Saturday, 03 May 2014 13:31

አሁን በወጣትነት እድሜ ላይ የደረሱ ከእናት ወደ ልጅ ኤች.አይ. ቪ የተላለፈባቸው ልጆች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ይኸው ተገልጦ ከማያልቀው ታሪካችን ለዛሬ ይህን ገፅ ፈቅዳችሁ ብታነቡኝ በመጨረሻ አእምሮአችሁ ውስጥ በርካታ ጥያቄዎች ሊነሱ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ አንባቢው ፀሃፊ (የስነ ፅሁፍ ሰው) ከሆነ ደግሞ ቀጥሎ ከማወጋችሁ ብጥስጣሽ የህይወት ገፅታዎች ጫፋቸውን ይዞ በመከተል ሌሎች ደርዞችን ሊያወጣ ይችላል፡፡
በየትኛው ግለሰብ ታሪክ ልጀምር፡- ስሜትን በሚጎዱ፣ በሚያሳዝኑ፣ እጅግ በሚደንቁና በሚያስደስቱ፣ የሚገርም የስነ ልቦና ብርታት በሚታይባቸው፣ ወደ ስጋት ስሜት በሚጨምሩ? ቆይታዬ እስከ አስር የሚደርሱ ታዳጊ ወጣቶች ጋር ነበር እድሜአቸው ከ14 እስከ 18 ነው፡፡ የተለያዩ ጥያቄዎችን እያነሳሁ፡፡ የግል ጉዳይ ከመሆኑ አንፃር አንድ በአንድ ለማውጋት ችለናል፡፡
እድሜህ ስንት ነው?
   “14”
ስንተኛ ክፍል ነህ?
  “9ኛ”
የትምህርት ደረጃህ እዴት ነው ጎበዝ ነህ ወይስ?
  “ በጣም ጎበዝ ተማሪ ነኝ 8ኛ ክፍል በት/ቤቴ ከፍተኛ
   ውጤት ካመጡ ውስጥ አንዱ ነኝ 92 ነው ያመጣሁት
   ከ7 ወደ 8ኛ አንደኛ ነው የወጣሁት”
ቤት ምን ይደረግልሃል እደዚህ ከፍተኛ ውጤት   ስታመጣ?
   “ ብስክሌት ሁሉ ተሸልሜ አውቃለሁ”

ሌላዋ የ 18 ዓመት ታዳጊ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ስትሆን የጤና ትምህርት ትማራለች፡፡ መቼና እንዴት ከቫይረሱ ጋር እንደምትኖር አወጋችኝ፡፡ የሰባት አመት ልጅ ከሆነች በኋላ የጊዜ ቁጥጥር እየተደረገ መድሃኒት እንድትወስድ ይደረጋል፡፡ ይህን መድሃኒት ግን ሌሎች ታላላቆቿ አይወስዱም፡፡ እንክብካቤ ይበዛባል፡፡ በተወሰኑ ጊዜያት በሁለትና በሶስት ወራት ጊዜ ሃኪም ቤት በመሄድ የጤና ምርመራ እንድትወስድ ይደርጋል፡፡ ይች ህፃን እያደገች ስትሄድ የንባብ አቅሟም ከነበረበት ሲጎለብት ከመድሃኒቷና ምርመራዋ ጋር የተያያዙ ወረቀቶችን ታነባለች፡፡ ልጆች እንኳንስ እንዲህ የተለያዩ ጉዳዮችን እየተመለከቱ እንዲሁም በርካታ ጥያቄዎችን ማንሳታቸው የማይቀር ነው፡፡ ይች ልጅም ጥያቄዎችን ማጉረፍ ጀመረች… ቀጠለች፡፡ እድሜዎ 13 ሲደርስ ግን የሆነው ሁሉ በሃኪሟ አማካኝነት ተገለጠላት
“ ግን ያኔ አብዛኛውን ጉዳይ ቀድሜ ስለጠረጠርኩና ስላወኩ ብዙ አልተደናገጥኩም፡፡ ቤተሰቦቼም በጣም አገዙኝ፡፡”
ሌላዋ የሞያና ቴክኒክ ተማሪ የሆነችው የ17 ዓመት ታዳጊ ወጣትም በተመሳሳይ መንገድ ነው ከቫይረሱ ጋር መኖሯን ያወቀችው፡፡ የምትወስዳቸው መድሃኒቶችና ሌሎች የምርመራ ወረቀቶቿን (CD4 መጠንን የሚገልፁ) አስቀድማ ታነብ ነበር፡፡ ሆኖም እናቷን  ላለማስጨነቅ ጥያቄውን ማንሳት አልፈለገችም፡፡ በኋላ ሃኪሟ ከቫይረሱ ጋር እንደምትኖር (አግባብ ነው ባለችው እድሜ) ስትገልፅላት አውቃለሁ አትጨነቂ በሚል ነው የተቀበለችው፡፡ ጊዜውን ጠብቆ መድሃኒት መውሰድ ለብዙዎቹ ታዳጊ ወጣቶች መደበኛና በጣም ተለመደ ድርጊት ነው፡፡ “ለእኔ ኖርማል ነው፡፡ ቁርስ ምሳ ትበላለህ ውኃ ትጠጣለህ እነዚህ ጉዳዮች ለመኖር አስፈላጊ ናቸው፤ ሳትበላ ወይም ሳትጠጣ መኖር አይቻልም መድሃኒቱም ለእኛ እንደዛው ነው” ይላል ሌላው የ16 ዓመት ታዳጊ፡፡
ከእነዚህ ታዳጊ ወጣቶች ጋር በነበረኝ ቆይታ ሌላው በጣም አስፈላጊ የነበረው ጉዳይ የፆታ ግንኙነትን የተመለከተው ­ጥያቄ ነው፡፡ ወጣቶች ናቸው፣ በርካታ ጓደኞች ይኖራሉ፤ ትምህርት፣ ጨዋታ፣ መዝናናት፣ ይኖራል፡፡ በዚህ እድሜና የህይወት ገፅ ላይ ደግሞ መወደድም መውደድም (ማፍቀርም መፈቀርም) ይኖራል፡፡ የፆታ ጓደኝነትና የፍቅር ግንኙነት ጥያቄም ሊቀርብ ወይም ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ይህን በተመለከተ ያለው አስተሳሰብ የተለያየ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ይህን ጉዳይ ፈፅሞ አስበውበት የማያውቁ ናቸው፤ አንዳንዶቹ ጓደኛ አላቸው፡፡ ሆኖም ጓደኛ የያዙት በተመሳሳይ መንገድ (ከእናት ወደ ልጅ ቫይረሱ ከተላለፈባቸውና) ከቫይረሱ ጋር ከሚኖሩ የእድሜ አቻዎቻቸው ጋር ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ፍቅሩ መዋደዱ ወይም ጥያቄው ከቫይረሱ ጋር ከማይኖር ሰው ከመጣስ ወይም ከተፈጠረስ ለሚለው ጥያቄ አንዳንዶች ፈፅሞ አላደርገውም ተገቢም አይደለም ብለው ያስባሉ፡፡ ከዚህ ሁኔታም መራቅ እንደሚፈልጉ ይገልፃሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ እንደሁኔታው ሊወሰን ይችላል፡፡ ለምሳሌ “ጥያቄውን የሚያነሳው ከቫይረሱ ጋር የማይኖር ሰው ከሆነ ራሴን እገልፅላታለሁ፡፡ ሆኖም ፍቅሩ ካየለና መለያየቱ ከባድ ከሆነ አብሬ ልሆን እችላለሁ” ሌላዋ ወጣት ደግሞ “ይከብዳል ምናልባት ዛሬ በአፍላ እድሜና ፍቅር ምንም አይደለም ሊባል ይችላል ነገ ከነገ በኋላ ግን ግጭት ሊፈጠር ይችላል፣ ስሜትን የሚጎዱ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ” የሚሉ አስተሳሰቦች ይሰማሉ፡፡
ልጆቹ በአብዛኛው እንደገለፁልን በመኖርያ አካባቢያቸውና በትምህርት ቤቶቻቸው ያላቸው የህይወት ጉዳይ ሁለት የተለያየ ገፅ የያዘ ነው፡፡ በሰፈራቸው አብረዋቸው ለመብላት የሚፈሩ አብሮ መጫወት የሚሰጉ፣ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን የሚፈፀሙ ሰዎች እንዳሉ ይነገራሉ፡፡ በአንፃሩ በት/ቤቶቻቸው ደግሞ የልጆቹ ማንነት ምንም ስለማይታወቅ ሁሉም ነገር ምንም ባልተለየ መንገድ ይጓዛል(ማግለል፣ መፍራት፣ መፈራት፣ አይታይም)፡፡ ይሁንና ትላለች የዩኒቨርሲቲ የጤና ተማሪ የሆነችው የ18ዓመት ታዳጊ ወጣት አብዛኞቹ የጤና ተማሪዎች አይመስሉም ስለ ኤች አይ ቪ ያላቸው አስተሳሰብና እውቀት ያስደነግጠኛል ፍፁም ከእነሱ የማይጠበቅ ጉዳይ ያጋጥማል በቁንጫ ቫይረሱ ይተላለፋል የሚል ግምት ያለው ሰው ያጋጥማል፡፡
አብዛኞቹ ከቫይረሱ ጋር በሚኖሩ ታዳጊ ወጣቶች ዘንድ የተገነዘብኩትና ተመሳሳይ ሆኖ ያገኘሁት አንድ ጉዳይ አለ፣ ከቫይረሱ ጋር መኖራቸውን እያወቁ(እየተጠራጠሩ) ደጋግመው ጥያቄዎችን ለወላጆች (ለአሳደጊዎቻቸው፡- በአያት፣ በአክስት፣ በእናት ብቻ፣ ወዘተ የሚያድጉ አሉ) ማንሳት አይፈልጉም መድሃኒት በየቀኑ ለምን እንደመሚወስዱና ሃኪም ቤት በተደጋጋሚ ለምን እንደሚሄዱ አይጠይቁም፣ አባታቸው ወይም እናታቸው (ወይም ሁለቱም) በህይዎት ይኑሩ አይኑሩ አይጠይቁም፡፡ ለምን ለሚለው ጥያቄ የአብዛኞቹ  አስተሳሰብ ሲጠቀለል ወላጆቻቸው እንዲጨነቁ ስለማይፈልጉ ነው፡፡ በፈለጉት ጊዜ ይንገሩንየሚል ሃሳብ ነው ያላቸው፡፡ በእርግጥ ይህ አስተሳሰብ የአብዛኞቹ እንጂ የሁሉም አይደለም፡፡ ለምሳሌ የ17 አመት ታዳጊ ወጣት የሆነችው ባለታሪክ እድሜዋ 14 እስኪደርስ ከቫይረሱ ጋር እንደምትኖር አታውቅም፡፡ ሁለት ወንድሞች አሏት ፣ እናቷ ከቫይረሱ ጋር ይኖራሉ፣ አባትዋ በህይወት የሉም፡፡ ይች ታዳጊ ወጣት ጉዳዩን እናቷ እስከዚህ እድሜ በመደበቃቸው እጅግ እንዳዘነች (እያለቀሰች) ትናገራለች፡፡ እናቴ ይህን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብዙ ጉዳዮች እንደምትደብቀኝ ተሰማኝ በወቅቱ መድሃኒቱን በአግባብና ለምን እነደምወስድ ሳልጨነቅ መውሰድ እችል ነበር፡፡ ሆኖም ለብዙ ጊዜ ደበቀችኝ፡፡ ይህች ታዳጊ ወጣት ከሁለት ወንድሞቿ ውስጥ አንዱ ቫይረሱ የለበትም፡፡ የሌላኛው ሁኔታ ግን አይታወቅም፡፡ የራሱ ሁኔታ አለመታወቁ ብቻ ሳይሆን ስለ ቤተሰቦቹ(ስለ እናትና እህቱ) ከቫይረሱ ጋር መኖር አያውቅም፡፡ ይህም በጣም እንዳሳሰባት ትገልፃለች፡፡
እንግዲህ ወደ ኋላ መለስ ብለን ያለፈውን ጊዜ ስንመለከት ከ20 ዓመታት በፊት ከነበረው ጊዜ ጀምሮ የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ በርካቶች የእድሜ ማራዘሚያ መድሃኒት ባለማግኘታቸው እንዲያልፉ ግድ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ከእነርሱ የሚወለዱ ልጆች ከተወለዱበት ቀን ጀምሮ በወራት እድሜ ውስጥ በርካቶች ከእቅፍ አምልጠዋል፡፡ ጊዜ ተለውጦ መድሃኒቱ ወደ ሀገራችን ከገባበት ( በተለይ በነፃ ከቀረበበት) ጊዜ ጀምሮ በርካታ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖች ህይወታቸውን በአግባቡና በጤና ለመመራት ያስቻለ ሲሆን ራስን የመተካት ምኞትም እውን ሆኗል፡፡ መድሃኒቱ በተለይ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ እድል እንዳይኖር ረድቷል፡፡ ይሁንና ዛሬ የዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆኑት ታዳጊዎች ምንም እንኳን መድሃኒቱ ደርሶላቸው ከቫይረሱ ነፃ መሆን ባይችሉም እድሜያቸውን ለማራዘም ግን መደበኛውን መድሃኒታቸውን ተግተው ይወስዳሉ፡፡ አብዛኞቹ ትልቅ ተስፋ አላቸው የሳይንስ እድገት በእነሱ እድሜ መፍትሄ እንደሚወልድ፡፡ የሁላችንም ተስፋ ነው፡፡ በርቱልን
 የዚህ ርእሰ ጉዳይ ወግ አልተጠናቀቀም፣ ከፈቀዳችሁ ሳምንት አንብቡኝ፡፡   

Read 3092 times