Monday, 19 May 2014 08:29

ታዳጊዎች በንባብ እንዲገፉ የሚያግዝ መፅሐፍ

Written by  ሊንዳ ዮሐንስ
Rate this item
(0 votes)

                      ስለ ንባብ ጠቃሚነት ብዙ ተብሏል። የንባብ ልምድን ባህል ለማድረግ ደግሞ ንባብ ከልጅነት መጀመር እንዳለበት፣ ለልጆቻችን የህፃናት መፅሐፍ ማንበብና እነሱንም ማስነበብ እንዳለብን የምናውቅ ይመስለኛል። ግን ብዙ የማንሰማውና ክፍተት የሚታይበት የንባብ ጉዳይ የታዳጊ ወጣቶች የንባብ ሁኔታ ነው። ስለ ሕፃናት መፃሕፍት እና የንባብ ልምድ ብዙ ይባልና፣ ህፃናቱ አድገው 12 ወይም 13 አመት ላይ ሲደርሱ፣ ልጆቹ ወደ ምን አይነት መፃሕፍት መሸጋገር እንዳለባቸው ብ ዙ ሲ ታሰብ ወ ይም ሲ ነገር አ ናይም። እድሜያቸው ከ13-18 የሆኑ ታዳጊዎች ልዩ የሆነ ባህሪያት አላቸው። ህፃናት አይደሉም፤ ስለዚህ ስዕልና ደማቅ ቀለማት ያላቸው አስቂኝ የእንስሳት ታሪኮች እንደ ድሮ አይመስጧቸውም። ወይም ደግሞ እንደ ትልቅ ሰዎች የታሪክ ወይም የአዋቂ ልብ ወለድ መፃሕፍት ላይስቧቸው ይችላሉ።

እነኚህ ታዳጊዎች (teenagers) በባህሪያቸው ስለ ራሳቸውና ስለ አካባቢያቸው እውነታ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተረዱ ያሉ እና የመረዳትም ከፍተኛ ፍላጐት ያላቸው ናቸው። ነገር ግን በልጅነታቸው የጀመሩትን የንባብ ልምድ ሊያስቀጥል የሚችል እና የእድሜያቸውን ፍላጐት ታሳቢ ያደረጉ የፅሑፍ ስራዎች ካላገኙ፣ ሌሎች ትኩረቶቻቸውን የሚሻሙ ብዙ ክፉ ጊዜ ማሳለፊያዎች አሉላቸው። በኢትዮጵያ እጅግ ጥቂት ቢሆኑም ለታዳጊ አንባቢያን የተፃፉ መፃሕፍት አሉ። ከነዚህ መሀል የዳንኤል ነጋሽ Breaking the Chain አንዱ ነው። መፅሐፉ በእንግሊዝኛ የተፃፈ ሲሆን 138 ገፆች አሉት። ዳንኤል ነጋሽ ከስምንት በላይ የህፃናት እና የአዋቂዎች መፃሕፍት ያሳተመ ደራሲ ነው።

ይህ መፅሃፍ የዳንኤል የመጀመሪያው የእንግሊዝኛ ስራ ቢሆንም ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት የሚያስገኘውን የ2013 Burt Award for African Literature የተሰኘ ውድድር በአንደኝነት አሸንፎበታል። “ብሬኪንግ ዘ ቼይን” ስለ “ቀውጢዋ” ሙኒት ይተርካል። ሙኒት አስቸጋሪ ኑሮ ትመራለች። በወጣት እድሜዋ ታናሽ ወንድሟን እና ጠጪ አያቷን ትንሽ ሱቅ ውስጥ በመነገድ ታስተዳድራለች። ቤት ውስጥ የምትጋፈጣቸው ችግሮች ሳያንሳት፣ ወንድሟን ከአደጋ ለመጠበቅ በምታደርገው ጥረት በአካባቢዋ ያሉ ወንጀለኞች የሚሰሩትን ሙስና እና በደል ትደርስበታለች። እናም ዳንኤል ነጋሽ ለ138 ገጾች የሙኒትን ውጣ ውረድ ያስነብበናል። የታዳጊዎችን ልብ ሊይዝ በሚችል መልኩ ስለ ሰዎች ህገ-ወጥ ንግድ፣ ስደት እና ሙስና ጉዳዮች ያነሳል።ከላይ ለማስረዳት እንደተሞከረው፣ ታዳጊዎች በልጅነታቸው የጀመሩትን የንባብ ልምድ መቀጠል አለባቸው። እንደ “ብሬኪንግ ዘ ቼይን” ያሉ መፃሕፍት መኖር ደግሞ ይህንን ለታዳጊዎቻችን ማድረግ እንድንችል ያግዙናል። መጽሐፉ፤ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቤተ - መፃሕፍት እና በሜጋ መፃሕፍት መደብር ይገኛል።

Read 2009 times