Saturday, 19 April 2014 11:50

የዝንጀሮ ልጅ እናቱን “ቅቤ ስጪኝ” ቢላት፤ ቅቤ ቢኖር ያባትህ ታፋ ይህን ይመስል ነበር ወይ? አለችው” የጉራጊኛ ተረት

Written by 
Rate this item
(15 votes)

አንዳንድ በጣም ቀላል ተረት ሲቆይ እጅግ ትልቅ ታሪክ ይመስላል።
ከዕለታት አንድ ቀን የትልቅ አገርና የትንሽ አገር ሁለት ሰዎች ይገናኛሉ። ከዚያም አንድ የዓመት በዓል ዕንቁላል ሰብሮ አስኳሉን ለማውጣት በየት በኩል ቢሰበር ይሻላል የሚል ጥያቄ ያነሳሉ።
ከትንሽ አገር የመጡት አዛውንት፤ “ዕንቁላሉን ከጎን ሞላልኛ ጫፉ ላይ ብንመታው ነው አስኳሉ ሙሉውን ከነውሃው የሚወጣው” አሉ። ከትልቅ አገር የመጡት አዛውንት ደሞ፤ “የለም ወገቡ ላይ ብንመታው ነው ሙሉውን አስኳል ከነውሃው የምናገኘው” አሉ።
ቀኑን ሙሉ “አይሆንም ይሆናል”፣ “ልክ ነህ፣ ልክ አይደለህም፣” ሲባባሉ ዋሉ።
“አይ የትልቅ አገር ሰው በጣም ያሳዝናል! ዕንቁላል እንኳን መስበር አይችልም” አሉ የትንሽ አገር ሰው።
“የትንሽ አገር ሰው ፈፅሞ አይረባም። ዕንቁላል እንዴት እንደሚሰበር እንኳን የማያውቅ መሀይም ነው” አሉ የትልቅ አገር ሰው።
ተካረሩ፡፤ ተማረሩ!
“ይሄን ካልክ ሁለተኛ ዐይንህን አላይም። ለልጆቼም የትልቅ አገር ሰዎች ምን ዓይነት አላዋቂዎች እንደሆናችሁ እነግራቸዋለሁ!” አሉ አንደኛው።
“አንተም መቃብሬ ጋ እንዳትደርስ! እኔም መቃብርህ ጋ አልደርስም!” አሉ ሌላኛው።
እየተሰዳደቡ እኚህም ወደ ትልቅ አገር፣ እኒያም ወደ ትንሽ አገር ሄዱ። ብዙ ጊዜ አለፋቸው። ጉዳዩ የታሪክ ያህል አረጀ። ዋለ አደረና፤ በማናቸውም አጋጣሚ የትልቅ አገር ልጅ ወደ ትንሽ አገር ከሄደ ተደብድቦ ይመለሳል። በሌላ አጋጣሚ የትንሽ አገር ልጅ ወደ ትልቅ አገር ከሄደ ዱላ ቀምሶ ይመለሳል።
ነገር እየገፋ ሲሄድ የትልቅ አገርና የትንሽ አገር ሰዎች ጠላቶች ነን ተባባሉ። ጠበኝነታቸው በልጆች መደብደብ የሚያባራ አልሆነም። ወደ ጦርነት ገቡ። ሰው ተላለቀ። ብዙ ሬሣ ወደያገራቸው አጋዙ። ጦርነቱና ዕልቂቱ የማይቆም ሲመስል የጎረቤት አገሮች ጣልቃ ገብተው አገላገሏቸው። ሽምግልናም ተቀመጡ። በታሪክ በጣም ወደ ኋላ ሄደው ነገሩ ሲጣራ፣ ለካ “ዕንቁላል በየት በኩል ነው መሰበር ያለበት?” በሚል ነው ቅድመ - አያቶቻቸው ሲከራከሩ የተጣሉት። ለጊዜው ታረቁ።
የዛሬዎቹ የልጅ-ልጆች ግን፤ “ከአባቶቻችንና ከአያቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ጠብና ጠላትነት አለን!” ይላሉ። ዛሬም።
*      *       *
ጉዳይን በጥሞና መርምረን ሀቁ ጋ መድረስ እያቃተን ጭራና ቀንድ ቀጥለን፣ አካብደን፣ አከባብደን ስንከራከርበት አሣር የሚያህል ፖለቲካ፣ አሣር የሚያህል የፓርቲዎች ግጭት፣ አሣር የሚያህል የመንግሥታት ውዝግብና ጦርነት ጋ እንደርሳለን። ከዚያም ለልጅ ልጅ የሚደርስ ነቀርሳ እናተርፋለን። ስሙንም ታሪክ እንለዋለን!
ዘውግ ለዘውግ፣ ጎሣ ለጎሣ፣ ነገድ ለነገድ፣ ሃይማኖት ለሃይማኖት፣ መንግስት ለመንግስት የጠብ ፈትል እናወርዳለን። ስለተቃጠለ ቤት መነጋገር አቅቶን ስለ አገር መቃጠል እናወጋለን። ዘመን ወደ ዘመን ሲሸጋገር ወገንና ወገን የሁለት ዓለም ሰዎች ሆነው ቁጭ ይላሉ።
የሁለት ዓለም ሰዎች ተረት፣ የሁለት ዓለም ሰዎች ታሪክ ነው ብለን The Tele of Two People የሚለውን፤ History of Two Worlds እያልን እንፅፋለን። የሁለት ሰዎች ተረት የሁለት ዓለም ሰዎች ታሪክ ይሆንና ያርፋል እንደማለት ነው። ሀገራችን የዚህ ዓይነት ታሪክ በየዘመኑ አይታለች። በታዋቂው የጥንቸልና የዔሊ ውድድር የልጅነት ታሪክ፤ ጥንቸል ዔሊን በመናቋ ተኛች። ዔሊ በቀርፋፋ ግን በማያቋርጥ ጉዞ ቀደመቻት። እንደ ዔሊም ተንቀርፍፈን ነገር ቢገባን እንዴት መታደል ነበር!
“አንዱ ቅጠል እሺ፣ አንዱ ቅጠል እምቢ” ይላሉ ፖርቹጋሎች ሲተርቱ። መደማመጥ መግባባትና መስማማት እየተቸገርን ስንት ዘመን ተጉዘናል። ይሄ ትንሣኤ በአል፤ ትንሳኤውን ይስጠን!!
ቻርለስ ዲከንስ በ“የሁለት ከተሞች ወግ” መጽሐፉ (The Tele of Two Cities) ሲጀምር “ከጊዜ ሁሉ ጥሩ ጊዜ ነው። ከጊዜ ሁሉ የከፋ ጊዜ ነው። የጠቢባን ዘመን ነው። የጅሎችም ዘመን ነው። የዕምነት ዘመን ነው። የክህደትም ዘመን ነው። የብርሃን ወቅት ነው። የጨለማ ወቅት ነው። የተስፋ ፀደይ ጊዜ ነው። ተስፋ - አስቆራጭ የክረምት ጊዜ ነው። ፊታችን ሁሉም ነገር አለ። ፊታችን ምንም ነገር የለም። ሁላችንም ወደሌላኛው ቦታ እየሄድን ነው” ይላል።
እንደኛ አብዮት ግራ የተጋባ የፈረንሳይ አብዮት ገጥሞች ነው። መልካም መልካሙን ለመሰብሰብ ቀና ልቦና ይስጠን!
በተለይ እንደኛ መልከ - ብዙ ህዝብ ባለበት አገር አንዱን መልክ ለይቶ ማየት አይቻልም። ሁሉም ታሪኬ የሚለው፣ ሁሉም እውነቴ የሚለው፤ የየራሱ አመጣጥ አለው። ችግሩ፤ የሚናገርበት ግላዊ መንገድ አለውና መግባባት ጠፋ!! አየርላንዳውያን “እያንዳንዱ ተረት የሚነገርበት ሁለት መንገድ አለው” የሚሉት ለዚህ ነው!
ለማናቸውም ታሪካዊ የህዝብ አዛዥ ታዛዥ መሆን፤ ሦስት መሰረታዊ ነገሮችን ዋቤ ያደርጋል። አንደኛ/ታዘዙ የሚባሉት ህዝቦች ድምፅ እንዳላቸው ሲሰማቸውና ቢናገሩ የሚደመጡ መሆናቸውን ማመን አለባቸው። ሁለተኛ/ ህጉ ተተንባይ (prediticable) ነገም የሚታይ የሚታወቅ መሆን አለበት። በቅጡ ለመገመት በሚቻል መልኩ የዛሬው ህግ ነገ ከሞላ ጎደል ያው ነው ተብሎ የሚታሰብ መሆን አለበት። ሦስተኛ/ባለሥልጣኑ ወይም ገዢው ክፍል ሁሉን እኩል፣ ሁሉን ያለ አድልዎ የሚያይ መሆን አለበት። እንግዲህ፤ የህዝብ ድምፅ፣ ተተንባይ ህግ እና ኢወገናዊነት ሦስቱ ቁልፎች ናቸው። የአባት ያያቶች ታሪክ ምን እንከን፣ ጉድለት ወይም መሰረታዊ አሊያም ተፈጥሮአዊ ህፀፅ እንዳለው መመርመርና በለሆሳስ ማጤን የሁሉም ወገን ግዴታ ነው። ብዙ፤ ሳናገኝ የቀረነው ነገር አለ። ከፖለቲካዊ ነፃነት እስከ እኮኖሚያዊ ነፃነት! የጀርባ አመጣጥና አካሄዳችን በቁጡና በለሆሳስ ካላስተዋልነው፤ የዛሬው ሁሉ - በጄ - ሁሉ በደጄ - ሊሆንልኝ አይችልም። የዝንጀሮ ልጅ እናቱን “ቅቤ ስጪኝ” ቢላት፤ “ቅቤ ቢኖር ያባትህ ታፋ ይህን ይመስል ነበር ወይ? አለችው”፣ የሚለው የጉራጊኛ ተረት፤ ልብ በሉ እሚለን ይሄንኑ ነው።
የትንሣኤንን በዓል በየአቅጣጫው ትንሳኤ አድርጎት ፍቅርና ሰላምን ያጎናፅፈን!!”   

Read 7105 times