Saturday, 03 May 2014 13:30

በመንግስት የተከለከሉ ስሞች

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ሳውዲ ዓረቢያ በዚህ ወር 50 ስሞችን ጥቁር መዝገብ ውስጥ አስገባች
አንዳንድ መንግስታት፣ ይህንንም ከልክለው ያንንም አግደው ሲያበቁ የሚሰሩት ነገር እየጠፋባቸው የሚጨነቁ ይመስላሉ - የሚከለከል ነገር ቢጠፋ የስም አይነት ይከለክላሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የአንዳንድ ወላጆች ነገረ ሥራ ከአብዮት አይተናነስም፡፡ በስዊድን አገር የልጃቸውን ስም ሲያስመዘግቡ፣ “Brfxxccxx” ብለው ነው የጀመሩት፡፡ የልጃቸው ስም ገና ተጽፎ አላለቀም፡፡ ከ40 በላይ ፊደሎችን የያዘ ስም ነው፡፡ የመጨረሻዎቹ ስምንት ፊደላት “Sqlbb11116” ይላል፡፡ በስንት መከራ ነው ለልጃቸው ሌላ ስም እንዲያወጡ የተደረጉት፡፡
በየአገሩ በልጆቹ ስም ላይ ለመጫወት ወይም ለመቀናጣት የሚሞክር ወላጅ እንደማይጠፋ በመጠቆም፣ ግሎባል ፖስት ዘገባውን ሲያቀርብ በኒውዝላንድ ሁለት ወላጆች ሊነበብ የማይችሉ ስሞችን እንዳስመዘገቡ ገልጿል፡፡
እንደ ገመድ የረዘሙ ስሞችን አልመረጡም፡፡ እጥር ምጥን ያሉ ስሞችን ነው ያስመዘገቡት፡፡ አንደኛው ወላጅ ለልጃቸው ስም ሲመርጡለት በአንድ ነጥብ ጨረሱት፡፡ አንዲት የነጥብ ምልክት ብቻ ነች የምትታየው - ሲመዘገብ በድምጽ ምን ተብሎ እንደሚጠራ እንጃ፡፡ ሌላኛው ወላጅም እንዲሁ የልጃቸውን ስም ሲያስመዘግቡ ትንጥዬ ጨረር መሰል ምልክት አስፍረዋል (*) በዚህም በዚያም ተብሎ የኋላ ኋላ ለልጆቻቸው ሌላ ስም ለመምረጥ ተስማምተዋል
እንዲህ አይነት ችግሮችን ለማስወገድ፤ በጃፓን፣ የልጆች ስም በቀላሉ በጽሑፍ የሚገለጽና የሚነበብ መሆን አለበት የሚል ህግ አለ፡፡ ተገቢ አይደሉም የሚባሉ ስሞችም ይከለክላሉ፡፡ ለምሳሌ “አኩማ” ብሎ ስም አይፈቀድም - ሰይጣን እንደማለት ነው፡፡
በጀርመን፣ የወንዶችን ስም ለሴት ወይም ደግሞ የሴቶችን ስም ለወንድ መጠቀም አይቻልም፡፡ ከዚህ በላይ፤ የወንድ ይሁን የሴት ተለይተው የማይታወቁ ስሞች ተቀባይነት አይኖራቸውም፡፡
አንዳንድ አገሮችማ የሚፈቀዱና የማይፈቀዱ የስም አይነቶችን እየዘረዘሩ አዋጅ አውጥተዋል፡፡ በክርስትና የሃይማኖት አክራሪነት በነበረበት ዘመን በፖርቱጋል የሚፈቀዱ ስሞች በሃይማኖታዊ መፃሕፍት ውስጥ የተጠቀሱ ስሞች ብቻ ነበሩ፡፡ በእስልምና የሃይማኖት አክራሪነትን የሚያራምዱ ሰዎች በመበርከታቸው ይመስላል፣ ማሌዢያ ከስምንት አመት በፊት አዲስ ህግ አውጥታለች፡፡ ልጆችን በእንስሳት፣ በነፍሳት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በቅጠላቅጠልና በቀለም አይነቶች መሰየም ይከለክላል ህጉ፡፡ ብርቱኳን፣ ሃረገወይን፣ አንበሴ፣ ነብሮ፣ ግራር ወይም ፅድ ብሎ መሰየም አይቻልም፡፡ በዚህ ወር በሳዑዲ አረቢያ በጥቁር መዝገብ ውስጥ እንዲካተቱ ከተደረጉት 50 ስሞች መካከል ገሚሶቹ የተወገዙት ከውጭ አገር የተወሰዱ ናቸው በሚል ምክንያት ነው - ሊንዳ እና አሊክ የመሳሰሉ ስሞች፡፡ የንጉሳዊውን ቤተሰብ ክብር ይዳፈራሉ ተብለው ከታገዱት ስሞች መካከል ደግሞ “ማሊካ” የሚል ይገኝበታል - እቴጌ ወይም ንግስት ማለት ነው፡፡ በሃይማኖት ሰበብ የተከለከሉም አሉ፡፡ ጅብሪል (ገብርኤል) ብለው ለልጅዎ ስም ማውጣት አይችሉም፡፡  

Read 8361 times