Saturday, 10 May 2014 12:24

በየዓመቱ የሚሊዮኖችን ሕይወት እየቀጠፉ ያሉት የመኪናና የሥራ ቦታ አደጋዎች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ለራስ፣ ለቤተሰብ፣ ለማህበረሰብ፣ ለአገር፣…. የሚጠቅም ራዕይና ሕልም ይዘው ወደ ት/ቤት ወደ ግል ጉዳይ፣ ወደ ሥራ፣

ወደቤት… ሲሄዱ፣ የመኪና አደጋ ካሰቡበት ሳይደርሱ መንገድ ላይ ያስቀራቸውን ዜጎች ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ በኮልፌ

የደረሰውን የመኪና አደጋ፣ አባይ በረሃ የተቃጠለውን ስካይ ባስ፣ በቅርቡ እንኳ በሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ … የደረሱትን

የመኪና አደጋዎች ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
በየዕለቱ፣ በራዲዮ በሚቀርበው የትራፊክ አደጋ፣ የሞት፣ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት… ሲሰማ

“አሽከርካሪዎች ጆሮ የላቸውም ወይ?” ያሰኛል፡፡ ይህ ሁኔታ ሁነኛ መፍትሔ ካልተፈለገለትና በዚሁ የሚቀጥል ሆነ ከ16

ዓመት በኋላ (በ2030 እ.ኤ.አ)፣ የመኪና አደጋ በመላው ዓለም ከመጀመሪያዎቹ 5 የሞት መንስኤዎች አንዱ እንደሚሆን

የዓለም ጤና ድርጅት ተንብዮአል፡፡
ግምቱ ያለምክንያት አይደለም፡፡ በዓለም ላይ በየዓመቱ በመንገድ ላይ (በመኪና) አደጋ 1.24 ሰዎች እንደሚሞቱና 50

ሚሊዮን ያህል እንደሚቆስሉ የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል፡፡ ከሟቾቹ ግማሽ ያህሉ፣ እግረኞች፣ ቢስክሌትና የህዝብ

ትራንስፖርት ተጠቃሚ መንገደኞች ናቸው፡፡ ከመቶ ሰዎች 90ዎቹ የሚሞቱት አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች

ሲሆን ከመቶ የመኪና አደጋዎች 62ቱ የሚከሰቱት አገራችንን ጨምሮ በ10 አገሮች ብቻ እንደሆነ የጤና ድርጅቱ ሪፖርት

አመልክቷል፡
ሌላው የሚሊዮኖች ሞት ምክንያት የሥራ ቦታ አደጋና በሽታ ነው፡፡ በሥራ ቦታ አደጋና በሽታ በየ15 ሰከንዱ አንድ

ሰራተኛ ይሞታል፡፡ 160 ሰራተኞች ደግሞ የስራ ቦታ አደጋ ሰለባ ይሆናሉ፡፡ በደሌ (ሄኒከን) ቢራ የዘንድሮውን የዓለም

የደህንነትና የጤና ቀን ባሳለፍነው ሳምንት ባከበረበት ወቅት ለሰራተኞቹ ያሰራጨው በራሪ ወረቀት፣ በዓለም ላይ በየቀኑ

6,300፣ በዓመት 2.3 ሚሊዮን ሰዎች በሥራ ቦታ በሚፈጠር አደጋ እንደሚሞቱና በየዓመቱ 317ሺ የሥራ ቦታ አደጋዎች

እንደሚያጋጥሙ አመልክቷል፡፡
በዕለቱ፣ በደሌ ቢራ የመኪናና የሥራ ላይ አደጋዎች የሚያደርሱትን ጉዳትና መከላከያውን በልዩ ልዩ ዘዴዎች፣

ለከተማዋና ለአካባቢዋ ነዋሪዎች፣ እንዲሁም ለፋብሪካው ሰራተኞች አስተምሯል፡፡ በከተማዋ አደባባይ እግረኞች

ከትራፊክ አደጋ ለመጠበቅ ግራቸውን ይዘው እንዲጓዙ፣ አሽከርካሪዎችም የትራፊክ ሕግ አክብረው እንዲያሽከረክሩ፣

ጉዳዩ በሚመለከታቸው ሰዎች ትምህርት ከመሰጠቱም በላይ የነዋሪውን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ በሁለቱም ፆታ በጎዳና ላይ

ሩጫ ላሸነፉ ተወዳዳሪዎች ሽልማት ሰጥቷል፡፡  በድርጅቱ ግቢ ውስጥ የሥራ ላይ ደህንነትን አስመልክቶ ለሰራተኞች

የተለያዩ የአደጋ ዓይነቶች፣ መንስኤና መከላከያ በተለያዩ ዘዴዎች ከማስተማሩም በላይ በተደረጉ ውድድሮች ላሸነፉ

ሰራተኞች ሽልማት ሰጥቷል፡፡
በሞባይል እያወሩ መኪና ማሽከርከር፣ ሲዲ ወይም ራዲዮ መቀየር፣ መኪና ውስጥ መብላት፣ ወደ ውጪ ሌላ ነገር ማየት፣

ጠጥቶ ማሽከርከር፣ የተለያዩ አደንዛዥ ዕፆች መጠቀም፣ እያሽከረከሩ መዋብና አጎንብሶ ዕቃ ማንሳት፣ በፍጥነትና

በግዴለሽነት መንዳት፣ መጥፎ የአየር ፀባይና የተበላሸ መንገድ ዋነኞቹ የአደጋ መንስኤ ምክንያቶች መሆናቸው

ተገልጿል፡፡
በደሌ ቢራ የሥራ ቦታ ደህንነትን ለመጠበቅና አደጋን ለመከላከል ከሰራተኞቹ ውስጥ የሙያ ደህንነት ጀግና ለመምረጥ፣

የእሳት አደጋ መኪና ለመግዛትና ጥራት ያላቸው የአደጋ መከላከያ ቁሳቁስ ከውጭ ለማስመጣት ማቀዱ ታውቋል፡፡

Read 2397 times