Saturday, 26 April 2014 12:06

እነ አቶ መላኩ ፈንታ በድጋሚ ለብይን ተቀጠሩ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

           በፌደራል የስነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ለቀረበባቸው የከባድ ሙስና ክስ ቀደም ባሉት ቀጠሮዎች የክስ መቃወሚያቸውን ያቀረቡት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታን ጨምሮ በ3 መዝገቦች ክስ የቀረበባቸው ተከሳሾች፣ ያቀረቡትን መቃወሚያ መርምሮ ብይን ለመስጠት ፍ/ቤቱ ለሚያዚያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም በድጋሚ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ከትናንት በስቲያ ሐሙስ የዋለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት፣ አቶ መላኩ ፋንታ እና ምክትላቸው አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስ 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪ ሆነው የቀረቡባቸውን የሶስት መዝገብ ተከሳሾች በችሎቱ ስለመቅረባቸው ስም በመጥራት ካረጋገጠ በኋላ፣ የሁሉም መዝገቦች ብይን ሙሉ ለሙሉ ተሠርቶ ባለመጠናቀቁ ተጨማሪ አጭር ቀጠሮ መስጠት ማስፈለጉን አስረድቷል፡፡
ፍ/ቤቱ በቀጣዩ ቀጠሮ የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ እና አቃቤ ህግ ለመቃወሚያው የሰጠውን ምላሽ መርምሮ ብይን እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ ተከሳሾቹ የክስ መቃወሚያቸውን እንዲሁም አቃቤ ህግ ምላሹን ለፍ/ቤቱ በፅሁፍ ያቀረቡ በመሆኑ ዝርዝሩን ማግኘት አልተቻለም፡፡

Read 1836 times