Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 December 2011 10:29

የ”ሳክስፎኑ ንጉስ” በለንደን ተደነቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“የሳክስፎኑ ንጉስ” በሚል የሚታወቀው የ76 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ ጌታቸው መኩርያ ከሳምንት በፊት በለንደን ከተማ በሪች ሚክስ አርት ቬኑ ባቀረበው የሙዚቃ ዝግጅት አድናቆትን አተረፈ፡፡ አርቲስት ጌታቸው ሙዚቃውን ያቀረበው “ዘ ኢኤክስ” ከተባለው የሙዚቃ ቡድን ጋር ሲሆን በርካታ እንግሊዛዊያውያንና በለንደን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዝግጅቱን ታድመውታል፡፡ 10 የሙዚቃ መሳርያ ተጫዋቾች የተካተቱበት የአምስተርዳሙ “ዘ ኢኤክስ”  ባንድና የሳክስፎን ተጫዋቹ ጌታቸው መኩርያ የሙዚቃ ዝግጅት ለንደን ውስጥ ለረጅም ጊዜ በጉጉት ሲጠበቅ እንደቆየ ያወሱ ዘገባዎች፤ ጌታቸዉ መኩርያ ከዓለም ምርጥ የሳክስፎን ተጫዋቾች ተርታ የሚሰለፍ ምርጥ ባለሙያ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ በሙዚቃ ሙያው ለ60 ዓመት ያገለገለው አርቲስት ጌታቸው መኩርያ፤ በወርቃማ ጎፈሬውና በቀለማት ባሸበረቀ ካባው ለመድረኩ ሞገስ እንዳጐናፀፈው “ዘ ኢቭኒንግ ስታንዳርድ” ጋዜጣ ጠቁሟል፡፡ “ዘ ሪች ሚክስ” የተባለ ድረገፅ በበኩሉ፤ አርቲስቱ በጥልቅ ስሜት ተውጦ በሳክስፎን ባቀረበው የሙዚቃ ሥራ ብቃቱን እንዳሳየ ዘግቧል፡፡

የ”ዘ ኢኤክስ” ባንድ አባላት ከጌታቸው መኩሪያ ጋር መስራት የጀመሩት ከ8 ዓመት በፊት ከኢትዮፒከስ አልበሞች አንዱ የሆነውን “ኪንግ ኦፍ ኢትዮጵያን ሳክስ” ከሰሙ በኋላ እንደሆነ ይታወቃል፡፡   ከ5 ዓመት በፊት በሲዲ “ሞ አንበሳ”፣ በዲቪዲ ደግሞ “ጌታቸው መኩርያ ኤንድ ዘ ኢኤክስ” የተባሉ ሁለት የሙዚቃ አልበሞችን በጋራ ለዓለም ገበያ አቅርበዋል፡፡ በፖስትፓንክ የሙዚቃ ስልት የሚታወቀው ”ዘ ኢኤክስ” ባንድ፤ ባለፉት 8 ዓመታት በመላው አለም ሙዚቃውን በታላላቅ መድረኮች ሲጫወትም ሳክስፎኒስቱ ጌታቸው የቅርብ ተባባሪ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡ ከተመሰረተ 32 ዓመት ያስቆጠረው ባንዱ ተቀማጭነቱ በአምስተርዳም ሆላንድ ሲሆን ከ25 በላይ አልበሞችን ለገበያ ሲያቀርብ በአውሮፓ፤ በኤስያና በሰሜን አሜሪካ ከ1500 በላይ ኮንሰርቶችን ያዘጋጀ ቡድን ነው፡፡

 

 

Read 1987 times Last modified on Saturday, 17 December 2011 10:35