Saturday, 26 April 2014 12:47

ልብ ድካምና ወሲባዊ ግንኙነት

Written by  አበበ ተሻገር abepsy@yahoo.com
Rate this item
(7 votes)

     ይቅርታ አንባብያን፡፡ የልብ ድካም ያለባቸው ሰዎች በተለይ ከፍቅር ጓደኞቻቸው ወይም ከትዳር አጋራቸው ሰርቀው ወሲባዊ ግንኙነት በሚፈፅሙበት ጊዜ የደም ብዛት አይሎ የልብ ምትም ፈጥኖ ህይወታቸው ያለፈበት አጋጣሚዎች ተመዝግበዋል፡፡ እስኪ የግለሰቦችን ታሪክ መነሻ እናድርግ ምናልባት የጉዳዩ አሳሳቢነት ወደኛ ቀርቦ ከታዬን፣
“ትውውቃችን ሁለት ዓመታት አስቆጥሮአል፣ ትላለች ወጣቷ ችግሯን ለመግለፅ ስትጀምር በእነዚህ ጊዚያት ውስጥ በቻልነው አጋጣሚና ባገኘነው ትርፍ ጊዜ እንገናኛለን፣ እንዋደዳለን፣ እንነፋፈቃለን፣ .  .  . ከእርሱ ጋር በማሳልፋቸው ጊዜያቶች ደስተኛ ነኝ፡፡ ሆኖም ሁኔታዎች ፈቅደው ወሲባዊ ግንኙነት ለመፈፀም ስናስብ ጓደኛዬ በጣም ይፈራል፣ ስሜቱ አይነሳሳም፣ ወሲባዊ ግንኙነት ከመፈፀም ይልቅ ከእኔ ጋር በሌሎች ጉዳዮች ጊዜ ማሳለፉን ይመርጣል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም ያለፉትን ስድስት ወራት አሳለፍን፡፡ ጓደኛዬ ከእኔ በፊት ከሴቶች ጋር በጓደኝነት ከስድስት ወራት በላይ ባለበት ችግር ምክንያት አብሮ መቆየት አልቻለም፡፡ አሁን አሁን ስሜቴ እየቀዘቀዘ እያስፈራኝ መጣ . . .”
ሌላኛዋ ደግሞ ጓደኛዋ ራሱን ስቶ እርቃኑን መሬት ላይ ሲዘረገፍባት ላዩ ላይ ውሃ  ደፍታ፣ መስኮት በመክፈት አየር እንዲገባ በማድረግ የሆነውን ሁሉ ከሆነ በኋላ ለመረዳት እንደቻለች አስታውሳለች፡፡ በፀና የጓደኝነታቸው ወቅት ምንም እንኳን ከአደጋው በፊት ግንኙነት ቢኖራቸውም ይህ ክስተት ግን የመጀመሪያ እንደነበረና ከዚያ በኋላ እንደገና ወደ ግንኙነት ለመግባት ስጋት ውስጥ እንደወደቀ ትገልፃለች፡፡
ሰዎች ከተግባሩ በኋላ የሚያገኙት ውጤት ይለያይ እንጂ በአካላዊ እንቅስቃሴ (ስፖርት) እና በወሲባዊ ግንኙነት ወቅት የልብ ምት ፍጥነትና የደም ግፊት ይጨምራል፡፡ ለማነፃፀር ያህል በሰዓት ከሶስት እስከ ስድስት ኪሎ ሜትር ሜዳ ላይ (ዳገትና ቁልቁለት ወይም ጭቃ በሌለበትና ወጣ ገባ ባልበዛበት መንገድ) በፍጥነት የሚራመድ ሰው ወይም 20 የፎቅ መወጣጫ ደረጃዎችን በአስር ሰከንድ የሚወጣ ሰውና አንዴ ወሲባዊ ግንኙነት የሚፈፅም  ሰው የልብ ምታቸውና የደም ግፊታቸው በእኩል ይጨምራል፡፡ ያም ሆኖ ግን ሁለቱ ሰዎች የሚገኙበት እድሜ፣ የሰውነት ክብደት፣ ያለባቸው ሱሶች (ለምሳሌ አጫሾች)፣ ከተግባሩ በፊት የተመገቡት ምግብና የወሰዱት መጠጥ  ወዘተ ሁኔታውን ሊለውጡት ይችላሉ፡፡
ወሲባዊ ግንኑነት የሁለቱን ተቃራኒ ፆታ የግንኙነት ጥልቀትና ጥብቅ መሆን የሚያመላክት ተግባር (ከሴተኛ አዳሪዎ ጋር የሚደረግ ግንኙነትስ?) ሲሆን ጤናማና የተሳካ ህይወት ለመምራትም ወሲባዊ ግንኑነት የራሱ ድርሻ አለው፡፡ አካልም መንፈስም የሚጠይቁት ጥያቄ አለ፡፡ ይህም ጤናማ ፍላጎት ነው፡፡ ማንኛውም ሰው መጠጣትና መብላት እንደሚፈልገው ሁሉ በተመሳሳይ አካልና አእምሮም ወሲብ የመፈፀም ፍላጎት ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በእርግጥ ማንኛውም ሰው ይብዛም ይነስም፣ ጥራት ይኑረውም አይኑረውም .  .  .  ሳይበላና ሳይጠጣ መኖር አይቻለውም (ከተቻለም ከስድስት ሳምንታት ላልበለጠ ጊዜ ብቻ ነው መዝለቅ የሚችለው ከዚያ በኋላ በህክምና መሞት ይጀምራል፣ ውሃን በተመለከተ ደግሞ ከሶስተ ቀናት እስከ አምስት ቀናት መቆዬት ይቻላል)፡፡ የወሲባዊ ግንኑነት ፍላጎትን ግን ለእድሜ ልክ ማቀብ ይቻላል፡፡ ሆኖም ይህ ለአብዛኞች የማይቻልና ህይወትንም ምልዑ ሊያደርግ የማይችል እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚያስፈልገው ጉዳይ ህይዎት ላይ ለህይዎት እጅግ አስፈላጊ የሚባሉ ዋና ዋና ጉዳዮች በርካታ ሊሆኑ ይችላሉ ይህም ከሰው ሰው ይለያያል፡፡ ለአንዱ አስፈላጊ የሚባለው ለሌላው ያንያህል ትርጉም የሚወስድ ላይሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ከፍላጎቱ ባሻገር ራስን መተካት ቤተሰብ ማፍራት በዚህም ደስታን መጨመር ብዙ ሰው ይፈልጋል፡፡
ከእነዚህ ምክንያቶች በመነጨ ታዲያ የልብ ህሙማንም ይኸው ፍላጎትና ስሜት ይኖራቸዋል፡፡ ሆኖም እንደማንኛውም የስፖርት እንቅስቃሴ ወሲባዊ ግንኑነትም የሰውነትን የልብ ምት ፍጥነትና የደም ግፊት ስለሚጨምር ግለሰቦቹ (ወንዶችም ሆኑ ሴቶች) አደጋ ላይ ሊወድቁ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ይከሰታሉ፡፡ አንዳንድ የትዳር አጋሮች ወይም የፍቅር ጓደኞች እንዲህ ያለ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ቶሎ ሊርቁ ወይም ሊለዩ ይችላሉ፤ ሌሎች ደግሞ ችግሩን በውስጣቸው አምቀው ለብቻቸው እየተብሰለሰሉ መለየትም አለመለየትም መሃከል ሆነው ይመሻል ይነጋል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን መፍትሄ የሌለው ችግር አይደለም፡፡ በእርግጥ እርዳታ ወደሚገኝበት ማቅናት ያልቻሉ ሰዎች ድንገት ህይወታቸው በተቃራኒ ፆታ ጓደኞቻቸው እቅፍ ውስጥ ዝም ያሉ ተገኝተዋል፡፡ አንዳንድ ጥናቶች ግለሰቦቹ ከሞቱ በኋላ አስክሬናቸው ሲመረመር ለሞታቸው ምክንያት የልብ ድካሙና የደም ግፊቱ እንደሆነ ተመዝግቧል፡፡ ከዚህ በመለስ ግን ድንገት ራሳቸውን ስተው የሚወድቁ ግን ለከፋ አደጋ የማይዳረጉ አብዛኛውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡
እንግዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ያለፉ ሰዎች ደግሞ ድጋሜ ወደ ወሲባዊ ግንኙነት ለመግባት ይቸገራሉ፡፡ ይፈራሉ፣ ጭንቀትና ድብርት ውስጥ ይገባሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ስሜታቸው ይቀዘቅዛል (ይሞታል) አንዳንዴ ስንፈተ ወሲብ እስኪመስል  ይቀዘቅዛሉ፡፡ ይህ ክስተት ደግሞ ከሴቶች ይልቅ በወንዶች ላይ ይጎላል፡፡ ይበዛል፡፡ ልብ ድካም ያለባቸው ሰዎች በተለይ በስርቆት በሚፈፅሙበት ወሲባዊ ተራክቦ ምክንያት ብዙዎች ለአደጋ ይጋለጣሉ፡፡ በመጀመሪያ በስርዎቱ ምክንያት ጭንቀት ውስጥ ይገባሉ ይህ ለልብ ምቱ ፍጥነት አስተዋፅዎ ያደርጋል፣ በሌላ በኩል በግንኙነቱ ምክንያት የልብ ምት ያይላል፣ የደም ግፊት ይጨምራል፡፡ በዚህ ምክንያት አደጋው ይሰፋል፡፡
በአካል እንቅስቃሴ የደም ግፊትና የልብ ምት ፍጥነትን ይጨምራሉ ብለናል፡፡ በዚህም በተለይ አካላዊ እቅስቃሴው ወሲባዊ ግንኙነትን የተመለከተ ከሆነ ግለሰቦች ለአደጋ ይጋለጣሉ ይባል እንጂ መፍትሄውም የሚወለደው እዚሁ ላይ ነው፡፡ እንቅስቃሴውን ከማድረግና ከመለማመድ፡፡ ብዙዎች ወደ ወደ ጤና ባለሞያዎች ከቀረቡ በኋላ ጤናማ የሆነ የወሲብ ህይወት (በዚህም ጤናማ የሆነ ትዳር) መምራት ችለዋል፡፡ በስነ ልቦና አማካሪዎቹ በኩልም በቃል ከሚሰጥ ሃሳብ ይልቅ በፁሁፍ የሚሰጣቸው የበለጠውን ውጤት አስገኝቷል፡፡ ይኽም የግለሰቦቹን ሁለንተናዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የሚቀርብ ነው፡፡
እንዲህ ያለ ችግር ያለባቸው ሰዎች መፍራት ያለባቸው ጉዳዩን አፍነው የሚይዙ ከሆነ ነው፡፡ በተረፈ ከፆታ ጓደኞቻቸው ጋር ፆታዊ ጉዳዮችን ማንሳትና መወያየት፣ ስለ ወሲባዊ ግንኙነታቸው በግልፅ ማውጋት፣ ግንኙነታቸውን ስለሚያውኩ ጉዳዮች ማንሳትና ያሉትን ችግሮች እንዴት መቅረፍ እንደሚችሉ ስልት ማበጀት፣ ከወሲባዊ ግንኙነት በፊት ከዚሁ ጋር የተያያዙ ወሬዎች ድርጊቶችን ለመፈፀም ግልፅ መሆን፣. . .፡፡ ከወሲባዊ ግንኙነት በፊት ከባድ ምግብ መመገብና አልኮል መጠጣትን ማስወገድ፣ የትንባሆ(ሲጋራ) ሱስ ካለ ማቆም ምንም አማራጭ የለውም (ማቆም የመፃፉን ያህ ቀላል ባይሆንም እንዴት ማቆም እንደሚችሉ የጤና ባሙያዎችን መጠጋቱ ወደ መፍትሄው ያደርሳል) ከዚህም ውጭ በግል ለባለ ጉዳዮቹ የሚቀርቡ መጠይቆችና ሃሳቦች ይኖራሉ (እነዚህን እውነቶች እንድፅፍፍ ሞያዬ ቢያስገድደኝም ባህል ይገድበኛል ሆኖም ችግሩ ያለበት ሰው በግል መረጃውን ቢፈልግ መደወል አቋራጩ ነው)፡፡ የፆታ ግንኙነት ምክር (sexual counseling) በዚህ ችግር ውስጥ ላሉ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ፍርሃትን ለማስወገድ፣ ፍላጎትን ወደነበረበት ደረጃ ለመመለስ፣ በዚህም የሚፈልጉትን ስሜት (ፍላጎት) እንዲያገኙ በጋራ ዘዴ ይቀየሳል፡፡ በጥቅሉም ጤናማ የሆነ ወሲባዊ ህይወትና ትዳር ይኖራቸዋል፣ በዚህም በሚፈልጉትን ደስታ እንዲያገኙ ያግዛል፡፡
ይህ ፅሁፍ መሰረት ያደረገው የተለያዩ ጥናቶችን መሆኑን ልጠቁም፡፡ ሳምንት እንገናኝ!

Read 10505 times