Monday, 19 May 2014 09:00

አዝናኝ እውነታዎች ስለ ፓብሎ ፒካሶ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

               ስፔናዊው ሰዓሊ ፓብሎ ፒካሶ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ አርቲስት እንደነበር ይታወቃል። እስከ 92 ዓመት እድሜው በመኖር ረዥም ህይወት ያጣጣመው ሰዓሊው፤ የዚያኑ ያህልም በሥራው ውጤታማ እንደነበር ይነገርለታል። በሙያ ዘመኑ እጅግ በርካታ የአሳሳል ዘይቤዎችንና ጭብጦችን የዳሰሰ ሲሆን በተለይ ኩቢዝም የተሰኘውን ዘመናዊ የሥነጥበብ እንቅስቃሴ በፈር-ቀዳጅነት በመምራት የገነነ ስም ተቀዳጅቷል። ፒካሶ ትውልዱ ስፔይን ይሁን እንጂ አብዛኛውን ህይወቱን ያሳለፈው ፈረንሳይ ውስጥ ነበር። የዚህን ታላቅ ሰዓሊ አዝናኝ እውነታዎች እነሆ በረከት - *አዋላጇ የሞተ መስሏት ነበር ፒካሶ ወደዚህች ምድር የመጣው በቀላሉ አልነበረም። በብዙ ውጣ ውረድ ነው የተወለደው። በዚያ ላይ ድክምክም ያለ ህፃን ነበር። በዚህ የተነሳ አዋላጇ ሞቶ የተወለደ ስለመሰላት ችላ አለችው። ጠረጴዛ ላይ አጋድማው እናትየዋን ልትንከባከብ ሄደች። ዶን ሳልቫዶር የተባለ ሃኪም አጎቱ ባያየው ኖሮ አክትሞለት ነበር፣ እሱ ነው ከሞት ያተረፈው።

“በዚያን ዘመን ሃኪሞች ትላልቅ ሲጋር ያጨሱ ነበር። አጎቴም ከእነሱ የተለየ አልነበረም። ጠረጴዛው ላይ ተጋድሜ ሲያየኝ ጪሱን ፊቴ ላይ አቦነነብኝ ። ይሄኔ ከመቀፅበት በብስጭት ድምፅ አሰማሁ” ሲል ፒካሶ የሰማውን ተናግሯል። አዝናኝ እውነታዎች ስለ ፓብሎ ፒካሶ *አፉን የፈታበት የመጀመርያው ቃል ሰዓሊነቱን ያወቀው ገና ሲወለድ ሳይሆን አይቀርም። ከአንደበቱ የወጣው የመጀመርያ ቃል እርሳስ (በስፓኒሽ “piz,”) የሚለው ነበር። ለነገሩ ሰዓሊነት ከዘራቸው ነው። አባቱ ሰዓሊና የሥነጥበብ አስተማሪ (ፕሮፌሰር) ነበሩ። ከ7 ዓመቱ አንስቶ በመደበኛ የሥነጥበብ ትምህርት ኮትኩተው ነው ያሳደጉት። ፒካሶ 13 ዓመት ሲሞላው አባትየው ስዕል መሳል እንደሚያቆሙ ምለው ተገዘቱ። ለምን ቢሉ? ልጃቸው ፒካሶ እንደበለጣቸው ስለተሰማቸው ነበር። *የመጀመርያ ስዕሉን በ9ዓመቱ አጠናቋል ፓብሎ ፒካሶ Le picador የተሰኘውን የመጀመርያ ስዕሉን ሰርቶ ያጠናቀቀው እ.ኤ.አ በ1890 ዓ.ም ሲሆን ያኔ ገና የ9 ዓመት ልጅ ነበር። ስዕሉም በኮርማ ትግል ላይ ፈረስ የሚጋልብ ሰው ያሳያል። የመጀመሪያ “ምሁራዊ” ሥራው የመጀመርያው ቁርባን የተሰኘ ሲሆን በስዕሉ ላይም እናትና አባቱ እንዲሁም አትሮንስ ፊት ተንበርክካ የምታነብ ታናሽ እህቱ ይታያሉ። ፒካሶ ይሄን ስዕሉን ሰርቶ ሲያጠናቅቅ የ15 ዓመት ታዳጊ ነበር። *ክፍል ውስጥ ረባሽ ነበር በሥነጥበብ በኩል ብሩህ አዕምሮ እንደነበረው ፈፅሞ የሚያጠራጥር አይደለም።

በእድሜ አምስትና ስድስት ዓመት የሚበልጡትን የክፍል ጓደኞቹን የትናየት ያስከነዳቸው ነበር። የሱ ችግር ረባሽነቱ ላይ ነው ። ይሄን አድርግ ሲባል ያፌዝ ነበር። በዚህም የተነሳ በተደጋጋሚ ባዶ ክፍል ውስጥ ተዘግቶበታል። “በረባሽ ተማሪነቴ ባዶ ክፍል ውስጥ ብቻዬን ይከረቸምብኝ ነበር። የክፍሉ ግድግዳ ኖራ የተቀባና አግዳሚ ወንበር ያለው ነው። እኔ ግን እዚያ መሆኑን እወደው ነበር። ምክንያቱም የስኬች ደብተሬን ይዤ እገባና ያለገደብ እስላለሁ---ዝም ቢሉኝ ያለማቋረጥ እየሳልኩ ለዝንተዓለም መቀጠል እችል ነበር” *የመጀመርያ ሥራው - 750 ዶላር ፒካሶ የመጀመሪያ ሥራውን የተዋዋለው ፈረንሳይ ውስጥ ከአንድ የስዕል ነጋዴ ጋር ሲሆን በወር 750 ዶላር እንዲከፈለው ነበር የተስማማው። *ፒካሶ ሞና ሊዛን ሰርቋል? በፍፁም አ ልሰረቀም። ነገሩ እንዲህ ነው። እ.ኤ.አ በ1911 ዓ.ም ሞና ሊዛ ከሉቨር ሙዚየም ትሰረቃለች። ፖሊስ የፒካሶ ገጣሚ ጓደኛውን Guillaume Apollinaireን ይይዘዋል። ጓደኛው ደግሞ ጣቱን ወደ ፒካሶ ይጠቁማል። ይሄን ጊዜ ፒካሶም ተይዞ ምርመራ ይደረግበታል። በኋላ ግን ሁለቱም በነፃ ተለቀዋል። *ፍቅረኞቹ ስፍር ቁጥር አልነበራቸውም ዝነኛ ሰዓሊ መሆኑ የፍቅረኞቹን ቁጥር አንበሽብሾለታል። አፍቃሪዎቹ ስፍር ቁጥር አልነበራቸውም። በሞዴልነት የሚሰራቸውንጨምሮ ብዙዎቹ ኮረዶች በቀላሉ ያፈቅሩት ነበር። የመጀመርያ ሚስቱን በ36 ዓመቱ ያገባው ፒካሶ፣ ሁለተኛ ሚስቱን በ79 ዓመቱ ነበር ያገባው - ያውም የ27 ዓመት ወጣት።

Read 5218 times