Saturday, 17 May 2014 15:36

“…ልክ አገባሁት!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

             ስሙኝማ፣ ወሬ በዛብንሳ!…ማለት በአንድ ጉዳይ ላይ የምንሰማውና የምናነበው ከመለያያቱና ከመብዛቱ የተነሳ እውነቱንና ሀሰቱን መለየት በጣም አስቸጋሪ የሆነበት ዘመን ላይ ነን። ቴክኖሎጂ ‘እንዳበጁት’ የሆነበት ዘመን ስለሆነ የተነካካውንና ያልተነካካውን መለየት አስቸግሯል። ስሙኝማ… እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… ይሄ ‘ፎቶሾፕ’ የሚሉት ሶፍትዌር ለአቅመ—ሰበብ ደረሰ አይደል! አሀ…የሆነ ነገር በታየ ቁጥር “በፎቶሾፕ አቀናብረውት ነው…” የሚባል ነገር በዛብና! (ፎቶሾፕ ሆዬ፣ ብታውቂበት ይሻልሻል፡ ‘እንዳትፈረጂና’ እንዳታርፊው! ቂ…ቂ…ቂ…) ይቺን ስሙኝማ…በቀደም አንድ ሠርግ ላይ ነው አሉ፤ እናላችሁ ሙሽሮቹ ሲገቡ ነው ሆታው ሲቀልጥ፣ ሁለት ሰዎች ጥግ ይዘው የራሳቸውን ወሬ ያወሩ ነበር አሉ። ታዲያላችሁ…አንደኛው “የት አባቱ ልክ አገባሁት!” ይላል።

“እሷ እሺ ብላ እንደዛ አይነት ነገር አደረግሁ ነው የምትለኝ?” “ደስ ብሏት እንጂ…” “መቼ ነው እንዲህ የሆነው?” “ሦስት ሳ ምንት አ ልሆነውም…” ነገርዬው ምን መሰላችሁ…ሰውየው ለካስ ሙሽሪት ሆዬን ደብቆ ወስዶ እነሆ በረከት ምናምን ብሏል። አጠገባቸው ሆነው የሰሟቸው ሰዎች፣ ሙሉ ታሪኩን ማወቅ ባይችሉም እንኳን ነገርዬው… ሰውየው ከሙሽራው ጋር በሆነ ነገር ተጋጭተው፣ እጩ ሙሽራዋን ‘እንደጎበኛት’ ገብቷቸዋል። አያስደነግጥም! እኔ የምለው እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይሄ ‘ጎበኛት’ የሚባለው አማርኛ አንዳንዴ ግራ ይገባል። ሊጎበኝ የመጣ ወይ እንደየሰዉ ጓዳ…አለ አይደል… “እንደው እንጀራ እጋግራለሁ ብዬ ሥራ ይዞኝ በባዶ መሶብ መጣህ…” ምናምን ተብሎ በርበሬ የተቀባች ቂጣም ሆነ “አንዱን ሲሉት ሌላው፣ አንዱን ሲሉት ሌላው…” ተብሎ የሚወራለት ‘ፋይቭ ኮርስ’ ምናምን ምግብ በልቶ ሲሄድ ነው የምናውቀው። አሀ…አንዳንዱ እኮ ‘ሲጎበኝ’ …‘የዘጠኝ ወር ጦስ’ ቅድሚያ ክፍያ ከፍሎ ነው የሚሄደው። ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ከነገሩ ሁሉ የሚገርመው ወሬው የሚነገረው ጓደኛ “እንዴት እንዲህ አይነት ነገር ታደርጋለህ?” ምናምን እንደ ማለት ሰውየውን እንደ ጀግና “ብራቮ!” ምናምን እያለ ይክበው ነበር። ይቺን ስሙኝማ…ፐርሲቫል ብራውን የተባለ ሀብታም ነበር። እናላችሁ…አንዱ ለእንትናዬው ፍቅሩን ሲገልጽላት እንዲህ ይላታል። “ውዴ፣ በጣም ነው የምወድሽ። እባክሽ የአንተ እሆናለሁ፣ አገባሃለሁ በዪኝ።

እንደ ፐርሲቫል ብራውን ሀብታም አይደለሁም። እንደ ፐርሲቫል ብራውን ቆንጆ ቤት፣ አሪፍ መኪና፣ የወይን ጠጅ ክምችት የለኝም። ግን ውዴ እወድሻለሁ፣ ያላንቺ መኖር አልችልም።” ይሄን ጊዜ እሷዬዋ ምን አለች መሰላችሁ…“ውዴ እኔም እወድሀለሁ፣ ግን የፐርሲቫል ብራውንን አድራሻ ልትሰጠኝ ትችላለህ?” አጉል እቀኛለሁ ብሎ ዋጋውን አገኘላችሁ። ዘንድሮ እዚቹ እኛዋ አገር ውስጥ…አለ አይደል… “የፐርሲቫል ብራውንን አድራሻ ልትሰጠኝ ትችላለህ?” የሚሉ እንትናዬዎች ብዛታቸው ይጠናልንማ! እንደምንሰማቸወ ታሪኮች ከሆነ እዛ አካባቢ ነበሮች እየተበላሹ ነው። ‘አካል’ እዚህኛው ቤት፣ ‘ልብ’ እዛኛው ቤት አይነት ነገር። በእውቀቱ ስዩም እንዲህ የምትል አሪፍ ስንኝ አለችው። አዳም የትናንቱ የጥንት የጠዋቱ ሳይለፋ ሳይታክት ተኝቶ ባደረ ውሃ አጣጭ አቻውን ተጎኑ ተቸረ ይብላኝ ላሁኑ አዳም ለታካች ምስኪኑ ምነው በተኛና በሸሸሁ ከጎኑ ለምትል ሄዋኑ። እናላችሁ…ነገሬ ብላችሁ አይታችሁልኝ እንደሆነ ይሄ ነገሮችን በጥሞናና በብስለት ማየት የሞኝነት አይነት ነገር እየሆነ ነው። ሰውየው ከሙሽራው ጋር በምንም ይጋጭ በምንም ሙሽሪትን ማሳሳት ምን ይሉታል! (“ድንቄም ተሳሳተች!” የምትሉ ሰዎች ትታዩኛላችሁ…) ደግሞስ የትኛውን ትርፍ ሲያስገኝለት ነው! የምር ግን አህያው እያለ ዳውላው ላይ አካኪ ዘራፍ ማለት ቀሺም ነው። ዳውላው ምን ሆነ ምን… አህያው ምንም አይሆንም።

አዲስ ሙሽሪት አንዴም ‘ተጎበኘች’ አሥራ አንዴ እንዴት ሆኖ ነው ሰዎቹ ለተጋጩበት ነገር መፍትሄ የሚሆነው። ስሙኝማ… በፊት እዛ ፈረንጅ አገር ያሉ ወገኖቻችን “ትናንት እኮ የእንትናን እንትን አወጣኋት…” ምናምን ማለት የተለመደ ነበር አሉ። ዘንድሮ እዚሁ እኛው ዘንድ ‘የእንትናን እንትን’ ማውጣት የሂደት (ቂ…ቂ…ቂ…) ጉዳይ ሆኗል አሉ። ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ! ከአንድ ሁለት ዓመታት በፊት አንዲት ሴት አንድ ቀን ማታ አራት ሰዓት አካባቢ ስልክ ትደውልልኝና ምን አለችኝ መሰላችሁ… “አሁን ቤቴ ከልጆቼ ጋር ነኝ ያለሁት። ባለቤቴ ከቅርብ ጓደኛዬ ጋር አልቤርጎ ሲገባ አይቼው ነው የመጣሁት። ይኸውልህ እንዲህ አይነት ዘመነ ላይ ነን።” እንዲህ አይነት ነገር አይደለም በቀጥታ በወሬ፣ ወሬ ስትሰሙ አያስደነግጣችሁም? እናላችሁ… ‘ከተሳሳተ ጥሪ’ ጋር አንሶላ መጋፈፍ የ‘ቴስቴሮን’ መጠን አናት ላይ የመውጣቱ ጉዳይ ሳይሆን ሰውየውንም የመበቀል አይነት ሲሆን… የእውነትም የጉድ ዘመን ላይ ደረስን ያስብላል። የእውነትም ‘ክፋት’ የባህሪይ መገለጫ መሆኑ ቀርቶ የብልህነት መለኪያ የሆነበት ዘመን ደርሰናል።

ምን አይነት ጭንቅላት ያለው ሰው ነው በሁለትና በሦስት ሳምንታት ውስጥ የምታገባ ሙሽራን የወደፊት ባሏን ‘ለመበቀል’ ብሎ የሚጎበኛት! (ቂ…ቂ…ቂ…) በነገራችን ላይ የሙሽሪትን ፈቃደኝነት እዩልኝና ምን አይነት ትዳር እንደሚሆን አስቡት። እናማ… አሁን ከዳር እዳር እያዳረሰን ያለ የሚመስለው የጥላቻ ፖለቲካችን መነሻ ‘ክፋት’፣ እንደ አጉል ባህሪይ መቆጠሩ እየቀነሰ መምጣቱ ይመስለኛል። ይሄ “የት አባቱ ልክ አግባው!” “ጉድ ባናደርጋቸው ሞተናላ!” ምናምን አይነት ነገሮች ሰሚ ጆሮን ‘መሰቅጠጣቸው’ እየቀረ ነው። ስሙኝማ…የከተማችን የመንገድ ትርምስ የትራፊክ ደንብ አለማወቅና የማሽከርከር ብቃት ማነስ ብቻ አይደለም…ውስጣችን በአርማታ እየተገነባ ያለው የጥላቻ ባህሪይ ውጤትም ነው። ነገሬ ብላችሁኝ እንደሆነ ሌላኛውን አሽከርካሪ ቆም ብሎ ከማሳለፍ ይልቅ ዘሎ ጥልቅ ነው። የማለፍ ቅድሚያው የዛኛው ቢሆን እንኳን የጥላቻ ባህሪያችን እንዴት አስችሎን! ድሮ በታክሲ ነጂዎች ብቻ ሲመረር የነበረ ህዝብ፣ አሁን እከሌ ከእከሌብሎ መለየት አቅቶታል። “እንዴት አልፈኸኝ ትሄዳለህ…” ብሎ ያቺን መከረኛ መሀል ጣት፣ ምንም አይነት ባንዲራ ሳይኖራት፣ በመስኮት የሚሰቅል፣ ሁለት ጸጉር አብቅሎ ‘ሦስተኛ ቀለም’ ስለሌለ ብቻ ተፈጥሮ ሂደቷን ያቆመችበት ‘የዕድሜ ባለጸጋ’ መአት ነው።

(መሀል ጣት መቀሰር በደንብና በመመሪያ ይከልከልልንማ! የጣት ነገር ከተነሳ አይቀር…ያኔ እንኳን ሁለት መሆናችንን ለባለታክሲ ለመጠቆም ሦስት ጣት እንቀስር የነበረበት ጊዜ ትዝ አይላችሁም!) ማስታወቂያዎች ስትሰሙና ስታዩ፣ ከዚሀ ቀደም እንዳልነው፣ የተደጋጋመ ነገር አለ። “ምርታችንን አስመስለው ወደ ገበያ ውስጥ የገቡ እንዳሉ ስለደረስንበት…” ምናምን አይነት ነገር ከመደጋገሙ የተነሳ፣ እንደውም አንዳንዴ ዋናዎቹን የማስታወቂያዎቹን መልእክቶች እየዋጠብን ነው። አስመስሎ መሥራቱ ‘በጨው ደንደስ የበርበሬ መወደስ’ አይነት ነገር ብቻ ሳይሆን የክፋትም ይመስለኛል— አለ አይደል…ያኛውን ድርጅት “ልክ አስገባናቸው…” ለማለት! የማስታወቂያ ነገር ካነሳን አይቀር…አንድ የሳሙና ፋብሪካ ምርቱን በተለያዩ መንገዶች ያስተዋውቃል። እናላችሁ…ለበርካታ ወራት ቢያስተዋውቁም ገበያው —የድሮ አራዶች እንደሚሉት—‘ገገመባቸው’። ታዲያማ መአት ወራት ቆይተው የሸጡት ሳሙና ሀምሳ ብቻ ነበር።

ከዚያ ሌላ አሥር ወር ቆይተው የሸጡት ሳሙና ብዛት መቶ ደረሰ። ይሄን ጊዜ ምን የሚል ማስታወቂያ ለቀቁ መሰላችሁ…“ምርታችን በህብረተሰቡ ከመወደዱ የተነሳ ሽያጫችን በእጥፍ ማደጉን ስንገልጽ በደስታ ነው።” እናማ… አሁን፣ አሁን ብዙ ማስታወቂያዎችን ሰምተንና አይተን “እሱን እንኳን ተዉት!” የምንለው…አለ አይደል…በአመት ከምናምን መቶ ሳሙና ስለተሸጠ “…ሽያጫችን በእጥፍ ማደጉን ስንገልጽ በደስታ ነው፣” አይነት ነገር ስለሚመስለን መሆኑ ይታወቅልንማ! እናላችሁ…“የት አባቱ ልክ አገባሁት!” ከሚል አይነት የክፋት አስተሳሰብ አንድዬ የታደገን ዕለት፣ ያኔ ምናልባት…ምናልባት ከክፋት ወዲያኛው ጫፍ፣ መኖሩንም እየረሳነው የመጣነው ‘ደግነት’ የሚባል ባህሪይ እንዳለ ‘እንደርስበት’ ይሆናል። ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4276 times