Tuesday, 06 May 2014 09:09

ዋልያዎቹ ለ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እድላቸውን ያሳካሉ!?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(5 votes)

ኢትዮጵያ - ዋልያዎቹ

  •  ዋና አሰልጣኝ —ማርያኖ ባሬቶ
  •  ደረጃ —101 በዓለም
  •  የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ —10  ጊዜ    (በ1968 ሻምፒዮን)
  •  23 ተጨዋቾች፤ 6  ፕሮፌሽናሎች፤ የዋጋ ተመን 675ሺ ፓውንድ
  •  ውዱ ተጨዋች —ሳላዲን ሰኢድ  275ሺ ፓውንድ
  •   አማካይ እድሜ— 25.3
  •   ልምድ— 325 ጨዋታዎች

ኢትዮጵያ በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ  ያገኘችው ድልድል ጠንካራ የሚባል ቢሆንም የማለፍ እድል እንደሚኖራት ግምት አሳደረ፡፡ የአፍሪካ  ኳስ ኮንፌደሬሽን ከ5 ወራት በኋላ ለሚጀመረው ማጣርያ የምድብ ድልድሉን ይፋ ሲያደርግ  ኢትዮጵያ በምድብ 2 ከአልጄርያና ከማሊ የተገናኘች ሲሆን የምድቡ አራተኛ ቡድን በሁለተኛ ዙር ማጣርያ ላይ ከሚገኙት ስዋቶሜ ፕሪሲፒ ፤ቤኒን፤ማላዊና ቻድ አንዱ ይሆናል፡፡
በምድብ ድልድሉ ላይ ካይሮ ተገኝተው የነበሩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ለካፍ ኦፊሴላዊ ድረገፅ ላይ በሰጡት አስተያየት‹‹ ጠንካራ ምድብ ውስጥ እንገኛለን፡፡  ከምድቡ አንደኛ ወይንም ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ የምንጨርስበት እድል መፈጠሩን አስባለሁ፡፡ አዎ ፉክክሩ ፈታኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በአፍሪካ ዋንጫ ከዚያም በቻን የነበሩን ተሳትፎዎችን ማጠናከር እንፈልጋለን፡፡ አዲስ የቀጠርናቸው አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ቡድኑን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ብቻ ሳይሆን የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የምድብ ማጣርያውን የምትጀምረው በሴፕቴምበር  5 እና 6 በሜዳዋ ከአልጄርያ ጋር በምታደርገው ጨዋታ ነው፡፡ ይህ ጨዋታ ለዋልያዎቹ እና ለአዲሱ አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ መልካም አጀማመር ወሳኝ ይሆናል፡፡ በዚሁ የምድብ 2 የማጣርያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባለው ሰፊ የዝግጅት ጊዜ በአካል ብቃት እና በአቋም መፈተሻ ግጥሚያዎች የተጠናከረ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አልጄርያ በብራዚል በሚደረገው 20ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ መሆኗ የግጥሚያውን ክብደት የሚያሳይ ነው፡፡ የምድብ 2 ሁለተኛ የማጣርያ ጨዋታ ሴፕቴምበር 10 ላይ ከሁለት ወራት በኋላ ከሚታወቀው አራተኛ ቡድን  ከሜዳዋ ውጭ የሚደረግ ነው፡፡ ስዋቶሜ ፕሪሲፒ ፤ቤኒን፤ማላዊና ቻድ አንዳቸው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ  3ኛውን የምድብ ማጣርያ ጨዋታ በሜዳዋ ኦክቶበር 10 እና 11 ላይ ከማሊ ጋር የምታደርግ ሲሆን በሳምንቱ የመልሱን ፍልሚያ ከሜዳዋ ውጭ ከማሊ በምታደርገው 4ኛው ጨዋታ ትቀጥላለች፡፡ 5ኛውን የምድብ ማጣርያ ጨዋታ  በኦክቶበር 15  ከሜዳዋ ውጭ ከአልጄርያ ጋር  ካደረገች በኋላ  የምድብ ማጣርያው የመጨረሻ ስድስተኛ ጨዋታ ኖቬምበር 14 እና 15 በአዲስ አበባ ከሁለት ወራት በኋላ የሚታወቀውን አራተኛ ቡድን  የምታስተናግድበት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአስተማማኝ ሁኔታ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፉን የሚያረጋግጠው በተሟላ ዝግጅት ለግጥሚያዎቹ ትኩረት መስጠት ከተቻለ ነው፡፡  ዋልያዎቹ በሜዳቸው የሚያደርጓቸውን ሶስቱንም ጨዋታዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማሸነፍ  አለባቸው፡፡ ከሜዳ ውጭ ከሚደረጉት ሶስት ጨዋታዎች ደግሞ  አንድ ድል እና አንድ አቻ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በምድብ 2 ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከተደለደሉት ቡድኖች ከባዱ አልጄርያ ነው፡፡  ኢትዮጵያ እና አልጄርያ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ዋንጫ በአራት ጨዋታዎች ተገናኝተዋል፡፡ በ1968 እኤአ ኢትዮጵያ 3ለ1 ስታሸንፍ፤ በ1985 እና በ1994 እኤአ በሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች 0ለ0 አቻ ተለያይተዋል፡፡ እኤአ በ1995 ደግሞ አልጄርያ 2ለ0 አሸንፋለች፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እና ማሊ በአፍሪካ ዋንጫ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ተገናኝተው አያውቁም፡፡  ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና በኮንፌደሬሽን ካፕ ስታድ ዴ ማሊዬን እና ስተታድ ዲ ባማኮ የተባሉት የማሊ ክለቦች ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር መገናኘታቸው በልምድነት ሊጠቀስ ይችላል፡

Read 3254 times