Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 17 December 2011 09:43

እባካችሁ - “ሽብርተኛ” ስትባባሉ ድምፃችሁን ዝቅ አድርጉ!!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የሶሪያ መንግሥት አይፎንን “ዓይንህ ላፈር” ብሎታል

የዓለምን ፖለቲካዊ ክስተቶች የምትከታተሉ ከሆነ አንድ ነገር ትገነዘባላችሁ ብዬ እገምታለሁ፡፡ ምን አትሉኝም… የዓለም የፖለቲካ መድረክ ስላቅ እየበዛበት መምጣቱን፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ… “ፖለቲካ በፈገግታ” እዚህ ጋዜጣ ላይ ብቻ አይደለም ያለው፡፡ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ፖለቲካ የእውነት “ፖለቲካ በፈገግታ” እየመሰለ መጥቷል፡፡ ለምሳሌ በሶሪያ ላለፉት 8 ወራት በተካሄደ ህዝባዊ አመጽ የአገሪቱ መንግስት በወሰደው የሃይል እርምጃ 4ሺ የሚደርሱ ሶሪያውያን ተገድለዋል፡፡ ሥልጣኔን ከምለቅ “ጥጋብ”  የነፋውን የሶሪያ ህዝብ ከወዳጅ አገራት በማገኘው የጦር መሣሪያ መፍጀት ይቀለኛል  ብለዋል - የሶሪያው ፕሬዚዳንት በሽር አል-አሳድ፡፡

(ወይ የሥልጣን አባዜ!) በቱኒዝያ፣ በግብጽና በሊቢያ ዜጐች አምባገነን መንግስታቸውን ለማስወገድ የተጠቀሙበት የግንኙነት ቴክኖሎጂ በእጅጉ ያስፈራው የሶሪያ መንግስት፤ አመፁ ከተጀመረ ወዲህ  ሶሪያውያን ኢንተርኔትን እንዳይጠቀሙ ገደብ ጥሎ ቆይቷል፡፡ (ቴክኖሎጂ የአምባገነኖች ጠላት ሆኗል!) በቅርቡ ደግሞ በሶሪያ ምድር አይፎን መጠቀም በህግ ተከልክሏል - ከሽብርተኝነት ተለይቶ የሚታይ አይመስልም፡፡ “አልናሻራ” የተባለ የሊባኖስ ድረ ገጽ እንደዘገበው፤ አይፎን በሶሪያ የተከለከለው መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ የሚወስደውን የሃይል እርምጃ ዜጐች እየቀረፁ ለዓለም ህዝብ በማጋለጣቸው ነው - በኢንተርኔት፡፡ ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ ዓለምአቀፍ ጋዜጠኞች ከአገሪቱ የተባረሩ ቢሆንም ሶሪያውያን ራሳቸው ጋዜጠኛ ሆነው ነበር - እድሜ ለአይፎን፡፡ ለዚያ ነው መንግስት አይፎንን “ዓይንህ ላፈር” ያለው፡፡

የሚያስገርመው ደግሞ ምን መሰላችሁ? የአይፎን ፈጣሪው የስቲቭ ጆብስ ወላጅ አባት አብዱልፋታህ ጆን ጃንደሊ፤ የትውልድ አገሩ ሶሪያ መሆኗ ነው፡፡ ከሶሪያዊ አባት የተወለደው ጆብስ፤ የፈጠረው አይፎን ግን ለአምባገነኑ የሶሪያ መንግስት የኩራት ምንጭ ሊሆነው አልቻለም፡፡ (አያሳዝንም!) በአሜሪካ በስደተኝነት የሚኖሩት የጆብስ አባት በሶሪያ በሚካሄደው ህዝባዊ አብዮት በርቀትም ቢሆን እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ እየወሰደ ያለውን የሃይል እርምጃ በመቃወም ለሶሪያ ህዝብ ድጋፋቸውን በዩቲዩብ የገለፁት የጆብስ አባት፤ ዝም ማለት መንግስት በሚፈጽመው ወንጀል ከመሳተፍ እኩል ስለሆነ በዩቲዩብ በሚካሄደው የሶሪያውያን ተቃውሞ እንደሚሳተፉ በይፋ ገልፀዋል፡፡

ከሶሪያው የፖለቲካ ሥላቅ በቅርቡ ምርጫ ወደተካሄደባት ሩሲያ ስንሻገርም ሌላ የ”ፖለቲካ በፈገግታ” ገጽታ እናገኛለን - ጋዜጣ አምድ ላይ ሳይሆን በተግባር፡፡ ከጠበቁት ባነሰ ውጤት ምርጫውን ያሸነፉት የሩሲያ ጠ/ሚኒስትር ቭላድሚር ፑቲን፤ ፓርቲያቸው 49.5 በመቶ ድምጽ ብቻ ማግኘቱን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ አስገራሚ መልስ ነው የሰጡት፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ አነስተኛ ድምጽ ያገኙበት ምክንያት ከዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ፍርጥም ብለው ተናግረዋል፡፡ በነገራችን ላይ የሩሲያ ምርጫ በፑቲን ፓርቲ መጭበርበሩ ሲዘገብ የሰነበተ ሲሆን የድምጽ ስርቆቱ የተጋለጠው በዚያ የፈረደበት የስቲቭ ጆብ አይፎን እንደሆነ ታውቋል፡፡

ዕድሜ ከሰጠን ደግሞ የሩሲያ መንግስትም በመጪው ምርጫ ሩሲያውያን አይፎን እንዳይጠቀሙ ሲከለክል እንሰማ ይሆናል፡፡ (አይሆንምን ትተሽ ይሆናልን አስቢ የሚል ተረት አለ አይደለ?)

ከዚህ የበለጠ የሰው አገር ፖለቲካ ማብጠልጠል በተረት ለታገዘ ተረት ይዳረገኛል በሚል ፍራቻ በቀጥታ ወደ አገራችን ፖለቲካ ለመግባት ተገድጄአለሁ (የሶሪያ መንግስት “የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች” የሚል የተረት ሚሳዬል ቢሰነዝርብኝስ?)

እናላችሁ… ወደ ራሳችን ገበና ስንገባ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? በቅርቡ በተካሄደው ታላቁ ሩጫ ላይ መንግስትን የሚቃወም ነገር ተናግረዋል ተብለው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሯጮች ጉዳይ፡፡ አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ሯጮቹን ለምን ተቃወማችሁ ብለው ያሰሯቸው የሶሪያ ፖሊሶች ናቸው እንዴ? ግራ ገብቶኝ እኮ ነው! ኢህአዴግ ሽብርተኝነት ምንም ካልሆነ እኮ ተቃወሙኝ ብሎ ሲያስር እምብዛም አላየንማ! በተለይ ደግሞ “ንባብ ለውጥ ያመጣል” የሚል መፈክር የያዙትን እንዴት ያስራል? 17 ዓመት የታገለው ለዜጐች ነፃነት አይደለም እንዴ? ባይሆን ንባብ ምን ዓይነት ለውጥ ያመጣል ብሎ መጠየቅ የአባት ነው፡፡ ያኔ የስልጣን ሳይሆን የአስተሳሰብ ለውጥ የሚል መልስ ያገኛል፡፡ በንባብማ መንግስት አይለወጥም በምርጫ እንጂ!

መንግስትንም ሆነ ኢህአዴግን ወይም ደግሞ የትኛውንም ተቃዋሚ ፓርቲ መቃወምና መተቸት እኮ የህዝቦች ዲሞክራሲያዊ መብታቸው ሆኖ በህገመንግስቱ ከፀደቀ 20 ድፍን ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ኢህአዴግ ይሄን ጉዳይ በአስቸኳይ ካላጣራ እጀ ሰባራ ያደርገዋል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ ፖሊሶቹ ተቃውሞ ያሰሙትን ዜጐች የያዙትና ያሰሩት በዕውቀትና ግንዛቤ ማነስ ከሆነም በአፋጣኝ በህገመንግስቱ ዙሪያ ግንዛቤ የሚፈጥር ዎርክሾፕ ማዘጋጀት ብልህነት ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት እዚሁ ጋዜጣ ላይ የኢትዮጵያ ደራሲዎች ህገመንግስቱን አያውቁትም የሚል ጥናታዊ ጽሑፍን የሚተች መጣጥፍ አንብቤአለሁ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጥናታዊ ጽሑፍና ውይይት ይበልጥ የሚስፈልገውስ ዜጐች ተቃወሙ ብሎ ለሚያስር ፖሊስ ነበር፡፡

የታላቁ ሩጫ ተጠርጣሪዎች ተብለው የተዙት ተወዳዳሪዎች (የምርጫ አይደለም የሩጫ ነው) መንግስትን በሃይል ለመጣል በመሞከር ክስ ይመሰረትባቸዋል መባሉ ደግሞ ለእኔ ከ”ሽብር” ተግባር ፈጽሞ ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ ለምን መሰላችሁ? ኢህአዴግን በቋፍ ላይ ያለ መንግስት አስመስሎ የማቅረብ ድብቅ አጀንዳ ያነገበ ይመስላላ! እውነቴን ነው ያለፈውን የ2002 ምርጫ በ95 ነጥብ ምናምን ድምጽ በልዩ ማዕረግ (Great Distinction) አሸንፎ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ እንዴት ትችትና ተቃውሞ ያስበረግገዋል?

በፍፁም ሊያስበረግገው አይችልም፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ… ኢህዴግ ተቃውሞና ትችት ሲያስቦካው አይቼ አላውቅም፡፡ ኢህአዴግ በሰላማዊ መንገድ የሚካሄድ ተቃውሞ አያስፈራውም፡፡ የትጥቅ ትግል ከሆነ ግን ሌላ “ጨዋታ” ነው፡፡ (እሱም አይወደው ህገመንግስቱም አይፈቅደው) ግን ደግሞ የትጥቅ ትግልን ፈርቶ እንዳይመስላችሁ፡፡ (ጥርሱን የነቀለበት እኮ ነው!) የአገሪቱ ህግ ስለማይፈቅድ ነው፡፡

እናንተ … ድንገት ሳላስበው የአገራችን የፖለቲካ ትኩሳት ወደሆነው የሽብርተኝነት ጉዳይ ሰተት ብዬ ገባሁበት አይደል! ለነገሩ ችግር የለውም፡፡ ስለሽብርተኝነት መፃፍና መወያየት አያስጠይቅም፡፡ ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት መፍጠር ግን (የኢ-ሜይልም ሆነ የስልክ ወይም የሻይ ቡና ግንኙነትን ጨምሮ) ጣጣ ያመጣል ተብሏል፡፡ እኔ የምለው ግን ኢቴቪ ወጥዋ እንዳማረላት ሴት ሽርጉድ ሲልለት የሰነበተው “አኬልዳማ” የተሰኘውን ዶክመንታሪ ፊልም እንዴት አያችሁት? በተቃዋሚዎች ዓይን እንዳትሉኝ ብቻ፡፡ ለምን መሰላችሁ? ተቃዋሚዎች ፊልሙን “ዓይንህ ላፈር” ብለውታል፡፡

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ኢህአዴግ በሽብርተኝነት ጠርጥሮ ክስ ከመሰረተባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ጋዜጠኞች በተጨማሪ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም ከሽብርተኛ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በማገናኘት መወንጀሉ “ሽብር ሽብር ሸቶኛል” የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ፈልጐ እንደሆነ ሲናገሩ፤ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው “ችግሩ ያለው ከኢህአዴግ አፍንጫ ነው” ባይ ናቸው፡፡ (ኢህአዴግ የአፍንጫ ችግር እንዳለበት ባያምንም)

እስቲ ነገርዬዋን በኢህአዴግና በተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አንደበት እንደግፋት (የኛ አቋም እንዳትመስልብን) አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ የኢህአዴግ አመራር በቅርቡ ለግል ጋዜጣ በሰጡት ቃል እንዲህ አሉ “ተቃዋሚዎች የአሸባሪዎች ምሽግ ሆነዋል” (እውነትም ሽብር ሽብር ሸቶታል!) እርግጠኛ ነኝ እኚህ የኢህአዴግ አመራር መቼም ቢሆን ዲፕሎማት የመሆን ዕድል የላቸውም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ “አንዳንድ ተቃዋሚዎች” የሚል የትህትናና የጥንቃቄ ዓ.ነገር ቢያክሉበት ምን አለበት፡፡ (እንዲህ ዓይነቶቹ ፖለቲከኞች እኮ ናቸው ኢህአዴግን ጐል የሚከቱት!)

ወደ ተቃዋሚዎች ጐራ ስናልፍ ደግሞ የኢቴቪ “አኬልዳማ” ያለስሜ ስም ሰጥቶኛል በሚል በኢቴቪ ጉዳዩን የሚያስተባብልበት የአየር ሰዓት እንዲሰጠው ጠይቆ እምቢም እሺም ያልተባለው የ”አንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ አስራት ጣሴ፤ “መንግስት ላይ የሚነሳን ማንኛውንም ህጋዊና ሰላማዊ ተቃውሞን ለማፈን ሽብርተኝነት ዋና መገልገያ መሳሪያ ሆኗል” በማለት ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ “አኬልዳማ”ን ሟርተኛ የሚል ቅጽል ያስታጠቁት አቶ አስራት፤ “ፊልሙ ያነጣጠረው ሽብርተኝነት ላይ ሳይሆን ሰላማዊ ትግል በሚያካሂዱ የተወሰኑ ፓርቲዎች ላይ ነው” ብለዋል፡፡

ከአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተለየ “ሦስተኛ አማራጭ” በማቀንቀን የሚታወቀው ኢዴፓ ሊ/መንበር የሆኑት አቶ ሞሼ ሰሙ በበኩላቸው፤ “መንግስት በማናቸውም ሁኔታ ሽብርተኝነትን ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ማዋል የለበትም” ብለዋል፡፡ ግለሰቦችን እየከሰሱ ፓርቲዎችን ማውገዝ ተገቢ አይደለም ሲሉም የሰላ ትችት በኢህአዴግ ላይ ሰንዝረዋል - የፓርቲው ሊ/መንበር ለአንድ የግል ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት፡፡

ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን “የሽብርተኞች ምሽግ” ሲል ቢከስም ተቃዋሚዎች መልሰው ራሱ ሽብር እየፈጠረ ነው በሚል ይከሱታል (ሽብርተኛ ነው እንደማለት) እኔ በግሌ ግን ይሄ ሽብርተኛ እየተባባሉ የመፈራረጅ ጉዳይ አንድ ስጋት እንደፈጠረብኝ መተንፈስ እወዳለሁ (ስጋቱን የተናገረ የሚል ተረት አልነበረንም እንዴ?) አደራችሁን ስጋቴን “ቅዱስ ስጋት ነው” በሚል እንዳታጣጥሉብኝ፡፡ እንግዲህ ስጋቴ ምን መሰላችሁ? ይሄን እርስ በርስ በሽብርተኝነት የምንወነጃጀለውን ጉዳይ የምዕራብ አገራት ከሰሙ ጉድ እንሆናለን የሚል ነው፡፡ እንዴት ብትሉ… ለምሳሌ ኢህአዴግ በፓርላማ ሦስት የፖለቲካ ድርጅቶችን በአሸባሪነት ፈርጆአቸዋል - ኦብነግ፣ ኦነግና ግንቦት 7፡፡ ይታያችሁ … ሁሉም ደግሞ ጽ/ቤታቸው ያለው ባህር ማዶ ነው፡፡ አሁን ደግሞ እንደምንሰማው ኢህአዴግ “ሽብር ሽብር ሸቶኛል” በሚል አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች “አሸባሪ” ተብለው ከተሰየሙት የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ግንኙነት አላቸው በሚል እየወነጀለ ይገኛል፡፡ ተቃዋሚዎቹ ደግሞ ይሄን ውንጀላ ሲቃወሙ “በሌለ ነገር ሽብር እየፈጠረ ያለው ራሱ ኢህአዴግ ነው” ሲሉ በተዘዋዋሪ ኢህአዴግ “አሸባሪ ድርጅት ነው” እያሉ ይገኛሉ፡፡ ሁሉም ደግሞ ሲወነጃጀሉ በይፋ ነው - ዓለም ሁሉ እየሰማ፡፡ እናም የአሁኑ ሁኔታችን ሲገመገም የኢትዮጵያ ፓርቲዎች በሙሉ እርስ በርስ በ”ሽብርተኝነት” ተፈራርጀዋል፡፡

ይሄን ገበናችንን ምዕራባውያን በተለይ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ጠንካራ አቋም ያላት አሜሪካ አንድ ቀን ብትሰማ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስቡት፡፡ የፀረ-ሽብርተኝነት አጋሮቿን ሰብስባ ወደ አገራችን ፊቷን ብታዞርስ የሚል ነው ስጋቴ - በ”አሸባሪነት” ጠርጥራን፡፡ ደግሞም ሊፈረድባት አይችልም፡፡ በኢትዮጵያ ምድር የተፈጠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ “ሽብርተኛ” እንደሆኑ እርስ በርስ እየተመሰካከሩ እያየች እንዴት ላትጠራጠረን ትችላለች፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎች ቢቻል “አሸባሪ” እየተባባላችሁ አትወነጃጀሉ፡፡ መወነጃጀሉና መካሰሱ ደግሞ የግድ ከሆነ እባካችሁ ድምፃችሁን ዝቅ አድርጋችሁ ተወነጃጀሉ፡፡ (እነ አሜሪካ እንዳይሰሙ) ቢሰሙስ ምን ያመጣሉ የሚል አጉል መታበይ ብዙም የሚጠቅመን አይመስለኝም፡፡ በፓርቲዎች ጦስ ሙሉዋ ኢትዮጵያ በ”አሸባሪነት” ከተፈረጀች አገሪቱ ምድር ላይ አንድም የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይበቅል ህዝቡ አድማ ከመምታት የሚመለስ አይመስለኝም፡፡ እናም “አሸባሪ” ከመባባላችሁ በፊት ቆም ብላችሁ አስቡ፡፡ ማሰብ ካቃታችሁ ደግሞ “አሸባሪ” የሚለውን ቃል የሚተካ ለዘብ ያለ ቃል ፈልጉለት ለምሳሌ ሁከት ፈጣሪ፤ ረባሽ፤ ጭር ሲል አልወድም፤ ወዘተ፡፡ ይሄን ሁሉ መዘባረቄ ከጭንቀት የተነሳ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደምትረዱልኝና ምክሬን እንደምትቀበሉኝ እተማመናለሁ፡፡ የሰላምና የፍቅር ዘመን ለፓርቲዎቻችን እመኛለሁ፡፡

 

 

Read 2393 times Last modified on Saturday, 17 December 2011 09:59

Latest from