Saturday, 19 April 2014 12:38

ሠራዊቱን ድል የነፈገው ማን ነው? በችሮታ የሚገኝ ድልስ አለ?

Written by  ካሌብ ንጉሤ
Rate this item
(5 votes)

የመጽሐፉ ርዕስ - ሁሉም ነገር ወደ ሰሜን ጦር ግንባር
የገፅ ብዛት - 705
የታተመበት ዘመን - እ.ኤ.አ 2012
አታሚ - ናፍቆት ኢትዮጵያ መጋዚን
ጸሐፊ - ብ/ጄኔራል ውበቱ ፀጋዬ
የሽፋን ዋጋ - 30 ዶላር
መቅድመ ኩሉ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባለፈው መንግሥት የኢትዮጵያን ሠራዊት በተለያየ ደረጃ ሲመሩ የነበሩ በርካታ ጄኔራል መኮንኖች ግለ ታሪካቸውን እየጻፉ አስነብበውናል። የሠራዊቱን ወኔ፣ ያለፈበትን ወታደራዊ ውጣውረድ፣ ያገኘውን ድል፣ ከውስጥም ከውጭም የነበረበትን ጫና፣ በኋላም የተከሰተው አስከፊ ሽንፈት ምን ይመስል እንደነበረ ከመጻሕፍቱ ማንበብ በመቻላችን ጸሐፊዎቹን “በርቱ” ማለት ይገባናል። ምክንያቱም መኮንኖቹ የሀገራችንን ዳርድንበር ለማስከበር ቀን ከሌሊት ሲዋትቱ ያዩትን፣ የኖሩትን፣ የተገነዘቡትንና ከህይወት ልምዳቸው የተማሩትን አካፍለውናልና ንፉግ ባለመሆናቸው ምስጋና ሲያንሳቸው ነው።
ብ/ጄኔራል ተስፋዬ ኃ/ማርያም፣ ብ/ጄኔራል ካሣዬ ጨመዳ፣ እና መሰሎቻቸውን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። የብ/ጄኔራል ውበቱ ፀጋዬ “ሁሉም ነገር ወደ ሰሜን ጦር ግንባር” መጽሐፍም ከእነዚሁ አይነት ግለ ታሪኮች የሚመደብ ነው።
በመሠረቱ ግለታሪክ በሚጻፍበት ወቅት ህዝቡ ሊያውቅ የሚገባው የባለታሪኩን ደግ ነገሮች ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ማንነቱን ነው። ማንኛውም ሰው የመለኮት ባህርይ የለውም፤ እንዲህ ባለመሆኑም ከእንከን የፀዳ ሊሆን አይችልም።
ስለሆነም ግለታሪኩን በሚጽፍበት ጊዜ ጥንካሬውንና ድክመቱን፣ ድሉንና ሽንፈቱን፣ ፍቅሩንና ጥላቻውን፣ ለጋስነቱንና ንፍገቱን፣ ሃብትና ድህነቱን፣ ክብሩንና ውርደቱን ወዘተ መሆን አለበት። ይህ ባልተሟላ መልኩ የሚጻፈው ግለታሪክ ሁሉ ምሉዕነት ይጐድለዋል።
ለዚህ ዓይነቱ ግለታሪክ አጻጻፍ የበጅሮንድ ተክለሐዋርያት ተክለማርያምንና የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን መጻሕፍት ማየት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በዚህ ስሌት “ሁሉም ነገር ወደ ሰሜን ጦር ግንባር”ን ስንመዝነው በርካታ ህፀፅ እናገኝበታለን። ህፀፁ የሚጀምረው ከርዕሱ ነው። እንደሚገባኝ ጸሐፊው ርዕሱን የወሰዱት በ1969 ዓ.ም ዚያድባሬ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ሻለቃ መንግሥቱ ኃ/ማርያም የክተት ጥሪ ለመላ የኢትዮጵያ ህዝብ ካስተላለፉ በኋላ ካሰሙት መፈክር ነው። “አይ ከዚያ አይደለም” ቢባልም ርዕሱ ለአንድ ግለታሪክ መጽሐፍ የሚሆን አይደለም።
የመጽሐፉ ይዘት በአጭሩ
ጄኔራሉ በመግቢያቸው ላይ ትኩረት መስጠት የፈለጉት ከ1967 ዓ.ም ሐምሌ እስከ 1981 ዓ.ም በነበሩት ዓመታት በተለይ በኤርትራ ስለተካሄዱት ውጊያዎች ቢሆንም፣ በአሰልጣኝነት፣ በሰልጣኝነት፣ በባሌና በሲዳማ በተካሄዱ የህዝብ አመጾች ስለተሳተፉባቸው ውጊያዎች፣ በኤርትራ ክ/ሀገር በተካሄዱ ውጊያዎች በተለያየዩ ደረጃዎች በአዛዥነትና በአዝማችነት የተሳተፉባቸው የጦር ሜዳ ውሎዎች፣ በፕሬዚዳንት መንግሥቱ አማካሪነት፣ የብሔራዊ ውትድርና ሲቪል መከላከል ዋና መምሪያ ሃላፊ በመሆን የሠሩባቸውንና በኋላም በ1981 ዓ.ም ተሞክሮ በከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ተሳትፈው መታሰራቸውን ይገልፅልንና ወደ መጨረሻ የህይወት ታሪካቸውንና “ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ጀግኖች” ያላቸውን የተወሰኑ ግለሰቦች አጭር አጭር ታሪክ በመጠቋቆም ይጠናቀቃል።
የመጽሐፉ ደካማ ጐኖች
“ሁሉም ነገር ወደ ሰሜን ጦር ግንባር” መጽሐፍ ሊያሳየን የተፈለገው በሰሜን ኢትዮጵያ፤ ምን አልባትም ከህወሃት እና ከሻዕቢያ ጋር የተካሄዱትን አስከፊ የጦርነት ቀጣናዎች ይመስላል፤ ግን ኤርትራም ሆነ ትግራይ ሳይወስን እዚያና እዚህ ይወራጫል። ለምሳሌ ምዕራፍ አንድ የሚጀምረው “ኮንጐ ዛየር” ብሎ ነው። ኮንጐ ዛየር የሚባል ቦታ ደግሞ እንኳንስ ኤርትራና ትግራይ ቀርቶ በመላ ኢትዮጵያም የለም፤ ኮንጐ ሌላ፤ ሰሜን ሌላ።
በምዕራፍ ሁለት ላይም ጸሐፊው በባሌና ሲዳማ ክፍላተ ሀገር የዘመቻ መኮንንና የሻምበል አዛዥ ሆነው ስለመስራታቸው ይነግረናል፤ ሁለቱ ክፍላተ ሀገር በጦርነቱ ተማርረው ወደ ሰሜን አቅጣጫ የዞሩበት የታሪክ አጋጣሚ ነበር ካልተባለ በቀር ርዕሱና ይዘቱ አይገናኙም።
ከዚህም ሌላ መጽሐፉ የታሪክ ፍሰት ችግር በብዛት ይስተዋልበታል፤ ስለ 1960ዎቹ የሠራዊት ውሎ ሲዘረዝር ይቆይና ድንገት ወደ 1927ዓ.ም ተመልሶ ስለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጦር ት/ቤት አጀማመር ይተርካል (ገፅ 60-63) ልብወለድ ቢሆን ኖሮ በምልሰት ሊያሳየን መብት ነበረው፤ ይህ ታሪክ ነው። ታሪክ በመሆኑም ቀጥታ ፍሰቱን ይዞ መጓዝ አለበት እንጂ ወዲያና ወዲህ መውረግረግ ያለበት አይመስለኝም። በትዝታ ወይም በምልሰት መተረክ ካለበትም ለዚህ የሚያበቃ ተጨባጭ ምክንያት ያስፈልጋል።
ስለ ሰሜን ግንባር ሲያወራ ቆይቶም በመሃሉ የሶማሊያን ወረራ ያለ ምክንያት ይደነጉራል (ገፅ 80-97) ይህ ሁሉ መውረግረግ የሚመጣው ርዕሱ ላይ ጥንቃቄ ባለመደረጉ ነው፤ ርዕሱ “ሁሉም ነገር ወደ ሰሜን ጦር ግንባር” ባይባል ኖሮ ጸሐፊው በደረሱበት ቦታ ሁሉ ታሪኩን አብሮ ማሽከርከር ይቻል ነበር። ግን ርዕሱም ዓመተ ምህረቱም (ከ1967-1981) ተብሎ መወሰኑም በታሪኩ ላይ ጣጣ አስከትሏል።
በሰሜንም፤ በምስራቅም፣ ሌላው ቀርቶ በኮንጐ ዛየር የነበረውን የጸሐፊውን ድርሻ ሲነግረን ቆይቶ ታሪኩ ከተደመደመ በኋላ እንደገና “የህይወት ታሪኬ” ብሎ ገፅ 632 ላይ ይቀጥላል፤ ያንን ያህል ሰፊ (631) ገፅ የያዘው የመጽሐፍ ክፍል ታዲያ የማን ታሪክ ነበር?  ቢባል መልስ የሚገኝለት አይመስለኝም። እናም የጄኔራሉ ታሪክ አለ አግባብ ተደርቷል፤ እንደነ ብ/ጄኔራል ካሣዬ ጨመዳና ብ/ጄኔራል ተስፋዬ  ኃ/ማርያም “የጦር ሜዳ ውሎ” የሚል አይነት ርዕስ ቢሰጥ ኖሮ ጸሐፊው የፈለጉትን፤ ግን የታሪካቸውን ቅደም ተከተል ጠብቀው መጻፍ ይችሉ ነበር።
በመጨረሻው ምዕራፍ (28) ላይ “ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ጀግኖች” ብለው የደረደሯቸው ሰዎች ታሪክም ለመጽሐፉ ትርፍ አንጀት ነው። ከበሽታነቱ በቀር የሚጠቅመው አንድም ነገር የለም፤ ከተዘረዘሩት ግለሰቦች ውስጥ አሉላ አባ ነጋ፣ ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ራስ አበበ አረጋይ፣ ሜጄር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ሌ/ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም፣ ሌ/ጄኔራል ጃገማ ኬሎ፣ ወዘተ እና በግንቦት 1981 ዓ.ም የመንግሥት ግልበጣ ሴራ የተሳተፉ የተወሰኑ መኮንኖች ታሪክ ባልተሟላ መልኩ ተካትቷል።
አሁንም የመጽሐፉን ርዕስ አንርሳ “ሁሉም ነገር ወደ ሰሜን ጦር ግንባር” ነው። ትኩረት ተሰጥቶ የተጻፈው (በጄኔራል ውበቱ መግቢያ እንደተገለፀው) ከ1967 -1981 ዓ.ም በኤርትራ ስለነበረው ወታደራዊ ጣጣ ነው። ታዲያ ከላይ ስማቸው የተዘረዘሩት ሰዎች በተጠቀሰው ዘመንና ቦታ ነበሩ? ለአንድነት በተካሄደው ጦርነትስ ድርሻ ነበራቸው? መልሱ “በፍጹም” የሚል ነው። እርግጥ ነው ከላይ የተጠቀሱት ሰዎች ከመገንጠል እና አላስገነጥልም ትግሉ ጋር ባይያያዝም ለሀገራቸው በየዘመናቸው ታላላቅ ተግባራትን አከናውነዋልና እጅግ የሚከበሩ ሰዎች ናቸው፤ የእኔ አስተያየት ከዚህ መጽሐፍ ጋር የሚያያይዛቸው አንዳችም ጉዳይ የለም ነው።
ሆኖም እንደ ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ፣ ኮሎኔል አስማማው ይመር፣ ኮሎኔል ማሞ ተምትሜ (የናቅፋው ነብር)፣ የመሳሰሉትን መጥቀሳቸው ተገቢ ነው። ከስድስት ወራት ከበባ በኋላ የወገን ጦር እንደማይደርስላቸው ሲያረጋግጡ ሻዕቢያ ምሽግ ውስጥ ገብተው አንጀት ጉበቱን አውጥተው የሚመሯቸውን ጥቂት ወታደሮች ይዘው ከወገን ጋር የተቀላቀሉት ብቸኛው የህብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ ተሸላሚ ጄኔራል ተሥፋዬ ኃ/ማርያም፤ “ዳግማዊው ቴዎድሮስ” ተብለው የሚታወቁት ጄኔራል ተሾመ ተሰማ፣ ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ፤ እንዲሁም ቦንብ በራኬት እየቀለቡ ከሻዕቢያ ምሽግ ላይ ይጥሉ የነበሩ ጀግኖች፣ በፈንጂ ላይ እየተንከባለሉ ለቀሪው ጦር በር ይከፍቱ የነበሩ አንበሶች አለመጠቀሳቸው ግን በእጅጉ አስገርሞኛል።
ጄኔራል ተስፋዬ ኃ/ማርያም‘ኮ ዛሬም ሻዕቢያ ከሚያደንቃቸው ኢትዮጵያዊ ጀግኖች አንዱ ናቸው። ኮሎኔል ማሞ ተምትሜንና ጄኔራል ተሥፋዬን የማያውቅ ኢትዮጵያዊ መኮንን ቀርቶ የሻዕቢያ አባል አለ ብዬ አላምንም። ዓላማዬና እነራስ አበበ ሲጠቀሱ እንዴት እኒህ ጀግኖች አልታወሱም የሚል ነው፤ ራስ አበበ አረጋይ ምን አልባት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ከተዋሃደች በኋላ አስመራንና ምፅዋን የመጐብኘት እድል ገጥሟቸው ይሆናል እንጂ ከመጽሐፉ ዓላማ ጋር የሚያገናኛቸው አንድም ምክንያት የለም፤ ራስ አበበኮ በ1935ቱ መፈንቅለ መንግሥት በእነ ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ ተረሽነዋል።
ራስ አሉላም ቢሆኑ ጣሊያንን ዶጋሊ ላይ የቀጡ፣ ግብጾችን ጉንደትና ጉራዕ ላይ ያርበደበዱ ቀዳሚ ጀግና እንጂ ከ “ሁሉም ነገር ወደ ሰሜን ጦር ግንባር” ጋር የሚያያይዛቸው ታሪክ የለም። ፊታውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴማ እንዲያውም ሊነሱበት ከማይገባ ቦታ ነው በግድ የተዶሉት። ፊታውራሪ የአጤ ምኒልክ ታማኝ ባለሟልና ነገር አዋቂ እንጂ ከሰሜኑ ጦር ግንባር ጋር የሚያገናኝ ምንም ታሪክ የላቸውም። ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም ለመገደላቸው ሰበብ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ “ሻዕቢያን ውስጥ ውስጡን ይረዳል” ተብለው ነው። ታዲያ ከየት በመጣ ቸርነት ይሆን የ “ሁሉም ነገር ወደ ሰሜን ጦር ግንባር” ታዳሚ የሆኑት?
በሰሜን ጦር ግንባር ተአምራዊ የሚመስሉ ተግባራትን እየፈፀሙ ሻዕቢያ ሳይቀር በስማቸው ቦታ የሰየመላቸው እንደሚሊሻ ወታደር ታምሩ ያሉ ጀግኖችን ጄኔራል ውበቱ ይረሳሉ ብሎ መገመት ቢከብድም እነ ራስ አሉላ አባ ነጋን፣ ራስ አበበ አረጋይንና ፊታውራሪ ኃ/ጊዮርጊስ ዲነግዴን ሲያስታውሱ በዕዛቸው ስር ከነበሩ በርካታ ጀግኖች የጥቂቱን እንኳ አለመጥቀሳቸው ንፍገት ያስመስላልና ሊያስቡበት ይገባ ይመስለኛል።
ሌላውና ያስገረመኝ ነገር በጀግንነቱ ሻዕቢያ ሲርበደበድለት የኖረው የናደው ዕዝ መጋቢት 1980 ዓ.ም በጠላት የተደመሰሰበትን ሁኔታ የገለፁሰበት መንገድ ነው። ትልቁንና የ2ኛው አብዮታዊ ሠራዊት ዕዝ አዛዥነትን የሚያህል ሥልጣን ይዘው ሠራዊቱ በበላይ አመራር ትብብር ማጣት መደምሰሱን በመጽሐፉ የተነገረን የሚዋጥ አይመስልም፤ “ረዳት ጦር እንዲመጣልን የበላይ አካልን ብንጠይቅ እንደማይላክልን በግልጽ ተነግሮናል (ገፅ 507)” የተባለው በቂ ምክንያት አይመስልም።
የዚህ ታሪክ ጸሐፊ የግዙፉ 2ኛው አብዮታዊ ሠራዊት ዋና አዛዥ እስከሆኑ ድረስ በኤርትራ ውስጥ ከነበረው ከ300 ሺህ ያላነሰ ሠራዊት ከቦታ ቦታ አዘዋውሮ ማዋጋት አይቻልም ነበር ወይ? ይህን ለማድረግስ ምን የሚከለክል ነበር?  ሻዕቢያ ከዚህ የሚበልጥ ጦርና አቅም ነበረው? እንቆቅልሽ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ “ሠራዊቱን ድል የነፈገው ማን ነው? በችሮታ የሚገኝ ድልስ አለ?” የሚል ጥያቄ ለጸሐፊው ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል።
መጽሐፉ ልዩ ልዩ ፎቶግራፎችን ማካተቱ በጥንካሬ የሚታይ ቢሆንም የፎቶግራፍ መግለጫዎች ብላሽ ናቸው፤ ለምሳሌ ገጽ 16 ላይ የአራት ሰዎች ፎቶ እየታየ “ሻለቃ አሰፋ አሳምነውና የመ/አለቃ ውበቱ ፀጋዬ በቆቃ ወረዳ የከባድ ሞርታር ልምምድ ላይ” ይላል። ገፅ 33 ላይም ከሶስት ሰዎች ምስል ስር “ሻምበል ውበቱ ፀጋዬ በአሜሪካን አገር” የሚል ድፍን ያለ መግለጫ ተቀምጧል። ግን መግለጫው ሌላ መግለጫ ያስፈልገዋል፤ እኒህን ለአብነት ያህል ጠቀስሁ እንጂ በገፅ 15፣ 70፣ 459፣ ወዘተ ተመሳሳይና ከንቱ የፎቶግራፍ መግለጫዎች ተቀምጠዋልና ወይ ባይጻፍ ከተጻፈ ደግሞ የባለ ምስሎቹ ስም በትክክል መጻፍ ነበረበት።
በአጠቃላይ መጽሐፉ ድጋሚ መታተሙ ስለማይቀር በቋንቋ፣ በታሪክ ፍሰት፣ በአርትኦት፣ በመዋቅርና በመሳሰሉት ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ እንደገና ሊሠራ፤ ከተሠራም የግለ ታሪክ አጻጻፍ መስፈርቶችን አሟልቶ ቢጻፍ የተሻለ ይሆናል፤ በመጨረሻም “የያዘውን ከወረወረ ፈሪ አይባልም” እንደሚባለው ጄኔራል ውበቱ ያላቸውን ስላካፈሉን እናመሰግናለን።

Read 2041 times