Saturday, 19 April 2014 11:55

ኢህአዴግ የሚሰብከንን የሚኖረው መቼ ነው?

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(4 votes)

       ለአስራ ሰባት አመታት የዘለቀ እጅግ መራራና ፈታኝ የትጥቅ ትግል በማካሄድ ደርግን የገረሰሰው ኢህአዴግ፤እነሆ ላለፉት 23 ዓመታት ስልጣንን ተቆጣጥሮ ሀገሪቱን በመምራት ላይ ይገኛል። ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ተከናውነዋል። በፖለቲካው መስክ በተለይም የህዝቦችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በተመለከተ ከተከናወኑት ድርጊቶች ውስጥ ለእነዚህ መብቶች መከበር ህጋዊ ዋስትና ያጐናፀፋቸው ህገመንግስት ፀድቆ፣ወደ ተግባር መገባቱ አንዱና ምናልባትም ዋነኛው ክንውን ይመስለኛል።
ዲሞክራሲ ለሀገራችን የቅንጦት ወይም የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ኢህአዴግ ላለፉት በርካታ አመታት እስኪሰለቸን ድረስ ነግሮናል። በተለይ ደግሞ የህገመንግስቱ ነገር እንዲሁ እንደተራ ጉዳይ የሚታይ ሳይሆን ማንም ቢሆን ልክ እንደታቦት ሊያከብረውና ሊያስከብረው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አበክሮ ሲያሳስበን ኖሯል። ኢህአዴግ ይህንን ማድረጉ አያስወቅሰውም። እንደውም ያስመሰግነዋል እንጂ። ችግሩ የሚመጣው “ኢህአዴግ የሚሰብከውን በተግባር ይፈፅማል ወይ?” ብለን ስንጠይቅ ነው።
በሀገራችን እየተካሄደ ያለውን የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ በተመለከተ ኢህአዴግ ላለፉት 23 ዓመታት ራሱን የሂደቱ ዋና ሻምፒዮን አድርጎ ሲቆጥርና እኛም እንድንቆጥርለት ሲታትር ነው የኖረው። በእርግጥ በዚህ ጉዳይ ላይ በግንባር ቀደምትነት ከሚሰለፉት ኃይሎች አንዱ መሆኑን ማንም ሊክደው አይችልም። ይሁን እንጂ ኢህአዴግ በዚህ እውቅና የማግኘት የማራቶን ሩጫው፣መሰረታዊውንና ዋነኛውን ቁልፍ ጉዳይ አውቆም ይሁን ሳያውቅ የዘነጋው ይመስላል። ብሔራዊ ስልጣን ጨብጠው ህዝብንና ሀገርን የመምራት ታሪካዊ ኃላፊነትን የተሸከሙ መንግስታት፣ በህዝብ ዘንድ የሚኖራቸው እውቅናም ሆነ በታሪክ ማህደር የሚይዙት ሥፍራ የሚወሰነው እወቁኝ ወይም እወቁልኝ በሚል ውትወታ አልያም ሳይታክቱ በሚያደርጉት ሰበካ ሳይሆን በተግባር በሚያከናውኑት ድርጊት ብቻ መሆኑን ኢህአዴግ በእርግጥም አላጤነውም።
ህገ መንግስታዊ እውቅና ያገኙትን የህዝቦች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በማስጠበቅና በመጠበቁ በኩል ኢህአዴግ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሲነግረን የኖረው በተግባር ከሚፈጽመው ድርጊት ጋር ጨርሶ የሚጣጣም አይደለም። ይህ ተራ ስሞታ ወይም መሰረተ ቢስ ውንጀላ እንዳልሆነ ኢህአዴግ ራሱ ያምናል። እርግጥ ነው በየትም አገር ቢሆን የዲሞክራሲ ስርአት በአንድ ጀምበር አልተገነባም። አይገነባምም። ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ደግሞ የህግ የበላይነት መረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አንስተውም። የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣የሀገሪቱ ህጎች በሁሉም ዘንድ መከበርና መጠበቅ አለባቸው። በዚህ ረገድ ከማንም በላይ የግንዛቤ ክፍተት የሚታይበት ቀን ተሌት የህግ የበላይነትን የሚሰብከው ራሱ ኢህአዴግ ነው ብንል አልዋሸንም። ዛሬ በመላው የሃገሪቱ ክልል የህዝቦች አይነኬ ሰብአዊ መብቶች ከህግ አግባብ ውጭ የሚጣሱትና የሚረገጡት በዋናነት በመንግስት አካላት ነው። ህገመንግስታዊ ዋስትና የተሰጣቸው የህዝቦች በነፃ የመደራጀት፣ በነፃ የመሰብሰብ፣ በነፃ ሀሳብን የመግለጽ፣ የፕሬስ ነፃነትና የመሳሰሉት  የዲሞክራሲ መብቶች በዋናነት ኢህአዴግ በሚመራቸው የመንግስት አካላት ይጣሳሉ። ይሄ የሀሰት ስሞታ አለመሆኑን ለማረጋገጥ ደግሞ ከራሱ ከኢህአዴግ ሌላ እማኝ መጥቀስ ፈጽሞ አያስፈልገኝም። ኢህአዴግ ስር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳሉበት ያልነገረን ጊዜ የለም።
ለዚህ ስር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን እንደ መሠረታዊ መንስኤ ማቅረብ እንችላለን። አንደኛው ጉዳይ ኢህአዴግ እንደ ገዢ ፓርቲነቱ የራሱን ሚና ህግ በማውጣትና በማስፈፀም ብቻ ወስኖ፣ህግን ማክበር የሌሎች ሃላፊነት እንደሆነ አምኖ መቀበሉ ይመስለኛል። ሁለተኛው መሠረታዊ ነጥብ ደግሞ ራሱን ከህግ በላይ አድርጐ መቁጠሩና ህግን የመጠበቅ ሃላፊነት እንዳለበት በአስገራሚ ሁኔታ መርሳቱ ነው።
 ህገመንግስቱ የህጐች ሁሉ የበላይ ህግ መሆኑንና እሱን መጣስ ማለት ታቦት እንደ መርገጥ እንደሚቆጠር ወደን እስክንጠላ ድረስ ቢሰብከንም ለራሱ ግን አይጠቀምበትም። ምናልባትም እሱን የሚመለከተው አይመስለውም። ምንም እንኳን ኢህአዴግ የሰው ምክርና ሃሳብ የመቀበል በጎ ልማድ ባያዳብርም እኛ ግን ሁሌም ሳንሰለች መወትወታችን አልቀረም። እስከዛሬ ግን ጆሮ ዳባ ልበስ እንዳለን ነው። አሁንም ግን አንሰለችም። አንድ ቀን ጆሮ ይሰጠናል በሚል ተስፋ፣ ስጋታችንንና ጭንቀታችንን መተንፈሳችን ይቀጥላል። እናም ከዚህ ቀደም እንደምክር የነገርነውን አሁን ደግሞ በተማፅኖ እንጠይቀዋለን “ኢህአዴግ ሆይ፤እንደው በምታምነው ታቦት ይዘንሃል ---- እባክህን ጠብቃችሁ አስጠብቁት የምትለንን ህገመንግስት አንተም አክብረው፣አንተም ጠብቀው” በማለት። እርግጥ ነው በተለያዩ የልማት ሥራዎች ተጠምዷል። ነገር ግን በልማት ሥራ መጠመድ ህገመንግስቱን ከማክበርና ከማስከበር አያግድም። እናም በድጋሚ “የተከበርክ ኢህአዴግ፣ እባክህ ስለ ፈጣሪ ብለህ ህገመንግስቱን አክብርልን!” እንለዋለን።
ኢህአዴግ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያላቸውን ሚና በተመለከተ ሲገልፅ፤“ለሀገራችን የዲሞክራሲ ግንባታና ዴሞክራሲያዊ ባህል መዳበር ጠንካራና ህዝባዊ መሰረት ያላቸው የተቃዋሚ ፓርቲዎች መኖር በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ መፈለግ ብቻ ሳይሆን እንዲፈጠሩ ለማድረግም የድርሻዬን እወጣለሁ” ብሎ ነበር - ያውም በአደባባይ። ኢህአዴግ ይህን ኮሚክ የሆነ የፖለቲካ ጨዋታ ሲያስብ “ዓለም መጭበርበርን ትወዳለች” የሚለው የሆላንዳዊያን የተለመደ አነጋገር ትዝ ሳይለው አይቀርም። ኢህአዴግ ጨርሶ ያልተረዳው ነገር ቢኖር፣ እኛ አረፋው ሁሉ ቢራ አለመሆኑን በሚገባ ማወቃችንን ነው። ላለፉት 23 ዓመታት በዓይናችን እንዳየነው፣ ጠንካራ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ መፈለጉን የሚጠቁም አንዳችም የረባ ጥረት አላደረገም። እንደውም ያሉት እንዲከስሙ የበለጠ ተንቀሳቅሷል ቢባል ይሻላል።
የመጀመርያውን ቃሉን ያልፈፀመው ኢህአዴግ፣ የማታ ማታ ከተጠያቂነት ለማምለጥ ሲል “እንደአለመታደል ሆኖ ጠንካራ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሊፈጠሩ ባለመቻላቸው ኢህአዴግ የአውራ ፓርቲነትን ከባድ ቀንበር ለመሸከም ተገዷል” አለን። በአንድ ወገን ስትመለከቱት እውነቱን ነው ያስብላል። በአባላት ብዛት፣ በቢሮና መሰል ተቋማት ጥንካሬ እንዲሁም በገንዘብ አቅም ከታየ፣ በእርግጥም ኢህዴግ አውራ ፓርቲ ነው። በዚህች አገር ላይ እንኳንስ የሚፎካከረው አጠገቡ ድርሽ የሚል አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ አስሶ ማግኘት አይቻልም። ግን ኢህአዴግ የሚፈፅማቸው አንዳንድ ድርጊቶች እንኳንስ ከአውራ ፓርቲ ከተራ ፓርቲም የሚጠበቅ አይደለም። ከሰባት ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉት፣ በየክልሎቹ ግዙፍ የቢሮ ህንፃዎችና ፈርጣማ የገንዘብ ጡንቻ ባለቤት የሆነው ኢህአዴግ፤ እንኳን ሊፎካከሩት ቀርቶ አይኑ ውስጥ ቢገቡም የማይቆረቁሩት የተቃዋሚ ፓርቲዎች የኪራይ ቢሮ እንዳያገኙ፣ የስብሰባ አዳራሽ እንዳይከራዩ፣ ህዝባዊ ስብሰባም ሆነ ቅስቀሳ እንዳያደርጉ፣ አባላትን በነፃነት እንዳይመለምሉ ---- እንቅፋት መፍጠሩ ከአውራ ፓርቲነት ያሳንሰዋል። እውነቱን ለመናገር ግን እንዲህ ያለ የሰፈር ጉልቤ ዓይነት የወረደ ተግባር ራሱን አውራ ነኝ ከሚል ፓርቲ ጨርሶ አይጠበቅም። የአውራ ፓርቲነት ከባድ እዳ ለመሸከም ተገድጃለሁ እያለ ዘወትር የሚነግረን ኢህአዴግ፤የአንድ እጅ ጣት የማይሞሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ከህግ አግባብ ውጪ ስብሰባ እንዳያካሂዱ በእስር ማዋከብና የሞባይል ስልካቸውን ኬሚካል ውስጥ መንከርን የመሰለ እጅግ አስነዋሪ ድርጊት መፈፀሙ እንኳን ለሌላው ለደጋፊዎቹም ሃፍረት መፍጠሩ አይቀርም። ወደፊት አገሪቱን ለሚረከቡት የአዲስ ትውልድ አባላትም መጥፎ አርአያ መሆኑ አያከራክርም። ኢህአዴግ መቼ ይሆን “ምራቁን እንደዋጠ ፓርቲ” ማሰብና መንቀሳቀስ የሚጀምረው? ያቺ ቀን ትናፍቀኛለች።


Read 3584 times