Saturday, 26 April 2014 12:08

አምባሳደሩ ታስረው ስለነበሩ ስዊድናውያን ጋዜጠኞች አፈታት የሚተርክ መፅሃፍ አወጡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

ከኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ጋር ለሽብር ተልዕኮ ሲንቀሳቀሱ ነበር በሚል በቁጥጥር ስር ውለው የተፈረደባቸውን ሁለቱን የስዊድን ጋዜጠኞች በይቅርታ ለማስፈታት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተደረገውን ድርድር እና አጠቃላይ ሂደት የሚያትት መፅሐፍ በቀድሞው የስዊድን አምባሳደር ተዘጋጅቶ  ለንባብ በቃ፡፡
ለ4 ዓመታት በኢትዮጵያ የስውዲን አምባሳደር በነበሩት ዮስ ቡድላንደር የተፃፈው “ዲፕሎማሲ” የተሰኘው መፅሃፍ፤የሁለቱ ጋዜጠኞች ጉዳይ እንዴት ውስብስብ እንደነበርና የስዊድን መንግስት እንዲህ አይነት ችግሮች ሲያጋጥሙት ዜጎቹን ለመታደግ እንዴት እንደሚንቀሳቀስ ይተነትናል ተብሏል፡፡
የመፅሃፉ ደራሲ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት፤በስዊድንና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ከምርጫ 97 በፊት በሁሉም መስክ መረዳዳትና መተባበሮች ነበሩ፣ከምርጫው በኋላ ግን በሰብአዊ መብትና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ላይ አብዛኞቹ ምዕራባዊያን ሃገሮች ሲያደርጉት እንደነበረው የስዊድን መንግስትም በጉዳዩ ላይ ወቀሳ በመሰንዘሩ፣የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት በመጠኑ ሻክሮ ነበር ብለዋል፡፡ አምባሳደሩ አክለውም በሁለቱ ሃገራት መካከል የነበረው የቀደመ ግንኙነት መልካም መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት የጋዜጠኞቹ ጉዳይ በፍጥነት እልባት ያገኛል የሚል ተስፋ የነበራቸው ቢሆንም በተቃራኒው  በአታካችና ውስብስብ ሂደቶች ውስጥ ለማለፍ ተገደዋል ብለዋል፡፡
አምባሳደሩ ጋዜጠኞቹን ለማስፈታት ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ብቻ ሳይሆን እንደ ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅ ከመሳሰሉት ሰዎች ጋርም ይገናኙ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ “ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅ የማከብረውና የማደንቀው ሰው ነው፡፡ ጋዜጠኞቹን የማስፈታት ሂደት ቀልጣፋ እንዲሆን ተባብሮናል” ሲሉ በመፅሃፋቸው ገልፀዋል፡፡
ጋዜጠኛ ማርቲን ሲመይ እና ፎቶግራፈር ጆን ፐርሰን በሐምሌ 2003 ዓ.ም በሶማሌ ክልል በኦጋዴን አካባቢ በሽብርተኝነት ከተሰየመው የኡጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ጋር ሲንቀሳቀሱ ከ150 ያህል ታጣቂዎች ጋር በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት፣ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሃገር ለመግባት መሞከርን ጨምሮ የሽብር ቡድን መደገፍና ማበረታታት እንዲሁም ማስተዋወቅ የሚሉ ክሶች ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ወራት በፈጀው የፍርድ ሂደትም ሁለቱ ጋዜጠኞች እያንዳንዳቸው በ11 ወራት እስራት እንዲቀጡ የተወሰነ ሲሆን ለዓመት ከሁለት ወር ያህል ከታሰሩ በኋላ በይቅርታ ተለቀው ወደ አገራቸው መሄዳቸው  ይታወቃል፡፡

Read 2682 times