Saturday, 24 May 2014 15:04

አስቴር አወቀና ጃኪ ጎሲ ለሙዚቃ ሽልማት ታጩ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

አድናቂዎች ለዕጩዎቹ ድምጽ መስጠት ይችላሉ

ኢትዮጵያውያኑ ድምጻውያን አስቴር አወቀና ጃኪ ጎሲ፣ “አፍሪካን ሚዩዚክ ማጋዚን አዋርድስ” (አፍሪማ) ለተባለው ታላቅ አህጉራዊ የሙዚቃ ሽልማት በተለያዩ ዘርፎች በእጩነት ቀረቡ፡፡
አፍሪማ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የ2014 ሽልማት እጩዎች ዝርዝር ላይ እንደተጠቀሰው፣ ድምጻዊት አስቴር አወቀ በ“ምርጥ የምስራቅ አፍሪካ ሴት ድምጻዊት”፣ ጃኪ ጎሲ ደግሞ በ“ምርጥ የምስራቅ አፍሪካ ወንድ ድምጻዊ” ዘርፍ በእጩነት የቀረቡ ሲሆን፣ የሌሎች የአፍሪካ አገራት ድምጻውያን፣ የሙዚቃ ቡድኖች፣ ማኔጀሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ ፕሮዱዩሰሮች፣ ዲጄዎች፣ የዳንስ ቡድኖችና የሙዚቃ ቪዲዮዎችም በተለያዩ 26 ዘርፎች ለሽልማት ታጭተዋል፡፡
አስቴር አወቀ በታጨችበት የ“ምርጥ የምስራቅ አፍሪካ ሴት ድምጻዊት” ዘርፍ፣ ሌሎች ሁለት የኡጋንዳ፣ ሁለት የኬኒያና አንድ የታንዛኒያ ታዋቂ ድምጻውያን በእጩነት የቀረቡ ሲሆን፤ ጃኪ ጎሲ በቀረበበት የ“ምርጥ የምስራቅ አፍሪካ ወንድ ድምጻዊ” ዘርፍ ደግሞ፣ ሌሎች ሁለት የታንዛኒያ፣ ሁለት የኡጋንዳና አንድ የኬኒያ ድምጻውያን በእጩነት ቀርበዋል፡፡
አድናቂዎች http://afrimma.com/afrimma-nominees-2014/ በሚለው የድረ-ገጽ አድራሻ በመጠቀም ለሚፈልጓቸው እጩ ድምጻውያን፣ የሙዚቃ ቡድኖችና ሌሎች እጩዎች ድምጻቸውን በመስጠት፣ አሸናፊ እንዲሆኑ የራሳቸውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ የሽልማቱ አዘጋጆች ተናግረዋል።
በመጪው ሃምሌ ወር አጋማሽ በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት፣ ሪቻርድሰን ውስጥ በሚከናወነው የሽልማት ስነስርዓት ላይ፣ በአለማቀፍ ደረጃ እውቅናን ያተረፉ የተመረጡ አፍሪካውያን ድምጻውያን፣ ማኔጀሮች፣ ፕሮዲዩሰሮች፣ ዲጄዎች፣ ባህላዊ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በክብር ይሸለማሉ ተብሏል፡፡ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የተጋበዙና ከ17 የአፍሪካ አገራት በክብር እንግድነት ተጋብዘው የሚመጡ ታላላቅ ጀግኖች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የአፍሪካን ሙዚቃ የማስተዋወቅ አላማ ያለውና በየአመቱ በሚከናወን ደማቅ ስነስርኣት ለአሸናፊዎች የሚበረከተው ይህ ሽልማት፤ በዘርፉ ከሚሰጡ ታላላቅ አህጉራዊ ሽልማቶች አንዱ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ድምጻውያንና የሙዚቃ ቡድኖች ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡበትና በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ለእይታ የሚበቃውን የዘንድሮውን የአፍሪማ የሙዚቃ ሽልማት ስነስርዓት ስፖንሰር ያደረጉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ፓዎር ሃውስ ኢንተርናሽናል ኤርላይንና አክሴስ የተባለው የአሜሪካ ሶፍትዌር አምራች ኩባንያ መሆናቸውንም የሽልማት ድርጅቱ መስራች አንደርሰን ኦቢያጉ በድረ-ገጻቸው ላይ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

Read 6980 times