Tuesday, 06 May 2014 09:06

በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ሻምፒዮኖቹ ከሰሞኑ ይታወቃሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ማድሪድ 11ኛውን የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ወሰደች

በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የ2013 /14 የውድድር ዘመን በሚቀጥሉት ሦስት ሳምንታት ያበቃል፡፡ ከጀርመኑ ቦንደስ ሊጋ በስተቀር በእንግሊዙ ፕሪሚዬር ሊግ፤ በጣሊያኑ ሴሪኤ፤ በስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋ እና በፈረንሳዩ ሊግ 1 ሁለት እና ከሁለት በላይ ክለቦች ለዋንጫዎቹ እንደተናነቁ ሲሆን የየሊጎቹ ሻምፒዮኖች ነገ ወይንም በሚቀጥለው ሳምንት ጨዋታዎች  ይታወቃሉ፡፡
በተያያዘ የስፔን ዋና ከተማ ማድሪድ ለ11ኛ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ዋንጫን በመውሰድ አንደኛ ሆነች፡፡ የጣሊያኗ ሚላን ከተማ በ10 የዋንጫ ድሎች ሁለተኛ ደረጃ ስተወስድ የጀርመን ሙኒክ እና የእንግሊዝ ሊቨርፑል ከተሞች እያንዳንዳቸው አምስት፤ እንዲሁም ባርሴሎና እና አያክስ አራት አራት ዋንጫዎችን በመውሰድ ተከታታይ ደረጃ አላቸው፡፡የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ከሶስት ሳምንት በኋላ በፖርቱጋል ዋና ከተማ ሊዝበን በሚገኘው  ኢስታድዮ ዳ ሉዝ ስታድዬም በሁለቱ የማድሪድ ከተማ ክለቦች ሪያል ማድሪድ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ይካሄድል፡፡ የአንድ ከተማ ክለቦች በሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ሲገናኙ በውድድሩ የ55 ዓመታት ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ በግማሽ ፍፃሜው ሪያል ማድሪድ የጀርመኑን ክለብ ባየር ሙኒክ በደርሶ መልስ ውጤት 5ለ0 ሲያሸንፍ አትሌቲኮ ማድሪድ ደግሞ የእንግሊዙን ቼልሲ 3ለ1 በመርታት ለዋንጫው ተገናኝተዋል፡፡ሪያል ማድሪድ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ከሻምፐዮንስ ሊግ ፍፃሜው በፊት በውድድር ዘመኑ በ4 ጨዋታዎች ተገናኝተው ነበር፡፡ በላሊጋው ጨዋታ ላይ አትሌቲኮ 1ለ0 ሲያሸንፍ፤ በኮፓ ዴላሬይ የደርሶ መልስ ሁለት ጨዋታዎችን ሪያል ማድሪድ አሸንፎ በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ 2ለ2 ተለያይተዋል፡፡
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የሻምፒዮንስ ሊግን ዋንጫ ለሚያሸንፈው ክለብ 10.5 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ሽልማት የሚሰጥ ሲሆን ለሁለተኛው ክለብ ደግሞ 6.5 ሚሊዮን ዩሮ ያበረክታል፡፡
አትሌቲኮ ማድሪድ ለሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ከ1974 እኤአ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ሲበቃ ለ9 ጊዜያት የአውሮፓ ሻምፒዮን የሆነው ሪያል ማድሪድ ዘንድሮ ለ14ኛው የፍፃሜ ጨዋታ ከመድረሱም በላይ ከ2002 እኤአ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ለዋንጫ በመቅረብ ለ10ኛ ጊዜ ለአውሮፓ ሻምፒዮናነት ክብር ያነጣጥራል፡፡
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊጉ ከዋንጫው ጨዋታ በፊት በተደረጉት 124 ጨዋታዎች 357 ጎሎች የተመዘገቡ ሲሆን የኮከብ ግብ አግቢነቱን የሪያል ማድሪዱ ክርስትያኖ ሮናልዶ በ16 ጎሎች ይመራል፡፡ የሮናልዶ 16 ጎሎች በአንድ የውድድር ዘመን ከፍተኛው የግብ ብዛት ሆነው በክብረወሰን መዝገብ ሰፍረዋል፡፡ ሮናልዶ ባለፉት አምስት የውድድር ዘመናት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ያስቆጠራቸው ግቦች ብዛት 66 የደረሱ ሲሆን የምንግዜም ኮከብ ግብ አግቢው የቀድሞው የሪያል ማድሪድ ተጨዋች ራውል ጎንዛሌዝ በ71 ጎሎች ሲሆን የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ በ67 ሁለተኛ ደረጃ አለው፡፡
ሊቨርፑል 19ኛ ዋንጫውን በራሱ እድል የሚወስነው ሲቲ ነጥብ ከጣለ ነው
የተጨዋች ስብስብ የዋጋ ግምት ማንችስተር ሲቲ 395 ሚሊዮን ፓውንድ ፤ የቼልሲ 340 ሚሊዮን ፓውንድ ፤ የሊቨርፑል 250 ሚሊዮን ፓውንድ
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዘንድሮ ገናናውን ክለብ ሊቨርፑል ወደዋንጫ አቅርቦታል፡፡ ከሳምንት በፊት ግን ሁለተኛ ደረጃ ላይ የነበረው ቼልሲ ሊቨርፑልን 2ለ0 ማሸነፉ የዋንጫው ትንቅንቅ በሶስት ክለቦች መካከል እንዲሆን አድርጓል፡፡ ሊቨርፑል፤ ቼልሲ እና ማንችስተር ሲቲ የተናነቁበት ዋንጫ የት እንደሚገባ የሚወስኑት ደግሞ  የቀሩት የሁለት ሳምንት ጨዋታዎች ይሆናሉ፡፡ በፕሪሚዬር ሊጉ የ36 ሳምንታት ጨዋታዎች 357 ጨዋታዎች ተደርገዋል፡፡ 986 ጎሎች ከመረብ ያረፉ ሲሆን በእያንዳንዱ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ በአማካይ 2.78 ሲመዘገብ ቆይቷል፡፡ የኮከብ ግብ አግቢነቱን ደረጃ የሚመራው ደግሞ የሊቨርፑሉ ሊውስ ሱዋሬዝ በ30 ጎሎች ነው፡፡ በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾች ማህበር ምርጫ የፕሪሚዬር ሊጉ የዓመቱ ምርጥ አጥቂ የተባለው የ27 አመቱ ኡራጋዊ ሊውስ ስዋሬዝ አንፊልድን ይለቃል በተለይ ወደ ሪያል ማድሪድ መዛወሩ አይቀርም እየተባለ ነበር፡፡ ተጨዋቹ በጉዳዩ ላይ ሰሞኑን በሰጠው ምላሽ ‹‹ምንም ነገር አይፈጥርም፡፡ ትኩረቴ የሊቨርፑልን የዋንጫ ህልም ማሳካት ነው›› ብሏል፡፡ ሊቨርፑል በብሬንዳን ሮጀርስ አማካኝነት 19ኛውን የፕሪሚዬር ሊግ የሻምፒዮናነት ክብሩን ካጣጣመ ለፕሪሚዬር ሊጉ ፉክክር ከፍተኛ ለውጥ ይፈጥራል እየተባለ ነው፡፡
ሊቨርፑል የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ከሆነ ከ22 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ የአንፊልዱ ክለብ በዘንድሮ ግስጋሴው በከፍተኛደረጃ ለዋንጫ የቀረበው በ16 ጨዋታዎች ባለመሸነፉ እና 11 ጨዋታዎችን በተከታታይ በማሸነፉ ነው፡፡ ከሚቀሩት የሁለት ሳምንታት ቀሪ ጨዋታዎች በፊት ሊቨርፑል  በ36 ጨዋታዎች 80 ነጥብ እና 50 የግብ ክፍያ አስመዝግቦ ሊጉን ሲመራ፤ ቼልሲ በ78 ነጥብ እና በ43 የግብ ክፍያ በሁለተኛ ደረጃ  እንዲሁም አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማን ሲቲ በ77 ነጥብ እና በ58 የግብ ክፍያ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተያያዙት ሊቨርፑል እና ቼልሲ ለሚቀጥለው ውድድር ዘመን የሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል በቀጥታ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በቀሪዎቹ  ሁለት ሳምንት ጨዋታዎች  ከማን ሲቲ እና ከሊቨርፑል የቀለሉ ተጋጣሚዎች ያሉት ቼልሲ ሲሆን  በወራጅ ቀጠና የሚዳክሩት ኖርዊች እና ካርዲፍ ናቸው፡፡ ሊቨርፑል ደግሞ   ከሜዳ ውጭ ከክሪስታል ፓለስ  በነገው እለት እንዲሁም ከሳምንት በኋላ ከኒውካስትል ዩናይትድ ጋር በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የዋንጫ ሩጫውን ይወስናል፡፡  ነገ ማን ሲቲ ከሜዳው ውጭ ከኤቨርተን ጋር በሚያደርገው ፍልሚያ ነጥብ ከጣለ ለሊቨርፑል አሸናፊነት ምክንያት ይሆናል፡፡
አትሌቲኮ ሊጋውን ሰብሮ የገባው ከ18 ዓመታት በኋላ ነው
የተጨዋች ስብስብ የዋጋ ግምት ባርሴሎና 520 ሚሊዮን ፓውንድ ፤ ሪያል ማድሪድ 505 ሚሊዮን ፓውንድ ፤ አትሌቲኮ ማድሪድ 250 ሚሊዮን ፓውንድ
በስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ የሶስት ሳምንታት ጨዋታዎች ይቀራሉ፡፡ ለዋንጫ ተፎካካሪ የሆኑት አትሌቲኮ ማድሪድ፤ ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ሲሆኑ ሶስቱም ለሚቀጥለው ውድድር ዘመን የሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል በቀጥታ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በፕሪሚያራ ሊጋው በ35 ሳምንታት 334 ጨዋታዎች ተካሂደው 953 ጎሎች ከመረብ ማረፋቸው ሊጉ በአንድ ጨዋታ በአማካይ 2.85 ጎሎች በማስመዝገብ ከአውሮፓ ቀዳሚው አድርጎታል፡፡  በላሊጋው የኮከብ ግብ አግቢዎች ፉክክር ሁለተኛውን የፒቺቺ ሽልማት ለመቀበል እና የአውሮፓ ኮከብ ግብ አግቢ ለመሆን የታጨው የሪያል ማድሪዱ ክርስትያኖ ሮናልዶ በ30 ጎሎች አንደኛ ነው፡፡ አትሌቲኮ ማድሪድ ለረጅም ጊዜያት በባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ተይዞ የነበረውን የዋንጫ ፉክክር በአስደናቂ ብቃት ሰብሮ በመግባት የሻምፒዮናነት እድሉን በቀሩት ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ የሚወስን ይሆናል፡፡ አትሌቲኮ ፕሪሚዬራ ሊጋውን የሚመራው  በ35 ጨዋታዎች 88 ነጥብ እና 53 የግብ ክፍያ በማስመዝገብ ነው፡፡ ነገ ከሌቫንቴ ከሳምንት በኋላ  ደግሞ ከማላጋ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች አትሌቲኮ ማድሪድ ካሸነፈ ዋንጫውን ይወስዳል፡፡ በሁለቱ ጨዋታዎች ካልተሳካለት ግን በሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ የቅርብ ተፎካካሪውን ባርሴሎና በኑካምፕ በመግጠም ሻምፒዮናነቱን የሚወስንበት ከባድ ፈተና ይገጥመዋል፡፡ በነገው እለት በሜዳቸው ጌታፌ እና ቫሌንሽያን እንደየቅደም ተከተላቸው የሚገጥሙት ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ቢሸነፉ እና  በተመሳሳይ ሌቫንቴን አስተናግዶ አትሌቲኮ ማድሪድ የሚያሸንፍ ከሆነ የሁለት ሳምንት ጨዋታዎች እየቀሩት የሊጉን ሻምፒዮንነት ያገኛል፡፡ ከ18 አመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የሻምፒዮናነት ክብር ለማግኘት ከጫፍ የደረሰው አትሌቲኮ ማድሪድ በአርጀንቲናዊው ዲያጎ ሲሚዮኔ የሚመራ ሲሆን በስፔን ትልቁ ሶስተኛ ክለብ ነው፡፡ ባለፉት 5 አመታት  በደጋፊዎቹ ሃይል ያሳየው ለውጥ ከዩሮፓ ሊግ አሸናፊነት ወደ ላሊጋው የሻምፒዮናነት ክብርን ለመቀናቀን እና ለሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ፍልሚያ ለመድረስ አብቅቶታል፡፡ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከሆነ 14 ዓመታትን ያስቆጠረው አትሌቲኮ ማድሪድ ባለፉት ሶስት አመታት በከፍተኛ የመዋዕለ ንዋይ ቀውስም ተንገታግቷል፡፡ ያልተከፈለ 52 ሚሊዮን ዩሮ ደሞዝ፤ 517 ሚሊዮን ዩሮ የእዳ ቁልል እና 171 ሚሊዮን ያልተከፈለ ቀረጥ የሚያንገዳግደው ክለብም ነበር፡፡
ከላሊጋው የዋንጫ ክብር እየራቀ የመጣው ባርሴሎና በ84 ነጥብ እና በ67 የግብ ክፍያ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ  ሪያል ማድሪድ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ82 ነጥብ እና 66 የግብ ክፍያ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ጁቬንትስ ለስኩዴቶ ሃትሪክ ተቃርቧል
የተጨዋች ስብስብ የዋጋ ግምት ጁቬንትስ 310 ሚሊዮን ፓውንድ ፤ ሮማ 165 ሚሊዮን ፓውንድ
በጣሊያን ሴሪ ኤ ከሳምንት በፊት ኤኤስ ሮማ ኤሲሚላንን ካሸነፈ በኋላ  ጁቬንትስ ለሶስተኛ ተከታታይ ዓመት የስኩዴቶውን ክብር ለማግኘት የያዘውን ግስጋሴ ሊያዘገየው ችሏል፡፡ ያም ሆኖ ጁቬንትስ በቀጣይ ሰኞ በሜዳው ከአትላንታ ጋር ተጫውቶ የሚያሸንፍ ከሆነ ለ30ኛ ጊዜ የስኩዴቶውን ክብር የሚጎናፀፍሲሆን  ከዚያ በፊት ግን ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሮማ ነገ ከካታኒያ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ነጥብ መጣሉን ይጠብቃል፡፡ የጣሊያን ክለቦች ከሻምፒዮንስ ሊጉ በውጤት እየራቁ ቢሆንም የሴሪኤው ውድድር ዘንድሮ ከባለፉት ሶስት ዓመታት የተሻለ ፉክክር እንደታየበት ተዘግቧል፡፡  ጁቬንትስ በ35 ጨዋታዎች 93 ነጥብ በመያዝ እና 52 የግብ ክፍያዎች በማስመዝገብ ሴሪኤውን እየመራ ሲሆን ኤኤስ ሮማ በ85 ነጥብ እና በ52 የግብ ክፍያ ይከተለዋል፡፡ ሊገባደድ ሶስት ሳምንታት በቀሩት የጣሊያን ሴሪኤ በ35 ሳምንታት ውስጥ በተደረጉ 344 ጨዋታዎች 923 ጎሎች የተመዘገቡ ሲሆን በሊጉ በአንድ ጨዋታ በአማካይ 2.68 ጎሎች የሚገቡበት ሆኖ ቆይቷል፡፡
ፓሪስ ሴንትዠርመን ክብሩ ያስጠብቃል
የፈረንሳይ ሊግ 1  የዛሬ ሳምንት የሚያበቃ ሲሆን የአምናው ሻምፒዮን ፓሪስ ሴንትዠርመን  በተከታታይ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ክብሩን የማስጠበቅ እድል እንደያዘ ነው፡፡  የደረጃ ሰንጠረዡን ፓሪስ ሴንትዠርመን የሚመራው በ35 ጨዋታዎች 83 ነጥብ እና 56 የግብ ክፍያ በመሰብሰብ  ሲሆን   ኤኤስ ሞናኮ በ75 ነጥብ ሁለተኛ ነው፡፡ፓሪስ ሴንትዠርመን የተጨዋች ስብስቡ በ325 ሚሊዮን ፓውንድ ሲገመት ኤኤስ ሞናኮ በ190 ሚሊዮን ፓውንድ ተተምኗል፡፡
ባየር ሙኒክ የውድድር ዘመኑን በሶስትዋንጫ ለመደምደም አነጣጥሯል
የተጨዋች ስብስብ የዋጋ ግምት ባየር ሙኒክ 470 ሚሊዮን ፓውንድ  ፤ ቦርስያ ዶርትመንድ 285 ሚሊዮን ፓውንድ
በጀርመን ቦንደስ ሊጋ የሻምፒዮንነት ክብሩን ከወር በፊት ሰባት የሊግ ጨዋታዎች እየቀሩት ያረጋገጠው ባየር ሙኒክ ከዓለምክለቦች ሻምፒዮናነት ጋር ሁለት ዋንጫ ወደ መደርደርያው ቢያስገባም የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ክብር ሳያስጠብቅ መቅረቱ ደጋፊዎቹን አስከፍቷል፡፡
 የክለቡ አሰልጣኝፔፔ ጋርዲዮላ ግን  የውድድር ዘመኑን በሶስት ዋንጫዎች ከደመደምን ትልቅ ስኬት ነው ብሎ ተናግሯል፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ በጀርመን ካፕ ጨዋታ ባየር ሙኒክ ከቦርስያ ዶርትመንድ ጋር ይፋጠጣል፡፡ ቦንደስ ሊጋው ከሳምንት በኋላ የሚያበቃ ሲሆን ባየር ሙኒክ በ32 ጨዋታዎች 84 ነጥብ እና 67 የግብ ክፍያ በመሰብሰብ እየመራው ነው፡፡ ቦርስያ ዶርትመንድ በ65 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ተተምኗል፡፡

Read 2460 times