Saturday, 26 April 2014 12:11

ዛሬ በሚሌኒየም አዳራሽ ሊካሄድ የታቀደው የሙዚቃ ኮንሰርት ተራዘመ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

እስካሁን 5.2 ሚሊዮን ብር ወጥቶበታል ተብሏል

በ“አውሮራ ኤቨንትስ ኦርጋናይዘር” አዘጋጅነት ዛሬ በሚሌኒየም አዳራሽ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው “ሬጌ ዳንስሆል ኢን ኢትዮጵያ ቁጥር አንድ” የሙዚቃ ድግስ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን አዘጋጆቹ ገለፁ፡፡ ኮንሰርቱ የተራዘመው ዛሬ ምሽት በጊዮን ሆቴል ከሚቀርበው የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “ወደ ፍቅር ጉዞ”  የሙዚቃ ድግስ ጋር መደራረብ እንዳይፈጠር ታስቦ እንደሆነ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡
የ“አውሮራ ኤቨንትስ ኦርጋናይዘር” ስራ አስኪያጆች ከትናንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ በሚሌኒየም አዳራሽ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ኮንሰርቱ መራዘሙ እስከተወሰነበት ጊዜ ድረስ ለዝግጅቱ 5.2 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡ አዘጋጆቹ ለኮንሰርቱ መራዘም የቴዲ አፍሮን የሙዚቃ ድግስ እንደ ምክንያት ቢያቀርቡም ምንጮች እንደሚሉት፤ በኮንሰርቱ ላይ ይዘፍናል የተባለው ጃማይካዊው ድምፃዊ ቢዚ ሲግናል ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ባለመቻሉ ነው፡፡ ጃማይካዊው ዘፋኝ ባለው የፀረ ተመሣሣይ ፆታ አቋሙ የተነሳ እንግሊዝ፣ አሜሪካ እና ካናዳ ወደ አገራቸው እንዳይገባ ከልክለውታል የሚሉት ምንጮች፤  የሚመጣበት አውሮፕላን ደግሞ ከጃማይካ ተነስቶ እንግሊዝና አሜሪካ የሚያርፍ በመሆኑ በበረራ ችግር  ማምጣት አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡
አርቲስት ቢዚ ሲግናል፤ በዚህ አቋሙ የተነሳ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ካናዳ እንዳይገባ መከልከሉን ያመኑት የኮንሰርቱ አዘጋጆች፤ኮንሰርቱ የተራዘመው ግን ፈፅሞ በዚህ ምክንያት አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ “ሬጌ ዳንስሆል ኢን ኢትዮጵያ ቁጥር አንድ” የሙዚቃ ድግስ ላልተወሰነ ጊዜ የተራዘመበት ዋነኛ ምክንያት፣ “በአዲስ አበባ ከሚኖረው አራት ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ ለኢንተርቴይንመንት ፍቅር ያለው ጥቂቱ ሲሆን ከእዚህም ውስጥ ሁለት ቦታ ተከፍሎ የሚመጣው አመርቂ አይሆንም ብለን በማመናችን ነው” በማለት በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
ኮንሰርቱ ለመቼ እንደተራዘመ የተጠየቁት አዘጋጆቹ፤ ከሶስት ቀናት በኋላ ይሄንኑ ለማሳወቅ ሌላ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ ይህን ፕሮግራም ስታቅዱ ቴዲ አፍሮ ኮንሰርት እንዳለው አታውቁም ነበር ወይ? በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄም “በእርግጥ እናውቃለን፤ነገር ግን ከዚያ በኋላ ባደረግነው ጥናት፣ ወደ ድግሱ የሚመጣው ህዝብ ሁለት ቦታ ሊከፋፈል አይገባም፤ አውሮራ ኤቨንትስ የሚያዘጋጀው ኮንሰርትም ብራንድ አይደንቲቲው መጠበቅ አለበት በሚል ለተከታታይ ሶስት ቀናት ከፍተኛ ውይይትና ምክክር ከተደረገ በኋላ እንዲራዘም ተደርጓል” ብለዋል አዘጋጆቹ፡፡
በተለይ አርቲስት ቢዚ ሲግናል፣ሶስት አገሮች እንዳይገባ ከመከልከሉ ጋር ተያይዞ ከአዲስ አድማስ ለተነሳው ጥያቄ አዘጋጆቹ ሲመልሱ፣ “አርቲስቱ እንዳይገባ የተደረገው እንግሊዝ፣ አሜሪካና ካናዳ ብቻ ስለሆነ ከጃማይካ ቱርክ፣ከቱርክ ፍራንክፈርት፣ ከዚያ አዲስ አበባ መምጣት ይችል ነበር ካሉ በኋላ ዋናው ትኩረታችን የኮንሰርቱ መደራረብ ስለሆነ፣ ተመካክረን እስክንወስን ትኬት መሸጥ እንኳን አልጀመርንም ነበር ብለዋል፡፡
ኮንሰርቱ በመራዘሙ ለአርቲስት ቢዚ ሲግናል፣ቀደም ሲል ከተከፈለው የ10 በመቶ ጭማሪ ክፍያ ማድረጋቸውንም አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡

Read 2954 times