Saturday, 24 May 2014 15:07

የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ታሪካዊ ኤግዚቢሽን ነገ ይከፈታል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለሥሴ ህይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን

“RasTafari፡ The Majesty and the Movement` በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ታሪካዊ ኤግዚብሽን ነገ በብሔራዊ ሙዚየም ይከፈታል፡፡
ኤግዚቢሽኑ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በስልጣን ዘመናቸው ያበረከቷቸውን መልካም ተግባራት የሚዘክር ሲሆን፣ በፓን አፍሪካኒዝም ፅንሰ ሀሳብና በአፍሪካ የነፃነት እንቅስቃሴ ውስጥ ኢትዮጵያ የነበራትን ሁለንተናዊ አስተዋጽኦም ይዳስሳል ተብሏል፡፡ የአፍሪካ ጥቁር ህዝቦች፣ ቅኝ አገዛዝን ለመገርሰስ ስላደረጉት እልህ አስጨራሽ የነፃነት ትግልና አፍሪካውያን ወደ ትውልድ ምድራቸው ለመመለስ ያለፉባቸውን አስቸጋሪ ጉዞዎችም የሚቃኙበት እንደሚሆንም አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡
በኤግዚቢሽኑ ላይ ከሚቀርቡት የስዕል ሥራዎች መካከል በሰዓሊ ገ/ክርስቶስ ደስታ የተሰራው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ምስልና በዕምአላፍ ህሩይ የተሳለው የእቴጌ መነን ምስል ተጠቃሽ ሲሆኑ  የአትላንቲክ የባርያ ንግድን የሚያሳዩ በርካታ ስዕሎች እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡
በፎቶግራፍ የኤግዚቢሽኑ ክፍልም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴና እና የጋናው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማን፤ የቀዳማዊ ሐይለስላሴ የጃማይካ ጉብኝት እንዲሁም የማርክስ ጋርቬይና የቦብ ማርሌይ ስራዎችን የሚያስታውሱ ምስሎች ይቀርባሉ፡፡  በ12 ምዕራፍ የተከፋፈለው ኤግዚቢሽኑ፤ ፊልሞችም የሚቀርቡበት ሲሆን የንጉሰ ነገስቱ ንብረት የነበሩ ቁሳቁሶችና ሌሎች ታሪካዊ ቅርሶች ለህዝብ ይታዩበታል ተብሏል፡፡
ኤግዚቢሽኑ ለአንድ ወር ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን ከብሔራዊ ሙዚየም በተጨማሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የሚቀርብ ዝግጅት እንደሚኖረው ታውቋል፡፡ የፊታችን ረቡዕ ደግሞ ተመሳሳይ ኤግዚብሽን በሻሸመኔ በሚገኘው ሊሊ ኦፍ ዘ ቫሊ ሆቴል እንደሚከፈት ታውቋል፡፡ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ኤግዚቢሽን ያዘጋጁት የራስ ተፈሪያን ማህበረሰብ አባላት ሲሆኑ ላለፉት 4 ዓመታት በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣ በጃማይካና በሜክሲኮ ከፍተኛ ዝግጅት ሲደረግ እንደቆየ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 1388 times