Saturday, 26 April 2014 12:26

‘ተመሳሰል፣’ ‘ተቀላቀል’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የበዓሉ ሰሞን እንዴት አደረጋችሁሳ!
ስሙኝማ…የክትፎ ‘ግርግር’ ተጀመረ አይደል! ኮሚክ እኮ ነው…‘የተመሳሰል’ ‘የተቀላቀል’ ዘመን፡፡ ለታመመች ሚስቱ አሞክሲሊን መግዣ መሥሪያ ቤት የብድር ጥያቄ አግብቶ ከቢሮ ቢሮ የሚመላላሰው ሰው የክትፎ ቤት ‘ግርግር’ ዋና ተዋናይ ሆኖ ስታዩት ግራ አይገባችሁም!
ስሙኝማ… ይሄ “ምርታችንን አስመስለው የሚሠሩ ስላሉ...” “ተመሳሳይ ምርቶች ገበያ ውስጥ መግባታቸውን ስለደረስንበት…” ምናምን የሚሉ ማስታወቂያዎች አልበዙባችሁም! አሁን፣ አሁንማ “ተመሳስሎ ያልተሠራው የትኛው ምርት ነው?” ልንል ምንም አልቀረን! ልክ ራሱን የቻለ ‘አስመስሎ የመሥራት ኢንዱስትሪ’ የተፈጠረ ነው የሚመስለው፡፡ እኔ የምለው…ይሄ ዕቃ አስመስሎ የሚያትመው ‘3ዲ’ ማተሚያ ገባ እንዴ!
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የመመሳሰል ነገር ካነሳን አይቀር የባሰበት ደግሞ የሰዉ ‘ተመሳስሎ መሠራት!’ እናላችሁ… ‘ተመሳስለን የተሠራን’….በዝተናል!
ታዲያላችሁ….ዘንድሮ ተመሳስለው የተሠሩ ‘ቦተሊካ—ተኮሮች’ ብዛት ግርም የሚላችሁ ነው። ልክ ነዋ… ‘ቦተሊካ—ተኮር’ መሆን በተዘዋዋሪ “እዩኝ፣ ከእናንተው ጋር ነኝ…” አይነት ማመልከቻ ማስገባት ነዋ! ዘንድሮ የ‘ሥራ ችሎታ’ን ከማሳየት ይልቅ ‘ታማኝነትን ማሳየት’ አቋራጭ መንገድ እየሆነ ነው ስለሚባል ራሳችንን ‘አመሳስለን እየሠራን’ ያለን መአት ነን፡፡
እናላችሁ…የአለቆቻችንን ንግግሮች እንዳለ…አለ አይደል… ከእነማስነጠሱ ጨምረን የምንደግም ‘ተመሳስለን የተሠራን’ መአት ነን፡፡ ምክንያቱም ማስመሰል የታማኝነት ማሳያ ሆኗላ! “እየተከናወኑ ያሉ ሁለንተናዊ የዴሞክራሲ፣ የፍትህና መልካም አስተዳዳር እንቅስቃሴዎች አጠናከሮ ለማስቀጠል…” ምናምን አይነት በሚል በተመሳሳይ ማሸጊያዎች የተጠቀለልን ተመሳስለን የተሠራን ‘ቦተሊካ—ተኮሮች’ እየበዛን ነን፡፡
ስሙኝማ… በተለይ ይሄ ዘመን ያመጣው የፖለቲካ ‘ቋንቋ’ መጠቀም ተመሳስሎ የመሠራት ዋና መለያ ሆኗል፡፡ ገና ለገና የእሱ መሥሪያ ቤት ሁለት ተጨማሪ ኮምፒዩተሮች ስለገዛ “ታማኝ ነኝ” ለማለት “መንግሥታችን በሚያካሂደው ያልተቆጠበ የልማትና ዕድገት…” ምናምን የሚል ተመሳስሎ የተሠራ አትርሱኝ ባይ አለቃ ሞልቶላችኋል፡፡
ሠላሳ ተጨማሪ ሠራተኛ ለሚያስፈለገው መሥሪያ ቤት ሦስት የሥራ ማስታወቂያ ብቻ ስላወጣ… አለ አይደል… “መንግሥት ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ጋር ለማሰለፍ በሚያደርገው ያለሰለሰ ጥረት፣ የሥራ ሀይላችንን በማጠናከር ለልማቱ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እያደረግን ነው…” ምናምን አይነት ተመሳስሎ መሠራት ሞልቶላችኋል፡፡
ደግሞላችሁ…ተመሳስለው የተሠሩ የስኑፒ ዶግ፣ ፊፍቲ ሴንት ምናምን ቀሺም ‘ፎቶ ኮፒዎች’ ግልባጮች አሉላችሁ፡፡ በአንቺ ሆዬ ቅኝት ቅልጥ ያለ የራፕ ምት በማስገባት ራስን ‘ከአማሪካን ዘፋኞች’ አመሳስሎ የመሠራት ነገር ሞልቶላችኋል፡፡ ስሙኝማ… በራፕ ስልት የሚያስገቧቸው እንግሊዘኛ ‘ግጥሞች’ የሚሉት ተሰምቷችሁ ያውቃል! የምር… እኔ እንግሊዝኛ ቋንቋን እንዲህ ‘ዋጥ ማድረግ’ የሚቻል አይመስለኝም ነበር! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ተመሳስለን የተሠራን ‘አገር ወዳዶች’ ደግሞ ሞልተንላችኋል፡፡ አለ አይደል… የ‘አደባባይ’ አገር ወዳድነታችን የሚኖረው ጓዳችን እስከሞላ…ቦርሳችን እስከሞላ…ካዝናችን እስከሞላ ድረስ የሆንን ተመሳስለን የተሠራን ‘ፓትሪዮቶች’ አለንላችሁ፡፡ አገር መውደድ ማለት …‘እንደ ሰዉ’ የሀገር ልብስ መልበስ…‘እንደ ሰዉ’ አዳራሽ በባንዲራ ማድመቅ… በኳስ ስናሸነፍ መጨፈር፣ ስንሽንፍ ማኩረፍ …የሚመስለን የዘመኑ የ‘ተመሳሰል’ና ‘ተቀላቀል’ ጨዋታ ህጎች ‘የገቡን’ ሞልተናል፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የአገር ወዳድነት ነገር ካነሳን አይቀር የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ። ያለፈው ቅዳሜ በወጣው የ‘ፋክት’ መጽሔት እትም ላይ ሌፍተናንት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ያሉት ደስ አይልም! ስለ አሸፋፈታቸው ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ… “ጥይቱን በራስዎ ገንዘብ ገዝተው ነው የሚዋጉት?” ብሎ ሲጠየቃቸው…“በራሴ ገንዘብ ነው እንጂ! ሀገር አይደለችም እንዴ ታማ የተኛችው! እናት አይደለችም ሀገር! እናትህ ታማ መድኃኒት ግዛላት ስትባል ገንዘብ ስጪኝ ትላታለህ?” ብለው ነው የመለሱለት፡፡
እናማ…እንዲህ አይነቱ ሀገር ወዳድነት ነው የናፈቀን! እንዲህ አይነቱ ሀገር ወዳድነት መዳከሙ ነው ሀገርን ታማ ከምታቃስትበት አልጋ ላይ ቀና የሚያደርጋት፡፡
እናማ…“ሀገር አይደለችም እንዴ ታማ የተኛችው?” ብሎ የሚቆጭ ትውልድ ያብዛልንማ!
ደግሞላችሁ…በ15 ዓመታቸው አርበኝነት የመግባታቸውን ምክንያት ሲጠየቁ ምን ቢሉ ጥሩ ነው…“አሀ! እኔ በቁሜ እያለሁ ጣሊያን ሀገሪቱን ቅኝ ሲያደርጋት ዝም ብዬ ማየት አለብኝ?” ነው ያሉት፡፡
አንድዬ እንዲህ አይነት የሀገር ጥቃት ማየት የማይፈልጉ ዜጎችን በብዙ እጥፍ ይፍጠርልንማ!
ስሙኝማ…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…የጥንቷን ‘ጥልያን’ አይነት ሌላ ባላጋራ ቢመጣ…አለ አይደል…እንኳን ሁላችን ‘መጠቃቱ ሊያንገበግበን’ ቀርቶ…‘ዕንቁላል ለመሸጥ’ የሚደረገው ግፊያ በሪዮ ካርኒቫል የሚገኘውን ህዝብ በብዙ እጥፍ ብዛት የሚበልጥ ይመስለኛል፡፡ ዘንድሮም ቢሆን ዘዴው ይለዋወጥ እንጂ…‘ዕንቁላል እየተሸጠ’ እንደሆነ “ጠርጥር፣ ከገንፎ ውስጥ አለ ስንጥር…” አይነት ነገር የሚያስብሉ ነገሮች አሉላችሁ፡፡
እናላችሁ…ከተጨዋወትን አይቀር…
ለሰማው ዕፁብ ነው ላየውም ይደንቃል
እንዴት አንድ አገር ሰው በማበል ያልቃል
የምትል የጥንት ስንኝ አለች፡፡ ‘ተመሳስሎ መሠራት’…አለ አይደል…ማበልም ነው፣ ማዕበልም ነው፡፡ ‘አባዮች’ ሆነን በማዕበል ከመወሰድ ያትርፈንማ!
ደግሞላችሁ…ተመሳስለን የተሠራን…‘የፈረንጅ አፍ የሚቀናን’ አለንላችሁ— አለ አይደል…የቋንቋ ችሎታችን… ዝቅ ሲል ከ“ዋው!” ከፍ ሲል ከ“ኢንተረስቲንግ ነኝ” የማያልፍ፡፡ (ስሙኝማ…እግረ መንገዴን… ለፈረንጆቹ እንዲቀርብልን የምንፈልገው ሀሳብ አለን.. “ዋው!” የሚሏት ቃል የ‘ፈረንጅ አፍ’ ጆከር ትባልልንማ! ልክ ነዋ…“ዋው!” ያልገባችበት ነገር አለ እንዴ! “ዋው!” የማይል ቢኖር የቡቲክ አሻንጉሊቶች ብቻ ይመስሉኛል፡፡ እንደውም ቦሶቻችን “ዋው!” የምትለውን ቃለ መጠቀም ከጀመሩ፣ ምን አለፋችሁ፣ ወደ መካካለኛ ገቢ መጠጋታችንን ልንጠረጥር እንችላላን፡፡ ቂ..ቂ…ቂ…)
ታዲያላችሁ…ተመሳስለው የተሠሩ…በመሥሪያ ቤታቸው ፍቅር ብን ያሉ አሉላችሁ፡፡ ስብሰባ ላይ ዋና ‘ሀሳብ’ አቅራቢዎች (‘ሀሳባቸው’… “መንግሥት ዲሞክራሲ ስላጎናጸፈን ምስጋና ይግባውና… ምናምን ከማለት ባያልፍም) የሆነ ዝግጅት ሲኖር ዋና አፋሽ፣ አጎንባሽ የሚሆኑ…ከአእምሯቸው ይልቅ ጆሮዎቻቸው ሥራ የሚበዛባቸው…ተመሳስለው የተሠሩ ሞልተውላችኋል፡፡
እናማ…ተመሳስሎ የመሠራት ችግር በተለያዩ ምርቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በእኛም ላይ ነው። እናማ…“በእኔ አምሳል ተመሳስለው የተሠሩ ሰዎች መኖራቸውን ስለደረስኩበት ወዳጆቼ እንዳትታለሉ…” ምናምን አይነት ማስታወቂያዎች የምንሰማበት ጊዜ አይመጣም አይባልም፡፡ ሀገሯ ‘ጦቢያችን’ ነቻ!
ስሙኝማ…ከፍ ብለን በጠቀስነው ቃለ መጠይቅ ላይ ሌፍተናት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ያሏት አንድ ግሩም ነገር አለች…“እንኳንም የሀገሬን ውለታ የበላሁ እኔ አልሆንኩ፣” ነው ያሉት፡፡ በዚህ ዘመን ስንቶቻችን ነን እንዲህ ማለት የምንችለው?
ሀገሬ ጥሪኝ፣ ሀገሬ ጥሪኝ
እመጣልሻለሁ መቼም በራሪ ነኝ፣
እመጣለሁና ቀኑ ቢሞላልኝ
ሀገሬን አደራ ሀገሬን አቆዩኝ፣
…………
ልቤን ሀሳብ ገብቶት፣ እየሰረሰረው
አትስጡብኝ አለ አገሬንም ለሰው፡፡
ተመሳስሎ በመሠራት ሳይሆን በእውነተኛ ንጹህ ስሜት እንዲህ አይነቶቹን ዜማዎች ደጋግመን የምናዜምበትን ጊዜ ያቅርብልንማ! የ‘ተመሳሰል፣’ ‘ተቀላቀል’… ዘመን ዕድሜ አይርዘምብንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2070 times