Saturday, 03 May 2014 12:32

የጋዜጠኞች ማህበራት አይጥና ድመት መሆን

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

           ከአምስት ወር በፊት ነበር “የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” የተሰኘ አዲስ የጋዜጠኞች ማህበር የመመስረት እንቅስቃሴ የተጀመረው፡፡ በምስረታው ሂደት ግን ከነባሮቹ የጋዜጠኞች ማህበራት ጋር አይጥና ድመት ሆኖ ቆይቷል፡፡ የማህበሩ ስያሜ ለውዝግብ መነሻ በመሆን ተጠቅሷል፡፡ በዚህ ብቻ ግን አላበቃም፡፡ ነባሮቹ ማህበራት “የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በአመራር ደረጃ ተቀምጠዋል ሲሉ መተቸት ያዙ፡፡ በውጭ ኃይሎች ይደገፋል ሲሉም የወነጀሉ ቢሆንም በተጨባጭ ማስረጃ ማሳየት ግን አልቻሉም፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፤ አሁን እየተወገዙ ካሉት ዓለም አቀፍ የመብት ተቋማት መካከል ብዙዎቹ ከተለያዩ ማህበራትና ከመንግስት ጋር ሲሰሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የማህበራት ምዝገባ ኤጀንሲ ለአዲሱ ማህበር ዕውቅና እንደማይሰጥ ያስታወቀው ባለፈው ሳምንት ሲሆን “የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” በሚል ተመሳሳይ ስም የተመሰረተ ማህበር እንዳለ ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡
የማህበሩ ሊቀመንበር ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ እንደ ማህበር እውቅና እስከሚሰጠን ድረስ ተግባራችንን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የማህበሩ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በበኩላቸው፤ ጉዳዩን ለቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ ነባሮቹ የጋዜጠኞች ማህበራት አዲሱ ማህበር ዕውቅና ለማግኘቱ እምብዛም የተከፉ አይመስሉም፡፡
“የማህበራትን መቋቋም እናበረታታለን ድጋፍም እናደርጋለን” ያሉት የኢብጋህ ሊቀመንበር አቶ አንተነህ አብርሃም፤ እውቅና የተከለከለው ማህበር ግን ለመቋቋም ሲሞክር ነባር ማህበራትን “የመንግስት አሽከሮች፣ ተለጣፊዎች በሚል ውግዘትና ስድብ መጀመሩን በበጎ አላየነውም ብለዋል፡፡ ቀደምት ማህበራትን አውግዘው መነሳታቸውም የእነሱን መቋቋም እንደ ስጋት እንድናየው አስገድዶናል የሚሉት ሊቀመንበሩ፤ “ማህበሩ በውጭ ሃይሎች ገንዘብ እየተደገፈ ነው” ለሚለው መከራከሪያችን ማስረጃ አለን ብለዋል፡፡ ማንነታቸውን አሁን መግለፅ ከማንፈልጋቸው የውጭ ተቋማት “ምርጫ መጥቷል፤ በዚህ ምርጫ ይሄን ስርአት ካልጣልነው ሌላ ምርጫ የለንም፤ ትብብር አድርጉልን” ተብለን ተጠይቀን ነበር የሚሉት አቶ አንተነህ፤ እኛ ይሄን ባናደርግ ሌላ ማህበር እንደሚያቋቁሙ፣ ለጋዜጦች ገንዘብ እየሰጡ እኛን የሚያብጠለጥሉ ፅሁፎችን እንደሚያፅፉ፣ ከዚያም እኛም እንደምንጠፋና የመንግስት ስርአትም እንደሚቀየር ነግረውናል፤ እንደተባለውም ከሁለት ሳምንት በኋላ ማህበር ተቋቋመ፤ በሂደትም ለእኛ የተነገሩን ነገሮች መፈፀም ጀመሩ ብለዋል፡፡ ይህን መረጃ በመንተራስ አስቀድመን ጋዜጠኞች እንዲጠነቀቁ ተናግረናል ያሉት ሊቀመንበሩ፤ “የበግ ለምድ ለብሰው ከመጡ ተኩላዎች ተጠንቀቁ ማለት ውንጀላ አይደለም” ብለዋል፡፡
ማህበሩ፤ “አርቲክል 19” ከተባለ የውጭ ድርጅት ጋር በመመሣጠር አባላቱን ለማሰልጠን ተንቀሳቅሷል የሚሉት አቶ አንተነህ፤ በኢትዮጵያ ህግ “አርቲክል 19” አገር ውስጥ ውስጥ መንቀሳቀስ አይችልም፣ በውጭ ዜጋ ገንዘብና ድገፍ የሚካሄድ የመብት ማስከበር እንቅስቃሴ በህግ የተከለከለ ነው ብለዋል፡፡ ተቋሙ የተለያዩ የስለላ ስራዎች እንደሚሰራ፣ የተለያዩ የአመፅና ህገ ወጥ ተግባራትን እንደሚያነሳሳ ስኖውደን (የሲአይኤ አባል የነበረው ግለሰብ) ማጋለጡን የጠቆሙት አቶ አንተነህ፤ አዲስ ለሚመሰረተው ማህበር አባላት “ሴፍቲ” እና “ሴኩሪቲ” ጉዳይ ላይ ድብቅ ስልጠና መስጠቱ ተገቢ አይደለም ባይ ናቸው፡፡ አሁን እያንዳንዱ ምን እንደሚሰራ በሚገባ ይታወቃል” ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ “ማንም የፈለገውን ይበል፣ ከዚህ በኋላም ስለ ማህበሩም ሆነ ስለሌሎች የውጭ ተቋማት ለአባሎቻችን ግንዛቤ በመስጠት ግዴታችንን እንወጣለን” ብለዋል፡፡
የኢጋማ ሊቀመንበር አቶ መሰረት አታላይ በበኩላቸው፤ አዲስ ማህበር ማቋቋማቸው ላይ ምንም ተቃውሞ የለንም፤ ነገር ግን እኛን አውግዘው መነሳታቸው ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ ለወደፊትም ቢሆን አፍራሽ ተልእኮ ላይ የተሰማራ ጋዜጠኛ እና ማህበር አንፈልግም ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ከዚህ በኋላ ከማህበሩ ጋር በተያያዘ መግለጫና ማብራሪያ ለመስጠት እንቸገራለን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ወንደወሰን መኮንንም፤ አዲሱ ማህበር ነባሮችን በማውገዝ መጀመሩ ተገቢ አልነበረም ባይ ናቸው፡፡ ማህበር መቋቋሙ የሚደገፍ ነው ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ነገር ግን ጦርነት አውጆ መነሳት በስሜታዊነት ከመነዳት የዘለለ ፋይዳ የለውም ብለዋል፡፡ ማህበሩ ከውጭ ሃይሎች ጋር ተሣስሮ ለመስራት መሞከሩ በሃገር ህልውና ላይ አደጋ የሚጋርጥ ነው ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ለውጭ ሃይሎች የሚንበረከክ ማህበር ማየት እንደማይፈልጉ ጠቁመው፤ ከአዲሱ ማህበር ጋር ምንም አይነት የጥቅም ግጭት እንደሌላቸውም ገልፀዋል፡፡ እንዲህ ያለ ውዝግብና ትርምን ውስጥ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በዛሬው ዕለት በአገራችን ይከበራል፡፡

Read 1891 times