Saturday, 26 April 2014 12:15

ግብፅ ለህዳሴው ግድብ ብድር እንዳይገኝ ታሴራለች ስትል ሱዳን አወገዘች

Written by 
Rate this item
(27 votes)

 በግድቡ ላይ ለሚከሰት አደጋ፣ ሙሉ ለሙሉ ተጠያቂ የማደርገው ግብጽን ነው ብላለች - ሱዳን
“በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጽኑ እምነት አለን፣ የገንዘብ ጉዳይ አያሰጋንም!” - ሳሊኒ ኮንስትራክሽን

ግብፅ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አለማቀፍ የገንዘብ ብድሮች፣ ከውጭ መንግስታት እንዳይገኙ በማድረግ ግንባታውን ለማደናቀፍ እያሴረች ነው ስትል ሱዳን አወገዘች፡፡
የሱዳን ምስራቃዊ ብሉ ናይል ግዛት ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ሁሴን አህመድ፣ ኢትዮጵያ በማከናወን ላይ ለምትገኘው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውሉ አለማቀፍ ብድሮችን እንዳታገኝ ለማድረግ በግብጽ በኩል በድብቅ እየተከናወኑ ያሉት አግባብ ያልሆኑ ተግባራት፣ ግድቡ በገንዘብ እጥረት ሳቢያ ከሚፈለገው የጥራት ደረጃ በታች እንዲሰራና ለአደጋ እንዲጋለጥ ሊያደርጉ ይችላሉ በማለት ድርጊቱን ማውገዛቸውን ሱማሌላንድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ግድቡ ከሚፈለገው የግንባታ ጥራት በታች የሚሰራ ከሆነ፣ በረጅም ጊዜ ሂደት የሚፈርስበት ዕድል እንደሚኖርና ተያይዞ የሚከሰተው የጎርፍ አደጋም ሱዳንን ክፉኛ ሊጎዳ የሚችል በመሆኑ፣ ሱዳን የግብጽን ድርጊት አጥብቃ እንደምትቃወመውና ለሚደርሰው አደጋ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ እንደምታደርጋት ባለስልጣኑ መናገራቸውን ዘገባው ያስረዳል፡፡
የሱዳን ምስራቃዊ ብሉ ናይል ግዛት፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከሚከናወንባት የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሏ ጉባ ጋር በቅርብ ርቀት የሚካለል እንደመሆኑ፣ በግድቡ ላይ የመፍረስ አደጋ ቢከሰት፣ ግዛቱ በጎርፍ አደጋ ሙሉ ለሙሉ ሊወድም እንደሚችል ባለሙያዎች የሰጡትን አስተያየት ያቀረበው ዘገባው፣ ይህም የግዛቱን ባለስልጣናት እንዳሳሰባቸው ጠቁሟል፡፡
ግብጽ በግድቡ ላይ ባለቤትነት እንዲኖራት እንጂ፣ ስለ አካባቢው ደህንነት ደንታ የላትም ያሉት ባለስልጣኑ፣ የግድቡን ግንባታ በራሷ ወጪ ለማከናወንና በበላይነት ለማስተዳደር ከመጀመሪያ አንስቶ ፍላጎት እንደነበራት ተናግረዋል፡፡
“በግንባታ ጥራት መጓደል ሰበብ በግድቡ ላይ ለሚፈጠር የመፍረስ አደጋና ከዚያ ጋር ተያይዞ በግዛታችን ላይ ለሚከሰት የጎርፍ አደጋ፣ ሱዳን ሙሉ ለሙሉ ተጠያቂ የምታደርገው ግብጽን ነው” ያሉት ባለስልጣኑ፣ ግብጽ አስር አገራት በጋራ በሚጠቀሙበት የአባይ ወንዝ ላይ ኢኮኖሚዋን ሙሉ ለሙሉ ጥገኛ ከማድረግ ይልቅ፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዋን በሌሎች መስኮችም ማስፋፋት እንደሚኖርባት ተናግረዋል፡፡
ግብጽ ከረጅም አመታት በፊት የገነባችው አስዋን ግድብ፣ የኑብያ ህዝቦችን ህልውና ክፉኛ መጉዳቱንና ጥንታዊ የዕደ-ጥበብ ስራዎችን ማውደሙን ያስታወሱት ባለስልጣኑ፣ ይሄም ሆኖ ግን የትኛውም አገር የግድቡን ግንባታ እንዳልተቃወመና ስራዋን ለማደናቀፍ እንዳልሞከረ ገልጸዋል፡፡
የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ካርቲም፣ ባለፈው ጥቅምት ወር ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያነሳችውን ተቃውሞ እንደተቹት የጠቀሰው ዘገባው፣ ሚኒስትሩ በተለይም የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ግድቡን በተመለከተ መሰረተ ቢስ መረጃዎችን እያናፈሱ ነው በማለት መክሰሳቸውንና የግድቡ መገንባት ሊያስከትላቸው ይችላሉ ተብለው ከሚጠቀሱ ማናቸውም አይነት ችግሮች ይልቅ፣ ጠቀሜታው እጅግ የጎላ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን አስታውሷል፡፡
ተቀማጭነቱ በአውሮፓ የሆነው ስቶክሆልም ኢንተርናሽናል ዋተር ኢንስቲትዩት የተባለ አለማቀፍ ተቋም፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት፣ ግብጽ ለደለል ቁጥጥርና በትነት ሳቢያ የሚጠፋውን ውሃ ለማስቀረት ታወጣው የነበረውን በሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያስቀርላት በመሆኑ፣ ለኢትዮጵያ ገንዘብ መክፈል ይገባታል ማለቱንም ዘገባው ጨምሮ አስታውሷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት፣ በዜጎቹ የገንዘብ መዋጮ የተጀመረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ በተያዘለት ዕቅድ መሰረት ግንባታው እየተከናወነ እንደሚገኝ፣ ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ የገንዘብ ችግር እንደማይገጥመውና በታሰበው የጥራት ደረጃና በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተሰርቶ እንደሚጠናቀቅ በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወቃል፡፡
የሮይተርስ ዘጋቢ አሮን ማሾ በበኩሉ፣ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በማከናወን ላይ የሚገኘው ግንባር ቀደሙ የጣሊያን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሳሊኒ፣ ከግንባታው ጋር የተያያዙ ክፍያዎች በሙሉ በወቅቱ እየተፈጸሙለት እንደሆነ  ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡
የኮንስትራክሽን ኩባንያው፣ የኢትዮጵያ መንግስት በቀጣይም የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገውን በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ቀሪ ገንዘብ በማሟላት ረገድ፣ ችግር ይገጥመኛል ብሎ እንደማያስብና ከፋይናንስ እጥረት ጋር በተያያዘ ምንም አይነት የሚያሰጋው ነገር እንደሌለ መናገሩን የሮይተርስ ዘገባ ጨምሮ ገልጧል፡፡ “በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጽኑ እምነት አለን፣ የገንዘብ ጉዳይ አያሰጋንም!” ብሏል ሳሊኒ ለሮይተርስ፡፡

Read 8641 times