደነገገው “ህግን አለማወቅ ወይም በሕግ ላይ መሳሳት መከላከያ ሊሆን አይችልም” የሚለው ነው፡፡ የዚህ ፅሑፍ ዓላማም ይህንኑ ማስገንዘብ ነው፡፡ ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንምና በቀናነት የምንፈፅማቸው ድርጊቶች ሕግን የተከተሉ መሆናቸውን ለማወቅ ይረዳን ዘንድ የህግ ዕውቀታችንን ለመገንባት ልቦናችንን እንክፈት፡፡ ብሩሕ ቀናትን እመኝላችኋለሁ፡፡ ሰላም!!
ፀሐፊውን በሚከተለው ኢሜይል አድራሻቸው ማግኘት ይችላሉ፡፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Read 5074 times