Saturday, 10 May 2014 12:30

የፌስቡክ “ፓስዎርድ” ለመሰረቅ ሲሞክሩ ራሳቸው ጉድ ሆኑ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

የጓደኛዎን ወይም የጐረቤትዎን የፌስቡክ “ፓስወርድ” ለማግኘትና ገመናውን ወይም ሚስጥሯን መበርበር ይፈልጋሉ?

ቀላል ነው፡፡ አንድ መስመር በማትሞላ ጽሑፍ የልብዎን ማድረስ ይችላሉ፡፡ አንድ ደቂቃ አይፈጅም፡፡ “ኮፒ” ከዚያ

“ፔስት” ማድረግ ብቻ ነው ከእርስዎ የሚጠበቀው። ከሁለት ሰዓት በኋላ፤ የጓደኛዎ ወይም የጐረቤትዎ ፓስወርድ እጅ

ይገባል…
በኢንተርኔት የተሰራጨው መልዕክት አጭርና ግልጽ ነው፡፡ በዚሁ መልዕክት የተማረኩ ብዙ ህንዳዊያን ወጣቶች በሁለት

አቅጣጫ የሚመነዘር ትርጉም እንዳለው ልብ አላሉትም፡፡ የሰዎችን ፓስወርድ በቀላሉ መስረቅ ትችላለህ - ይሄ አንደኛው

ትርጉም ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች ያንተን ፓስወርድ በቀላሉ መስረቅ ይችላሉ፡፡ ይሄንን ሁለተኛ ትርጉም ልብ ለማለት ጊዜና

ፍላጐት ያልነበራቸው በሺ የሚቆጠሩ ህንዳዊያን፤ የጓደኞቻቸውን ወይም የስራ ባልረቦቻቸውን ገመና ለመበርበር

ቸኩለዋል። እውነትም ነገርዬው ቀላል ነው - “ኮፒ - ፔስት”… “ኮፒ - ፔስት”
በእርግጥም፤ ያቺ አንድ መስመር የማትሞላ ፅሁፍ የዋዛ አይደለችም፡፡ ፓስወርድ ለመስረቅ ተብላ የተቀመመች ናት፡፡

ግን…እዚህ ላይ ነው፤ ታሪኩ ድንገት የሚታጠፈው - “ሰርፕራይዝ” እንደሚባለው፡፡
“ኮፒ - ፔስት” ቀላል ቢሆንም፤ ኮምፒዩተራቸው ምን እያደረገ እንደሆነ አያውቁም። ፓስወርድ እየተሰረቀ ቢሆንም፤

ከሌላ ሰው ተሰርቆ እየመጣላቸው አይደለም፡፡ ከሁለት ሰዓት ጥበቃ በኋላ ምን እንደሚፈጠር ለማየት ነው የሚጠብቁት።

የራሳቸው ኮምፒዩተር፤ የራሳቸውን የፌስቡክ ፓስወርድ አፈላልጐ ለማግኘት፤ ከዚያም ያንን ፓስወርድ ወደሌላ ሰው

አድራሻ ለመላክ ትንሽ ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ ለካ፣ የሌላ ሰው ፓስወርድ ለመስረቅ ሳይሆን፣ የራሳቸው ፓስወርድ እንዲሰረቅ

ነው በፈቃደኝነት የተባበሩት፡፡ “አጭር ምጥን ብላ የተቀመመችና የተራቀቀች ስርቆት” ይሉሃል እንዲህ ነው፡፡ አንድ ሰው

የሆነ ጊዜ ላይ የፈጠራትና ያሰራጫት ዘዴ ናት፡፡ ከዚያ በኋላማ የሆነ ቦታ ሆኖ፣ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በሺ የሚቆጠሩ

የፌስቡክ ፓስወርዶች በአድራሻው እየተላኩ ፓስወርዶችን መሰብሰብ ነው፡፡
ከጥቂት ወራት በፊትም በተመሳሳይ የማታለያ ዘዴ የፓስወርድ ስርቆት እንደተካሄደ የገለፀው ገልፍ ኒውስ እንደሚለው፤

100ሺ ያህል የፌስቡክ ደንበኞች ፓስወርድ ተሰርቆባቸዋል፡፡ ቁምነገሩ ግን፤ እበላለሁ ሲሉ መበላት፤ እነጥቃለሁ ሲሉ

መነጠቅ ይኖራልና እንጠንቀቅ የሚል ነው፡፡
ከሰሞኑ ከወደ ፊሊፒንስ የወጣውም ጉድ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ በፌስቡክ አለም፤ ማን ምን እንደሆነ በእርግጠኛነት

ለማወቅ ያስቸግራል። ለዚያም ነው፤ በእውነተኛው አለም በሰው ፊት የማንናገራቸውና የማናደርጋቸው ነገሮች፤ በፌስቡክ

አለም ለመናገርና ለማድረግ ብዙዎች የሚደፋፈሩት። ስኮትላንዳዊው ታዳጊ፣ በፌስቡክ የአንዲት ቆንጅዬ ፎቶ በማየት

ተማርኮ ነው ጓደኝነት (ግንኙነት) የጀመረው፡፡ ብዙም ሳይቆይ የግል ወሬ ማዘውተር መጣ፡፡ ፎቶዎችን ተራ ፎቶ ሳይሆን

ከላይም ከታችም አጋልጠው የሚያሳዩ ፎቶዎችን ተለዋውጠዋል። መኝታ ቤት ውስጥ በወሲብ ጊዜ የሚያጋጥሙ አይነት

ወሬዎችንም ለምደዋል፡፡
ይሄ ሁሉ የሆነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ለታዳጊው ስኮትላንዳዊ ሰማይ ምድሩ የተገለባበጠበትም በአጭር ጊዜ

ውስጥ ነው። “ገንዘብ ካላመጣህ፤ ያ ሁሉ ያወራነውን ነገር በኢንተርኔት በፌስቡክ እለቀዋለሁ” የሚል ማስፈራሪያ

ደረሰው፡፡
“በጓደኝነት የፌስቡክ ግንኙነት የፈጠረው፤ ቆንጅዬ ፎቶ በማየት ከተማረከላት ሴት ጋር አይደለም፡፡ ሰዎችን

በማስፈራራት ገንዘብ ከሚዘርፉ የፌስቡክ ማፍያዎች ወጥመድ ውስጥ አስገብተውታል፡፡
የተጠየቀውን ገንዘብ ቢከፍል እንኳ አይለቁትም። በማፍያዎቹ ወጥመድ ተይዘው በማስፈራሪያ ገንዘብ የከፈሉ በርካታ

የፊሊፒንስ ወጣቶች፤ በአንድ ጊዜ አልተገላገሉም፡፡ እንደገና ገንዘብ እንዲያመጡ ይጠየቃሉ፡፡ ብዙዎቹ ሦስት አራቴ

ከከፈሉ በኋላ ነው፤ ማስፈራሪያው ማብቂያ እንደሌለው ገብቷቸው ለፖሊስ የተናገሩት፡፡ የፊሊፒንስ ፖሊስ ወደ 60

ገደማ የፌስቡክ “ማፊያዎችን” በመያዝ ሰሞኑን ፍ/ቤት አቅርቧል፡፡

Read 10392 times