Saturday, 07 June 2014 14:12

ኢትዮጵያዊው ተማሪ የቴክኖሎጂ ፈጠራውን በዋይት ሃውስ አቀረበ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ፈጠራው በአዲስ አበባ የትራፊክ አደጋን ይቀንሳል ተብሏል
“እነዚህ የላቀ የፈጠራ ክህሎት ከታደሉ የአሜሪካ ተማሪዎች ጥቂቶቹ ናቸው” - ባራክ ኦባማ

     የ18 አመት ዕድሜ ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ተማሪ ፈለገ ገብሩ፣ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ያስችላል የተባለውን የቴክኖሎጂ ፈጠራውን ባለፈው ሳምንት በዋይት ሃውስ በተካሄደው የሳይንስ ትርዒት ላይ ማቅረቡን ኤምአይቲ ኒውስ ዘገበ፡፡
በማሳቹሴትስ የሚገኘውን ኒውተን ኖርዝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወክሎ በትርዒቱ ላይ የቀረበው ፈለገ፣ የትምህርት ቤት ጓደኛው ከሆነችው ካሬን ፋን የተባለች የ17 አመት ወጣት ጋር በመተባበር የፈጠረው አዲስ ቴክኖሎጂ፣ የማስጠንቀቂያ መልዕክቶችን በማስተላለፍና እንቅስቃሴውን የተሳለጠ በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ የሚታውየን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የሚያስችል እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በሳይንስ ትርዒቱ ላይ ተገኝተው የወጣቶችን የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች የተመለከቱት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ በዝግጅቱ ላይ ስራዎቻቸውን ላቀረቡ ተማሪዎች ያላቸውን አድናቆት በመግለጽ፣ እነዚህ በዝግጅቱ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች፣ የላቀ ፈጠራ ክህሎት ከታደሉ በርካታ የአሜሪካ ተማሪዎች ጥቂቶቹ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ዴቪድ ሁድሰን በዋይት ሃውስ ድረገጽ ላይ ፈጠራውን በተመለከተ ባሰፈሩት ጽሁፍ፣ “እነዚህ ወጣቶች በአለማችን እንደ ኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ በርካታ ቁጥር ያላቸው እግረኞች የሚሞቱበት አገር እንደሌለ በማጤን ነው፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግና አደጋውን ለመቀነስ የሚያስችል ፈጠራ በማመንጨት ያቀረቡት ”ብለዋል፡፡
የቴክኖሎጂ ፈጠራው አሽከርካሪዎች እግረኞችን በተመለከተ መረጃ የሚያገኙበት እንዲሁም እግረኞችም የተጨናነቁ መንገዶችን ያለ ችግር ማቋረጥ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ያሉት ሁድሰን፣ ፈጠራው የጸሃይ ብርሃንን በሃይል ምንጭነት የሚጠቀምና የተሸከርካሪዎችን ፍጥነት በማስላት የተወሰነ ቦታ ላይ የሚደርሱበትን ጊዜ የሚያሰላ፣ ለእግረኞችም መንገድ ማቋረጥ የሚችሉበትን የተመረጠ ጊዜ የሚጠቁም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 በሚማሩበት ትምህርት ቤት የተቋቋመው ኢንቬንቲም የተባለ የፈጠራ ክበብ መሪዎች የሆኑት ፈለገ እና ካረን በፈጠራ ስራ ላይ የመግፋት ዕቅድ ያላቸው ሲሆን፣ ፈለገ በአሁኑ ወቅት በብራውን ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስና የቪዡዋል አርት የመጀመሪያ ዓመት ትምህርቱን በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡“የፈጠራ ስራዎቻቸውን በዋይት ሃውስ የሳይንስ ትርዒት ላይ እንዲያቀርቡ መጋበዛቸው፣ ለእነዚህ ልጆች እጅግ የሚደንቅ ክብር ነው የሚያጎናጽፋቸው፡፡ ፈለገም ሆነ ሌሎቹ ተሳታፊ ተማሪዎች ለሌሎች ወጣቶች መነቃቃትን የሚፈጥር የፈጠራ ተነሳሽነትና የአላማ ጽናት የተላበሱ ናቸው።” ብለዋል ሌሊልሰን-ኤምአይቲ የተባለው የፈጠራ ፕሮግራም መምህርና የፕሮጀክቱ አማካሪ የሆኑት ሌይ ስታብሩክስ፡፡
ኤምአይቲ ኒውስ እንደዘገበው፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ገብሩ፣ በአገሩ በኢትዮጵያ ከትራፊክ አደጋ ጋር በተያያዘ እግረኞች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በተመለከተ ለኢንቬንቲቭ ያቀረበውን መረጃ መነሻ በማድረግ ፕሮጀክቱ ሊቀጥል ችሏል፡፡

Read 3187 times