Saturday, 31 May 2014 14:09

የወንዶች የዘር መተላለፊያ ቱቦ ከተዘጋ በኋላ /vasectomy/ ወደነበረበት ሁኔታ መመለስ ይቻላል

Written by  አበበ ተሻገር abepsy@yahoo.com
Rate this item
(1 Vote)

በወሲባዊ ግንኙነት ጊዜ ከወንድ ልጅ የሚመነጨው ፈሳሽ/ semen/ የሚነሳው ከአንድ ቦታ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ አንድ በመቶ የሚሆነው እርግዝና እንዲፈጠር የሚያስችለው ፈሳሽ /sperm/ ከብልት ሁለት ፍሬዎች ውስጥ መንጭቶ ከዛው ላይ በሚነሳ እጅግ ቀጭን ቱቦ አማካኝነት በማለፍ ወደ ዋናው ቱቦ በመድርስ ከቀሪው 99 በመቶ ከሚሆነው ፈሳሽ ጋር ተቀላቅሎ ይጓዛል፡፡ ዘር እንዲፈጠር ምክንያት የምትሆነውም አንድ በመቶ የሆነችው የዘር ህዋስን/cell/ የተሸከመችው ፈሳሽ ብቻ ነች፡፡ ሌላው ፈሳሽ ይች ህዋስ በቀላሉ ወደ ሴቷ የዘር እንቁላል እንድትደርስ የሚያጓጉዝ፣ ሁኔታውን የሚያፋጥን፣ ለህዋሷ የሚፈጥር ፈሳሽ ነው፡፡ ታዲያ እርግዝናን በወንዶች በኩል ለመከላከል የሚሰራው የወንድ ዘር ማስተላለፊያ ቱቦ የመዝጋት ስራ የሚሰራው ይችን አንድ በመቶ የሚያጓጉዝ ቱቦ / Vas deference /ጠልፎ በመዝጋት /vasectomy/ ወይም በማቋረጥ ሂደቱን መግታት ነው፡፡
በአጠቃላይ ከምናውቃቸውና ሳይንስ ከፈጠራቸው የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዶች ውስጥ በሃገራችን ብዙ የማይታወቀውና በአገልግሎቱም በመጠነኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የወንድ ዘር መተላለፊያ ቱቦን ማገድ/vasectomy/ ዘዴ ነው፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ 43 ሚሊዮን የሚሆኑ ጥንዶች የዚህ ወሊድ መቆጣጠሪያ ተጠቃሚ ቢሆኑም 77 በመቶ የሚሆኑት የሚገኙት በእስያ ሲሆን፤ ከእነዚህም 70 በመቶዎቹ በቻይናና ህንድ ይገኛሉ፡፡
ይህን የቤተሰብ አገልግሎት እቅድ በለመለከተ ትንታኔ እንዲሰጡኝ እንግዳ ጠርቻለሁ፡፡ እንግዳዬ በተለይ በሃገራችን በመንግስት ጤና ተቋማት ውስጥ ዘላቂ የሆነውን የወንዶች የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገድ የሆነውን የዘር መተላለፊያ ቱቦ መዝጋትን በተመለከተ ሞያዊ እገዛና ስልጠና በሚሰጥ ኢንጀንደር ኅልዝ/Engender Health / በተሰኘ ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ የጤና አማካሪ ናቸው፡፡ ዶ/ር ደረጀ ንጉሴ የማህጸንና ፅንስ ስፔሻሊስት ሃኪምና የኢሶግ/Ethiopian Society of Obstetrician and Gynecologist / ፕሬዚዳንትም ናቸው፡፡
ዶ/ር ደረጀ ንጉሴ
የማህጸንና ፅንስ ስፔሻሊስት ሃኪም፣በኢንጀንደር ኅልዝ ኢትዮጵያ/Engender Health / ከፍተኛ የጤና አማካሪና  የኢሶግ/Ethiopian Society of Obstetrician and Gynecologist / ፕሬዚዳንት

እኔ ቀድሜ ያነሳሁላቸው ጥያቄ አልፎ አልፎ ከዘልማድ በመነሳት በሚሰሙ ጉዳዮች በማንሳት ነው። የወንድ ዘር ፈሳሽ መተላለፊያ ቱቦን መዝጋት ( vaslotomy) ከወሲባዊ እርካታ ከወሲባዊ ፍላጎትና ብቃት ጋር የሚያያዝ ጉዳይ አለ ወይ አልኳቸው።“ፈጽሞ ከእነኚህ ጉዳዮች ጋር አይያያዝም። የሚታገደው ቱቦ የዘር ፈሳሽን የሚያጓጉዘው ብቻ ነው። በተረፈ ሌሎች የሚመነጩ ፈሳሾች (testestrone)የሚሄዱት በደም ስር አማካኝነት  ነው። ይህ ደግሞ አይነካም። ግንኙነት በሚደረግበት ጊዜ የፈሳሹ መጠን፣ ቀለምና ማንኛውም ነገር በነበረበት ይሄዳል፣ይቀጥላል እንደተጠበቀ ነው። ሄኖም ማስረገዝ የሚችለው አንድ በመቶ የሚሆነው ህዋስ (spermatolzo) እሱ አይኖርም፡፡ ስለዚህ የወሲባዊ ፍላጎት፣እርካታ፣ወንድነትን የሚገልፁ ሌሎች ጉዳዮች ሁሉ እንደተጠበቁ ይቀጥላሉ” ።


ሀኪሞቹ የተሳሳተ ግንዛቤን (misconception) አንዴ ወደራሳችን ካስገባን በኋላ ያንን ግንዛቤ በቀላል ልንነቅለው ይከብዳል ይላሉ። እውነታው እንዲህ ምንም ያህል የጎላ ቢሆንም በሌሎች ሰዎች ተሞክሮ፣ በአይናችን አይተን፣ ውጤቱን ተረድተን ክልሆነ የተሳሳተውን ግንዛቤ ለራሳችን እውነት ነው ብለን ተቀብ እንኖራለን። ወሊድን መቆጣጠር የጋራ (የባልና ሚስት)ሃላፊነት ሆኖ እያለ ለብዙ ዘመናት ወንዶች ሀላፊነቱን ሴቶች ላይ ጥለው ይኖራሉ(እንኖራለን)፡፡
ይህን የዘር መተላለፊያ ቱቦ በሚያዘጋ አንድ ሰው ላይ የሚከሰቱ የጎን ጠንቆች ምንድን ናቸው ስል ዶ/ር ደረጀ ንግግራቸውን ቀጠሉ
“ይኸውልህ ሁለት ነገሮችን እናነፃፅር ለወንዶችም ይሁን ለሴቶች ወሊድን ለመቆጣጠር ሲባል የሚሰሩ ዘለቄታዊ የመቆጣጠሪያ መንገዶች አሉ። ለሴቶች የሚሰራው ሆድ ተቀዶ ነው። ይህም በአንፃራዊ ጊዜ ይወስዳል። ረዘም ላለ ጊዜ ህመም ይኖራል። የተወሰኑ ድህረ ህክምና ህመሞች(complications) ይኖራሉ፣መቀደድና መሰፋት አለ። ለወንዶች በሚሰራው የወሊድ መቆጣጠሪያ የዘር ቱቦን የመዝጋት ዘዴ  /vasectomy/ የሚቀደድና የሚሰፋ ነገር የለም፣ ከአስራ አምስት እስከ ሃያ ደቂቃ ብቻ የሚወስድ ስራና የሁለት ቀን እረፍት ብቻ የሚጠይቅ ሲሆን ከሁለት ቀናት በኋላ ወደ እለታዊ ተግባር መመለስ ይቻላል፣ በቀላሉ የሚሰራ ብዙ ውጣ ውረድ የሌለበት፣ የጎን ጠንቅ ያልበዛበት ነው፡፡ ወሲባዊ ግንኙነትን በተመለከተ ግን ስራው ከተሰራ ጀምሮ ለሶስት ወራት ጥንዶቹ ሌሎች የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዶችን መጠቀም ይኖርባቸዋል፣ ይህን የዘር መተላለፊያ ቱቦ ማዘጋትን የሚያሰራ ሰው አንዴ ወስኖ ከተሰራ በኋላ በእኛ ሀገር አሁን ባለ ህክምና ደረጃ ወደነበረበት መመለስና ግለሰቡ መውለድ ቢፈልግ እንዲወልድ ማድረግ አይቻልም”
በእኛ ሃገር አይቻልም ማለት በሌሎችም አይቻልም ማለት ነው? የእኔ ጥያቄ ቀጠለ፣ ዶ/ር ደረጀም “ ያን ማለት አይደለም፡፡ በእኛ ሀገር መሳሪያውና ስልጠናው ስለሌለ እንጅ በሌሎች ሃገራት ተሞክሮ 90 በመቶ በሚሆን ደረጃ የተሳካ ውጤት ማየት ተችሏል”፡፡
ከዚህ ይልቅ አልኳቸው እንደ ሴቶቹ ሁሉ የሚዋጡ ወይም በመርፌ የሚሰጡ የወሊድ መከላከያ መንገዶች ለወንዶችም መፍጠር አልተቻለም ማልት ነው? በጣም ጥናት የተደረገባቸውና ሙከራዎች ተጀምረውባቸው የነበሩ ዘዴዎች ነበሩ፤ ይሁንና ወንዶች የመድሃኒቶቹን የጎን ጠንቆች ተቅጣጥሮ ጥናቱን አስፈላጊ እስከሆነው  ጊዜ ማስቀጠል አልተቻለም፡፡ በዚህ ረገድ በእርግጥ ወንዶችም የሴቶችን ያህል ኃላፊነት ወስደው ሙከራዎቹን ማስቀጠል ቢችሉ ሙከራዎቹ አንደ ቦታ ላይ ውጤት ያመጣሉ፡፡ ለሙከራ ሙከራ ጣቢያዎች የገቡ ወንዶች መድሃኒቶቹን መውሰድ ከጀመሩ በኋላ በተለያዩ ከጎን ጠንቆች ጋር በተያያዘ እስከ መጨረሻ መዝለቅ አልቻሉም፡፡ ሴቶች ለረዥም ዘመናት ህመሙን፣ችግሩን፣ የጎን ጠንቆቹን ሁሉ ታግሰው እየወሰዱ ነው የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዶች አሁን ከደረሱበት የእድገት ደረጃ መድረስ የተቻለው፡፡ በተመራማሪዎችና ለሙከራዎቹ ፈቃደኛ በሆኑ ግለሰቦች መሃከል አሁንም ትብብሩ ከቀጠለ ጥናቶቹ ውጤት ላይ መድረሳቸው አይቀርም፡፡ ያም ሆነ ይህ አሁን ወንዶችን በተመለከተ አገልግሎት ላይ ያለውን የዘር መተላለፊያ መስመርን ወይም ቱቦን በማዘጋት ወሊድን መቆጣጠር ላይ ወንዶች የሴቶችን ችግር ከመጋራት፣ ከማበረታታትና ከመደገፍ አልፎ ኃላፊነት በመውሰድ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎቱን መጠቀም ይኖርባቸዋል”
እውነትም ልብ ብለን ስንመለከተው ሴቶች ስለበርካቶቹ የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዶች የጎን ጠንቆች ሲያነሱና አንዳንዶቹም ሲያማርሩ ይሰማሉ፡፡ በጣም አልፎ አልፎ ቢሆንም አንዳንዶቹ ፈፅሞ የሚስማማቸው የወሊድ መከላከያ መንገድ ያጣሉ፡፡ አንዱ ክብደት ይጨምራል ሌላው ምቾት ይነሳል፣ አንዱ ራስ ምታት ይሰጣል ሌላው የሆድ ህመም ይፈጥራል፣ አንዱ የወር አበባ ያዛባል ሌላው ጭራሹን ክስተቱን ያጠፋል ወይም ፈሳሹን ያበዛል ወዘተ፡፡ ነገር ግን ሴቶች ይህን ሁሉ ፀጋ እስኪመስል ለምደው ተለማምደውት የወሊድ መቆጣጠሪያዎቹን ይጠቀማሉ፡፡ ኃላፊነቱ የባልና የሚስት ሆኖ እያለ ወንዶች ይህን በተመለከተ ሚስቶቻቸውን ወይንም የፍቅር ጓደኞቻቸውን ‘ይህን ሞክሪ ያኛውን ተይው … ደግሞ እስኪ ሌላ ሞክሪ’ ከማለት ባለፈና የህመም ማስታገሻ መድሃኒት ከማቀበል ባለፈ ያለፈ ኃላፊነት የሚወስዱት በቁጥር እዚህ ግባ የሚባሉ አይደለም፡፡
ዶ/ር ደረጀ እርስዎ በዚህ ሞያና ስራ ውስጥ ከመገኘትዎ አንፃር ይህን አገልግሎት የሚፈልጉ ወንዶች ከውሳኔያቸው በፊት ልብ ሊሏቸው  የሚገቡ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? እንደገና ወደመጨረሻዎቸ ጥያቄዎች ገባሁ፡፡ ዶ/ር ደረጀ በጥብቅ ከነገሩኝ ጉዳዮች ውስጥ ይኽኛው መሰረታዊ ጉዳይ እንደሆነ ገመትኩኝ እስኪ እናንተም አንብቡት
“በመጀመሪያ የወንድ ዘር መተላለፊያ ቱቦን መዝጋት /vasectomy/ ዘላቂ የሆነ የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገድ ነው፤ ከተሰራ በኋላ በአንድና በሌላ ምክንያት ጥንዶቹ መውለድ እንፈልጋለን ቢሉና ሃሳብ ቢለውጡ ቱቦውን በመቀጠል ወደነበረበት መመለስ አይቻልም /አንድም ግለሰቡ አቅም ኖሮት ወደ ውጭ ሃገር ሄዶ ካላሰራ በስተቀር/ ስለዚህ . . . ውሳኔአቸው  ቅፅበታዊ መሆን የለበትም፣ ተረጋግተው ባልና ሚስቱ ተወያይተው መወሰን አለባቸው፤ ይሄ አስቸኳይና አጣዳፊ ጉዳይ አይደለም፤ በቂና የሚፈልጉትን የልጆች ቁጥርና ፆታ ማግኘታቸውንና ተጨማሪ እንደማይፈልጉ እርግጠኞች መሆን አለባቸው፤ የተደላደለና ስምምነት ያለበት ትዳር መኖር አለበት/ካልሆነ ምንም እንኳን ፍችን መተንበይ ባንችልም ድንገት ቢያጋጥምና ቀጥሎ ከሚኖር ግንኙነት ልጅ የሚፈልጉና የማይፈልጉ መሆናቸውን ከወዲሁ ማየት መገመት ያስፈልጋል/ ይህን ዘዴ የሚመርጡ ሰዎች ሌላውና ዋናው ሊያቁት የሚገባ ጉዳይ የወሊድ መቅጣጠሪያው ዘዴ የአባላዘር በሽታዎችንና ኤች አይ ቪን አይከላከልም፡፡ ቤተሰብ እቅድ አገልግሎት በሚያቀርቡ ተቋማትና ባለሞያዎች በኩልም የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዶችን በተመለከተ ያሉትን አማራጮች በሙሉ ለተጠቃሚዎች ማሳዎቅ ያስፈልጋቸዋል፤ ” ማጠቃለያችንም ይኽው ነው፡፡ ሳምንት እንገናኝ፡፡

Read 3734 times