Print this page
Saturday, 31 May 2014 14:28

ትልቁ አለማቀፍ ባንክ፣ የእንግሊዝን ሽንፈትና የብራዚልን ድል በስሌት ገለፀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንግሊዝ ከቡድን ማጣሪያ እንደማታልፍ የገለፁት የጎልድማን ሳችስ ታዋቂ የባንክ ኤክስፐርተቶች፣ ብራዚል ብርቱ ተፎካካሪዎች ቢኖሩባትም ዋንጫ የማንሳት እድሏ ከፍተኛ ነው አሉ።
እልፍ አይነት መረጃዎችን በመተንተንና በማጠናቀር፣ ዙሪያ ገባውን አበጥሮና አንጥሮ፣ ፈጭቶና ጋግሮ፣ እጥር ምጥን ያለች ፎርሙላ መፍጠር፣ ለፊዚክስ ጠብተቶች ብቻ የተተወ ስራ አይደለም። በአለም ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የያዙ እንደ ጎልድማን ሳችስ የመሳሰሉ ባንኮች፤ የእለት ተእለት ስራቸው፣ መረጃዎችን ማበጠርና መፍጨት ነው። በቅርቡ፣ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጤንነትን በሚመለከት፣ “ቢ” የተሰኘ ማርክ ሰጥተዋት መንግስት ምን ያህል እንደተደሰተ አላያችሁም? በመቶ የሚቆጠሩ አገራትን፣ በአስር ሺ የሚቆጠሩ ኩባንያዎችን እየፈተሹና እየመረመሩ፣ ማርክ ይሰጣሉ። በዚሁም መሰረት በቢሊዮን ዶላሮች ያበድራሉ፣ ኢንቨስት ያደርጋሉ፤ አክሲዮን ይገዛሉ፣ ይሸጣሉ። እንጀራቸው ነው። አሁን ደግሞ ለአለም ዋንጫ ተሳታፊ ቡድኖች ማርክ ሰጥተዋል።
ምን ይሳናቸዋል? ጨዋታዎችንና ጎሎችን፣ ድሎችንና ሽንፈቶችን፣ እንዲሁም ወቅታዊ ብቃትና ውጤቶችን በሚመለከት የ55 ዓመታት መረጃዎችን በመፈተሽ ነው የባንኩ ኤክስፐርቶች የራሳቸውን ቀመር ያዘጋጁት።
በባንኩ ቀመር መሰረትም፣ የዋንጫው ባለቤት ብራዚል ይሆናል። ለምሳሌ ከእንግሊዝ ቡድን ጋር ሲነፃፀር፣ የብራዚል የማሸነፍ እድል፣ ከ35 እጥፍ በላይ ይበልጣል። ምን ማለት መሰላችሁ? በውርርድ አንድ ብር ታስይዛላችሁ እንበል። ሁለት አማራጭ ይቀርብላችኋል። እንግሊዝ ያሸንፋል ብሎ የሚወራረድ፣ በአንዷ ብር 35 ብር ያገኛል። ብራዚል ያሸንፋል የሚል ካለ ደግሞ፣ በአንዷ ብር 2 ብር ያገኛል። ከእነዚህ ሁለት አማራጮች የትኛውን ትመርጣላችሁ? ከታዋቂው አለማቀፍ ባንክ ምክር የምትቀበሉ ከሆነ፣ “ብራዚል ያሸንፋል” ብላችሁ ለውርርድ ብታስይዙ ይሻላል።
ብራዚል በአለም ዋንጫው ወደ ሁለተኛ ዙር የማለፍ እድሏ ከ99 በመቶ በላይ ሲሆን፣ የእንግሊዝ እድል 54 በመቶ ያህል ነው። ለፍፃሜ የመድረስ እድላቸውስ? የብራዚል 60 በመቶ ሲሆን፣ የእንግሊዝ ግን ከ5 በመቶ ብዙም አይበልጥም።
ከብራዚል በመቀጠል ከፍተኛ ግምት የተሰጣት አርጀንቲና ነች። ከዚያ ደግሞ ጀርመንና ስፔን።

Read 1876 times
Administrator

Latest from Administrator