Saturday, 03 May 2014 13:23

በአስናቀች ወርቁ ህይወት ዙሪያ የሚያጠነጥነው ‘አስኒ’ ዘጋቢ ፊልም ለእይታ በቃ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በታዋቂዋ የክራር ተጫዋችና ድምጻዊት በአስናቀች ወርቁ የህይወት ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥነውና ‘አስኒ’ የሚል ርዕስ ያለው ዘጋቢ ፊልም፣ ከትናንት በስቲያ በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ-አሜሪካ ጉዳዮች የሲኒማ ጥናቶችና የአፍሪካ ጥናቶች ፕሮግራም ኢንስቲቲዩት ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ በቃ፡፡
ነዋሪነቷ በአሜሪካ በሆነው ራሄል ሳሙኤል ዳይሬክተርነት የተዘጋጀውና ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከአራት አመታት በላይ የፈጀው ይህ ዘጋቢ ፊልም፣ የድምጻዊቷን የህይወትና የሙያ ጉዞ በጥልቀት የሚዳስስ እንደሆነ ታዲያስ መጽሄት ከኒውዮርክ ዘግቧል፡፡
‘አስኒ’ ዘጋቢ ፊልም፣ ከሶስት አመታት በፊት በ76 ዓመት ዕድሜዋ ከዚህ አለም በሞት የተለየችው ድምጻዊት አስናቀች ወርቁ፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ የራሷን ደማቅ አሻራ ጥላ ያለፈች፣ በዘመኗ ለነበሩ ወጣት አርቲስቶች ፈር የቀደደችና፣ በትወናው መስክም ድንቅ ክህሎቷን ያሳየች ዘመን ተሻጋሪ አርቲስት መሆኗን የሚያሳይ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
የፊልሙ ዳይሬክተር ራሄል ሳሙኤል ከዚህ በፊትም በሳንፍራንሲስኮ ውስጥ በተከናወኑ ታላላቅ የማስታወቂያ ፕሮጀክቶች ላይ በተለያዩ ኤጀንሲዎች አማካይነት ስትሰራ የቆየች ሲሆን፣ ፊልሙን ኤዲት ያደረገውና በጋራ ፕሮዲዩስ ያደረገውም፣ በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ ሞሬስ ካንባር የፊልምና የቴሌቪዥን ኢንስቲቲዩት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆነው ኢትዮጵያዊው የማነ ደምሴ ነው፡፡

Read 2470 times