Saturday, 24 May 2014 15:20

ከ20 ዓመት በታች ደቡብ አፍሪካ 2 ኢትዮጵያ 0

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

     በ2015 በሴኔጋል ለሚካሄደው 19ኛው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ አንድ ዙር የማጣርያ ምእራፍ ይቀራል፡፡ ወደዚሁ የመጨረሻ የማጣርያ ምእራፍ ለመሸጋገር ደግሞ የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ነገ ከደቡብ አፍሪካ አቻው ከሜዳው ውጭ በመልስ ጨዋታ  ይገናኛል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ስታድዬም በተካሄደው ጨዋታ የደቡብ አፍሪካ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን   2ለ0 ከሜዳው ውጭ በማሸነፍ የማለፍ እድሉን አስፍቷል፡፡ በነገው የመልስ ግጥሚያ ከሜዳው ውጭ የሚጫወተው የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ወደ ቀጣዩ የማጣርያ ምእራፍ ለመሸጋገር በ3 ንፁህ ጎሎች ማሸነፍ ይጠበቅበታል። የመልሱን ጨዋታ ጌታነህ ከበደ የሚገኝበት የደቡብ አፍሪካው ክለብ ቢድቬስት ዊትስ ስታድዬም ያስተናግደዋል፡፡ ከሁለቱ ቡድኖች ጥሎ የሚያልፈው በ3ኛው ዙር የመጨረሻ ማጣርያ  ከካሜሮን ጋር ለደርሶ መልስ ትንቅንቅ ይደርሳል፡፡ በተያያዘ የወጣት ቡድኑን ተከላካይ መስመር ለማጠናከር ያሰበው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዋናው ብሄራዊ ቡድን የነበሩትን ሳልሀዲን በርጌቾ እና ቶክ ጀምስ ጠርቶ ነበር፡፡ ይሁንና የአፍሪካ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ይህን አካሄድ  ውድቅ አድርጎታል፡፡ ካፍ ለእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በላከው ደብዳቤ ሁለቱ የተጨዋቾች  ከጨዋታው አስር ቀናት በፊት ባለመመዝገባቸው ደቡብ አፍሪካን በሚገጥመው ቡድኑ ውስጥ መካተት እንደማይችሉ አስታውቋል፡፡

Read 1280 times