Saturday, 24 May 2014 15:14

በእርግዝና ወቅት ያልተለመደ በማህፀን ላይ የሚደርስ አደጋ (uterine Prolapse)

Written by  አበበ ተሻገር abepsy@yahoo.com
Rate this item
(2 votes)

አንድ
የህመምተኛዋ የኋላ ታሪክ
ያገባችው በ14 ዓመቷ ሲሆን የመጀመሪያ ልጇን በ15 ዓመቷ ወለደች፡፡ በአጠቃላይ ዘጠኝ የእርግዝና ጊዜዎች ነበሯት፤ ከእነዚህ እርግዝናዎች ውስጥ የመጀመሪዎቹ  አራት ልጆች በህይወት ተወለዱ፣ በአምስተኛ ግን ውርጃ አጋጠማት፡፡ የስድስተኛው እርግዝና ቀጠለ በዚህ ጊዜ በህክምና በጣም አልፎ አልፎ የሚያጋጥም ክስተት በዚች እናት ላይ ተከሰተ፣ ፅንሱን የተሸከመው ማህፀን አብሮ የመውጣት አጋጣሚ ተከሰተ (uterine prolapse)፡፡  በወቅቱ ለእናትም ይሁን በቅርብ ላሉ ሰዎች አስደንጋጭ ቢመስልም ከሌሎች ሶስት አመታት በኋላ ይችው እናት ሶስት ጊዜ እርግዝና ተከስቶ በተመሳሳይ የማህፀን መውጣት ችግር ፅንሶቹ ሁሉ በውርጃ ተጠናቀዋል፡፡ የሁሉም የፅንስ ማቋረጥ አጋጣሚዎች የተከሰቱት በመጀመሪያዎቹ ሶስት የእርግዝና ወራት ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ ይች እናትም ሆነች ባለቤቷ ምንም አይነት የእርግዝና መከላከያ መንገዶችን ተጠቅመው አያውቁም፡፡ ቀጥሎ (ከምታነቡት የመጨረሻና ዘጠነኛው እርግዝና በፊት ሃኪም ቤት ጎብኝታ ወይም ሃኪም አይቷት አያቅም፡፡ የት ነው የምትኖረው…….? በኔፓል አንዲት የገጠር መንደር ውስጥ፡፡ በቻይና፣ በህንድ፣ በባንግላዲሽና በቡሁታን መሃከል ላይ እነዚህን ሀገራት ተዋስና የምትገኝ የኤዥያ ሀገር ነች፡፡
በህክምና ተቋም ውስጥ ምን ተደረገላት?
እናት ሃኪም ቤት ስትደርስ እኩለ ለሊት አልፏል (መቼም በሽታም በሉት ምጥ ለሊት ላይ የሚከሰተውና የሚባባስበት ነገር አለው፡፡ እሱም ክፋት ሆኖበት ሰውም፣ ትራንስፖርትም፣ ስራም አገልግሎትም የሌለበትን ሁሌታ ይመርጣል ልበል?) እናት ስትደርስ ላብራቶሪውም፣ መድሃኒት ቤቱም ተዘግቷል፤ የደሟን አይነት (blood group) ለመለየት እንኳን ባለሞያዎቹ የተሟላ መሳሪያ አላገኙም-ለሁሉም እስኪነጋ መጠበቅ ሊኖርባቸው ነው፡፡ የተረገዘው ልጅ እግሩ ይታያል፡፡ ከዚህ በፊት እንዳጋጠማትና እንደተለመደው የእናት ማህፀን አብሮ ዘልቋል፡፡
የማህፀን በር (የልጁ እግር በዘለቀበት በኩል) ቁስለት (decubitus ulcer) ያሳያል፡፡ ባሙያዎቹ ምንም አይነት ከፍ ያለ አደጋን የመከላከል እርምጃ ከመውሰድ የተሻለና የመረጡት በአቅራቢያ ወደሚገኝ ሆስፒታል በፍጥነት መላክን ነበር፡፡ ለዚህ የጤና ተቋም በቅርበት የሚገኘው ሆስፒታል ደግሞ በ200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህ ደግሞ በአይሮፕላን ካልሆነ በመኪና የሚታሰብ አልነበረም፤ ወደ ቦታው ለመድረስ የመኪና መንገድ የለምና። ሃኪሞቹ ለመንገድ የሚያግዛት መጠነኛ እርዳታ ካደረጉላት በኋላ ከአዋላጅ ነርስ ጋር አቆራኝተው በ200 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደሚገኝ ሆስፒታል እድትሄድ ወሰኑ፡፡ ሆኖም በረራ የሚጀምረው ንጋት ላይ ሆነ፡፡ አይነጋ የለም ነጋ- ሲነጋ ቲኬት ተቆርጦ ለመሳፈር በተዘጋጀችበት የመጨረሻ ቦታ (boarding) ላይ ምጡ ተባብሶ በነርሷ እርዳታ ወለደች፡፡  ህፃኑ ሶስት ኪሎ ከ200 ግራም ይመዝናል፡፤ ወደ አየር ማረፊያና መነሻው በሄደችበት ሁኔታ መጀመሪያ ወደ ታየችበት ሆስፒታል እንድትመለስ ተደረገ፡፡
የባሙያዎች ቀጣይ ስራ ለማህፀን ቁስለት መፍትሄ መሻት ነበር፡፡
ለተከታታ አስር ቀናት ህክምናው በሆስፒታሉ ውስጥ ሲደረግላት ቆየች፡፡ ሆኖም ይች እናት ከዘጠነኛው እርግዝና አደጋ በኋላ የእርግዝና አጋጣሚ እንዳይኖራት ለባለቤቷ ሰፊ ምክር በመስጠት የእርግዝና መከላከያው ለሱ እንዲሰጥ ተጠየቀ ለዚህም ፈቃደኛ ሆነ፡፡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ባል የዘር መተላለፊያ ቱቦ እንዲቋረጥ ወይም እንዲዘጋ ተደረገ፡፡
በመጨረሻም ፀሃፊው መደምደም ሲፈልግ
ክስተቱ ያልተለመደና በጣም አልፎ አልፎ የሚታይ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ከ1988 እ.ኤ.አ ጀምሮ እስከ 2008 ባለው ጊዜ በተመዘገበ መረጃ ከደርዘን ባልበለጡ እናቶች ላይ ተመሳሳይ ሁኔታ መከሰቱን ያወሳል፡፡ ብዙ ጊዜ የህክምና ክትትል በሚያደርጉ፣ ተከታታይ እርግዝና ባለበት፣ ያለ ባለሙያዎች እገዛ በሰፈርና በቤታቸው ውስጥ አምጠው በሚወልዱ፣ የተመጣጠነ ምግብ በእርግዝና ወቅት አለማግኘትና ከወሊድ በኋላ እናቶች የማህፀናቸው መጠን ወደነበረበት ሁኔታ እስኪመለስ በቂ የእረፍት ጊዜ አለማግኘት ቀደም ሲል የተመለከትናትን እናት አይነት አጋጣሚ ሊከሰቱ የሚችሉባቸው ምክንያቶች ናቸው፡፡ ከተጠቀሱት ምክንያቶች በላይ ደግሞ በተለይ ማህፀን ወደ ማህፀን በር ማፈግፈግና በብልት የመውጣት አጋጣሚ ያለ እድሜ ጋብቻና ያለ እድሜ በሚወልዱ ህፃናት ላይ ሊከሰት የሚችል ችግር ነው ይላል። ምንጫችን ሬፕሮዳክቲቭ ኅልዝ ማተርስ የተሰኘው ጆርናል ነው፡፡
ሁለት
ህፃናት ከቀን ይልቅ ለሊት ለምን የበለጠ ያለቅሳሉ?
ከተወለዱ እስከ ስድስተኛው ወራት አብዛኞቹ ህፃናት (66 በመቶ የሚሆኑት ለሊት በሳምንት ሁለቴ ሊነቁና ሊያለቅሱ ቢችሉም ቀሪዎቹ (33 በመቶ የሚሆኑት) ግን በሳምንት ከ10 ጊዜ በላይ ከእንቅልፋቸው ሊነቁና ሊያለቅሱ ይችላሉ፡፡ መቼም በርካታ ወላጆች ቀን በአድካሚ ስራ ላይ ውለው እንደገና ለሊት በህፃን ልጃቸው አማካኝነት ሌላ ስራ ውስጥ የሚጠመዱበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ልጆቻቸውን አባብለው ካስተኙ በኋላ እነሱ እንደገና ወደ እንቅልፍ መመለስ የሚያቅታቸው ወላጆችም ይኖራሉ። በስንት መገላበጥ፣ ታሽተው….ታሽተው ሸለብ ማድረግ ሲጀምሩ ህፃኑ እንደገና ለቅሶ ያሰማል፡፡
ይናደዱ ይሆን ወይስ ያዝኑ? ከዚህም በሚብስ ሁኔታ ህፃናቱ ፈፅሞ መተኛት አቅቷቸው ለሊቱ ከቀኑ ጋር ሊገጥምም ይችላል፡፡ አንዳንድ ወላጆች የሚያግዝ ዘመድ፣ አያት ወይም ሞግዚት ይኖራቸዋል፡፡ ብዙ ባሎች ይህ ጉዳይ የእነሱም ጉዳይ እስከማይመስል ድረስ ጧ-ብለው ተኝተው የሚያንኮራፉ ባይጠፉም ከሚስታቸው ጋር ተራ የሚገቡ ባሎች መኖቸውም አይካድም፡፡
እውነታው ህፃናት ከተወላዱ ጀምሮ ያሉት ቀጣይ ሶስት ወራት የመጨረሻው የእርግዝና ጊዜ (fourth trimester) ተብሎ ይወሰዳ፡፡ ማህፀን ለፅንሱ የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ያለበትና መዋኛ ገንዳ አይነት ነው፡ ከተወለዱም በኋላ ታዲያ እንቅስታሴ፣ ምቾት፣ ሰላም ይፈልጋሉ፡፡
ህፃናት ከተወላዱ ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ወራት ማንኛውንም ስሜታቸውን የመቆጣጠር ወይም እኛ በምንፈልገው መንገድ መመራት አይችሉም፡፡ ሆኖም ወራቶች እየጨመሩ ሲሄዱ ስሜታቸው እየሰከነ ወይም መስመር እየተከተለ መሄድ ይቀጥላል፡፡ የስሜት ጉዳይ አንዱ ይሁን እንጂ ህፃናት እራቧቸው፣ ታመው፣ የለበሱት ልብስ ወይም የተደረገላቸው የሽንት ጨርቅ (ናፒ/ዳይፐር) ምቾት ነስቷቸው፣ ተባይ በልቷቸው፣ ሙቀት ወይም ብርድ ተሰምቷቸው፣ ወዘተ ሊያለቅሱ ይችላሉ፡፡ ብዙ ጊዜም ባይሆን አንዳንዴ የወላጆቻቸውን (የአሳዳጊዎቻቸውን) እቅፍ፣ የሰውነት ንክኪ ወይም ትንፋሽ ፈልገው ሊያለቅሱ ይችላሉ፡፡ ይህ የሚፈጥርላቸው የደህንነት (security) ስሜት ስላለ ነው፡፡ ህፃናት ምክንያት የሌለው ለቅሶ ባይኖራቸውም ወላጅ ምክንያቱን ልብ ለልብ ተናቦ ወይም የልጆቹን ቋንቋና ስሜት ተረድቶ መለየት ሊያቅተው ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ተፈጥሮ በምትመራው መንገድ ህፃናት የሚያመላክቱትን ምልክት ተከትሎ ለማረጋጋት መሞከር፣ ማባበልና ዝማሬ ወይ እ ሹ ሩ ሩ ማሰማት፣ ማጥባት፣ መዳሰስና መነካካት(መደባበስ) አይናቸው ተገልጦ ከሆነ አይናቸውን በፍቅር ማየት የተሻሉና ልጆችን ወደ እንቅልፍ ለመመለስ የሚጠቀሱ ዘዴዎች ናቸው፡፡
ሆኖም በማንኛውም ሁኔታ ማልቀስ የጀመሩ ልጆችን “ሲደክመው ይተኛል” በሚል መተው የሚመረጥ መፍትሄ አይደለም፡፡ ልጆች በሚያለቅሱበት ጊዜ ቀርቦ መደባበስ፣ ማቀፍ፣ ማጥባት፣ ወዘተ ለጊዜው ወደ እንቅልፋቸው ለመመለስ ብቻ ሳይሆን በሚረበሹበት፣ አቅላቸውን በሚጠባቸው (distress) ጊዜ ራሳቸውን እንዴት ከሚያጣብብ ስሜት እደሚያወጡ እየተማሩ ይሄዳሉ። ለምሳሌ ጡጦ ካጠገባቸው ካለ ጡጦውን ጠብተው ይተኛሉ (እንቅልፍ ላይ ሆነው መጥባት ግን አይመረጥም) ሌሎች ደግሞ ከእናታቸው የሰሙትን እንጉርጉሮ መሰል ነገር እያዜሙ ሊተኙ ይችላሉ፡፡ እንዲያለቅሱ ባሉበት ከተተዉ ግን ደክሟቸው ቢተኙም ስሜትን የማስታመም ክህሎትን ግን አይማሩም፡፡
የሆነ ሆኖ የህፃናት እንቅልፍ ከቀን ይልቅ ለሊት ላይ ለምን ይቀሰቀሳል ለምን ይበዛል? ይህ ቀደም ሲል ከጠቅስናቸው ምክንያቶች በአንዱና ከአንድ በላይ በሆኑ ምቾትን ከሚያውኩ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ቢሆንም አንድ ሌላ መሰረታዊ ምክንያትም ይጠቀሳል፤ ህፃናቱ ከወላጅ (አሳዳጊ) ጋር ባላቸው ቀረቤታና ትስስር ጋር በተያያዘ በተለይ ከአንድ ሰው ጋር (ከእናት፣ አባት፣ ምግዚት፣ አያት….) ቁርኝት /attachment/ይፈጥሉ፡፡ ይህም ለምሳሌ ቁርኝቱ ከእናት ጋር ቢሆን እናት ባለችበት ሁሉ ህፃኑ ደህንነት ይሰማዋል፡፡ ይች እናት ደግሞ ቀን ስራ የምትውል ከሆነ በቀሪው ጊዜ (ለሊት ላይ) ህፃናቱ ስሜታቸውን የበለጠ ትስስር ላለቸው ሰው ይገልፃሉ፤ ያንፀባርቃሉ፣ ያሰማሉ፡፡
ከዚህ በተረፈ ለሊት ላይ የህፃናት መንቃት ጤናማ ያልሆነ ክስተት አይደለም፤ እስከ ስድስትና 12 ወራት ድረስ የተለመደ ነው፡፡ በሌላ በኩል ህፃናት ራሳቸውን የሚከላከሉት በማልቀስ ነው፡፡ ሲታፈኑ ያቅሳሉ፣ ሲያማቸው ያቅሳሉ፣ ወዘተ እንዲያውም ቶሎ ከእንቅልፍ የሚነቁ ልጆች ታፍኖ ከመሞት አደጋዎች ራሳቸውን ታደጋሉ፡፡



=

Read 6183 times