Saturday, 26 April 2014 12:49

“ኢትዮ-ኤርትራ የቀን ግርዶሽ” መጽሐፍ በኔ እይታ

Written by  ዳንኤል ዘነበ (ከገርጂ)
Rate this item
(1 Vote)

           በሚያዝያ ወር 2006 ዓ.ም መግቢያ ላይ በመዲናችን አንድ መጽሐፍ ለምረቃ በቅቶ ነበር፡፡ ቦታው በብሄራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍ አዳራሽ ውስጥ ነበር፡፡  የመጽሐፉ ርዕስ “ኢትዮ-ኤርትራ የቀን ግርዶሽ” የሚል ነው፡፡ በመጽሐፉ ምረቃ ላይ ለመገኘት የቻልኩት በአንድ ጓደኛዬ ጥቆማ መሰረት ነበር፡፡ የመጽሐፉ ጸሐፊ ተስፉ (ኢትዮጵያ) አልታሰብ ማንነት፤ በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ ኤርትራ ተወልዶ ያደገ መሆኑ ተነግሯል፡፡ በስሙ መካከል የገባው “ኢትዮጵያ” የሚለው ስም የእናቱ ነው፡፡ “ለምን የእናትህን ስም ከአባትህ አስቀደምክ?” ሲባል “የሴት ልጅ መባል በሀገራችን እንደ ስድብ ስለሚታይ በእናት መጠራት ውርደት ሳይሆን ክብር መሆኑን ለማሳየት ነው” ብሏል፡፡  
ጸሐፊው ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በ1983 ዓ.ም ሲሆን፤ ከኤርትራ አወጣጡን በግፍ እንደነበር በመጽሐፉ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ፀሐፊው በወቅቱ በሻእብያ መንግስት ካደገበት ከአስመራ በግዳጅ መውጣቱን ይናገራል፡፡ ነገር ግን ይህን የግፍ ድርጊት የፈፀመው የሻእብያ መንግስት እንጂ የኤርትራ ሕዝብ አለመሆኑን በመጽሐፉ ላይ ምስክርነቱን አስቀምጧል፡፡ ከዚህም ባለፈ የማባረሩን ድርጊት የፈጸሙት የሻእብያ መሪዎች፣ ዛሬ በሰሩት ስህተት ተምረውበት ይሆናል በማለት ይቅር ልንላቸው ይገባል፤ በማለት ስለ ይቅር ባይነትና ቂምን መያዝ አስፈላጊ አለመሆን በመፅሀፉ ይነግረናል፡፡ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የነበረው ጸሐፊው፣ ድርጊቱን የፈፀሙት በጣት የሚቆጠሩ የሻእብያ መሪዎች መሆናቸውን ይናገራል፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከኤርትራ እንዴት እንደተባረሩ ለማናውቀው ዜጎች እውነታውን ለማሳየትና በኤርትራ ሕዝብ ላይ ምንም አይነት ቂም እንዳንይዝ በማስረጃ እያጣቀሰ፣ በጉዳዩ ላይ እውነታውን እንድናውቅና ከኤርትራ ህዝብ ጋር በፍቅር መኖር እንደሚገባን በስፋት ይነግረናል፡፡   
ከዚህ ቀደም የሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ግንኙነት የደም፣ የስጋ፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የልማድና የሥነ-ልቦና ትስስር እንዴት እንደነበረ ኤርትራ በኖረባቸው ሃያ ዓመታት ያየውን፤የሰማውንና ያነበበውን እውነታ በመጽሐፉ አስቀምጧል፡፡ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ስለ ሁለቱ ሕዝቦች ፍቅርና አንድነት የሚተርክልን መጽሃፉ፤ ወደፊት ይህን የሁለቱ ህዝቦች ፍቅርና አንድነት እንዴት ማስቀጠል እንደሚቻል መፍትሄዎችን ይጠቁማል፡፡
ዛሬ ግን በሀገራችን ያሉ የክልል ባለስልጣናት የሚሰሩትን ስራ ስንመለከት በግልፅ የምናየው ቂምና በቀልን ለቀጣይ ትውልድ የማውረስ ክፋት ተግባር ላይ ያተኮረ ሀውልት የመገንባት ተግባር ሲከናወን ነው፡፡ የቀደሙት አባቶቻችን ለኛ ትተውልን ያለፉት ስራ የፋሲል ግንብ፤ የላሊበላንና የአክሱምን ድንቅ ጥበብ  ስራቸው እንጂ የቂም ሀውልት አልነበረም፡፡ እኛ ግን የነሱን ያህል ድንቅ የጥበብ ስራ መስራት ሲያቅተን፣ የቂምና የጥላቻ ሀውልት አውራሽ ሆነን ተገኘን፡፡ በቃ እኛ ልጆቻቸው የመጨረሻው ችሎታችንና፣ እውቀታችን እንዲህ ሆነ ቀረ? እስኪ ስለ እውነት እንነጋገር ከተባለ፣ የኦሮሞ ህዝብ ዛሬ የቂም ሀውልት ነው የሚያስፈልገው ወይስ መሰረተ ልማት? የኦሮሞ ህዝብ የውሃ፤የጤና፤የመንገድ፤የመብራትና ዘመናዊ የግብርና ግብአት እንደሚያስፈልገው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የኛዎቹ የዛሬዎቹ መሪዎቻችን አሩሲ በ20% ሚልዮን ብር የቂም ማውረሻ ሀውልት ለአሩሲ ህዝብ በገፀ በረከትነት አቀረቡለት፡፡ የአሩሲ ህዝብ በዛሬዎቹ መሪዎቻችን ድርጊት እንዳፈረ ምንም አልጠራጠርም፡፡ የአሩሲ ህዝብ በድህነት ውስጥ እየኖረ በሃያ ሚሊዮን ብር የቂም ሀውልት ማውረስ ምን የሚሉት የአስተዳደር ስርአት ነው፡፡  
“የኢትዮ-ኤርትራ የቀን ግርዶሽ” መጽሐፍ ጸሐፊ ስለፍቅርና አንድነት ለማስተማር ድንበር ተሻግሮ ከዚህ ቀደም ከተለዩን የኤርትራ ሕዝቦች ጋር እንደገና ወደ ነበርንበት ሰላምና ፍቅር እንድንመለስ ለማድረግ የፃፈውን ፅሁፍ ስመለከት፤የታዘብኩት ነገር ቢኖር በተራው ዜጋና በመሪዎቻችን መካከል ሰፊ የአመለካከት መራራቅ መኖሩን ነው፡፡
በመጽሐፉ ምረቃ ዕለት ከመድረኩ ጀርባ ተለጥፎ የነበረው ጥቅስ እስካሁን ድረስ በልቤ ውስጥ ተሰንቅሮ ቀርቷል፡፡  ጥቅሱ የሚለው “ከወረስነው ቂም ይልቅ የምናወርሰው ፍቅር ይበልጣል” የሚል ነበር፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝቦች ከወረሱት ጊዜያዊ ቂም ይልቅ የሚያወርሱት ፍቅር እንደሚበልጥ መሪዎቻችን አለማወቃቸው ያሳዝናል፡፡
የእኔ አባትና እናቴ የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው፡፡ እኔ የተወለድኩት አዲስ አበባ ነው፡፡ ነገር ግን እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ በአሩሲ በተሰራው የአኖሌ ሀውልት አፍረናል፡፡ አንገታችንም እንድንደፋ አድርጎናል፡፡
“የኢትዮ-ኤርትራ የቀን ግርዶሽ” መጽሐፍ ጸሐፊ እንደ ቼ ጉቬራ ከአገሩ ተሻግሮ ከሃያ ዓመታት በፊት የተለዩንንና ከ15 ዓመታት በፊት በአስከፊ ጦርነት ውስጥ ገብተን ከነበሩት የኤርትራ ሕዝቦች ጋር የእርስ በርስ ግንኙነታችን እንደገና ወደ ነበረበት ለመመለስና “ኖርማላይዜሽን” ለመፍጠር ያደረገው ጥረት ከልብ አስደስቶኛል፡፡
በግሌ፤ “የኢትዮ-ኤርትራ የቀን ግርዶሽ” መጽሐፍ ድንበርና ዘመን ተሻጋሪ ከመሆኑ በላይ ገዢዎቻችን መጽሐፉን አንብበው ቂም ከማውረስ ይልቅ ፍቅር ማውረስ የበለጠ እንደሆነ ሊያስተምር የሚችል በመሆኑ፣ እንዲያነቡት በዚህ አጋጣሚ በትህትና እጋብዛለሁ፡፡ የመጽሐፉ ጸሐፊ ለኔ የፍቅር፤የሰላምና የአንድነት ሰባኪ ታጋይ ከመሆኑ በላይ የዘነጋናቸውን የኤርትራ ሕዝቦችን ለማቀራረብ ጥረት በማድረጉ ሊመሰገን ይገባል፡፡ እንደዚህ አይነት ጸሐፊዎች ይብዙልን፤ ይበርክቱልን እላለሁ፡፡

Read 2517 times