Saturday, 17 December 2011 10:53

40 ዓመት ያስቆጠረው “አደፍርስ” አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(2 votes)

2011-12-17

“አደፍርስ” ሲወጣ 10 ብር መሸጡ አስገርሞ ነበር፤ አሁን ፎቶ ኮፒው 200 ብር ይሸጣል

ዳኛቸው ወርቁን የማየው እንደ ፖለቲካ ሳይንቲስት ነው

ዳኛቸው በዚህ ዘመን ቢኖር “አደፍርስ”ን ላይጽፈው ይችላል

“አደፍርስ” ሲወጣ 10 ብር መሸጡ አስገርሞ ነበር፤ አሁን ፎቶ ኮፒው 200 ብር ይሸጣል
የአዳራሹ ወንበሮች ሞልተው ለመረማመጃ ክፍት የሆኑ ቦታዎች ላይ የቀመጡትን ጨምሮ 120 የሚደርሱ ሰዎች ተገኝተዋል፡ በዕለቱ ለውይይት የተመረጠው በደራሲ ዳኛቸው ወርቁ ተዘጋጅቶ በ1962 ዓ.ም የታተመው “አደፍርስ” ረጅም ልቦለድ መጽሐፍ ነው፡፡ የመወያያ ሐሳብ ያቀረበው ወግ ፀሐፊው መስፍን ሀብተማርያም “መጽሐፉን ምን ያህሎቻችሁ አንብባችሁታል?” በሚል ላነሳው ጥያቄ 20 የሚደርሱ ሰዎች ብቻ ነበሩ እጃቸውን በማውጣት ማንበባቸውን ያሳወቁት፡፡

ይህን ያስተዋለው ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም፤ ተሰብሳቢውን ፈገግ ያሰኘ ታሪክ ተናገረ፡፡ ቄሱ ምእመናኑን ሰብስበው ሲያስተምሩ ዋሉና ሲያጠናቅቁ “በሚቀጥለው ቀን የማስተምራችሁ ስለ ውሸት ነው፡ ስለዚህ ሁላችሁም የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 17ን አንብባችሁ እንድትመጡ” ብለው ያሰናብቷቸዋል፡ በማግስቱ ምእመናኑ ተሰብስበው ቄሱ ማስተማር ሲጀምሩ “የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 17ን ምን ያህሎቻችሁ አንብባችሁ መጥታችኋል” ብለው ሲጠይቁ ሁሉም ምእመን እጁን አወጣ፡፡ ይህን ጊዜ ቄሱ “የማርቆስ ወንጌል ከ16 ምዕራፍ በላይ የለውም” ብለው ስለውሸት ሕዝቡን አስተማሩት፡፡ ከዕለቱ ተሰብሳቢዎች “አደፍርስ”ን ያነበቡት ጥቂቶች እንደሚሆኑ ገምቼ ነበር ያለው ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም፤ ስለ መጽሐፉና ደራሲው እኔ የማውቀውን ጥቂት ነገር ነግሬያችሁ እናንተም የምታውቁትን ስትናገሩ ሰምቼ ለመማር ነው የመጣሁት፣ በማለት ስለደራሲው ማንነት፣ ልቦለዱን ልዩ የሚያደርገው ምን እንደሆነና መጽሐፉ እንዴት እንደታተመ የመግቢያና የመወያያ ሐሳብ አቀረበ፡፡ እሁድ ታህሳስ 1 ቀን 2004 ዓ.ም አምስት ኪሎ በሚገኘው ብሔራዊ ሙዚየም አዳራሽ ሚዩዚክ ሜይዴይ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በ”አደፍርስ” ልብወለድ ዙሪያ የተነሱት አስተያየቶች፤ መጽሐፉ ዘመን ተሻግሮም አነጋጋሪ መሆን መቻሉን ያመላከተ ነበር፡፡ መጽሐፉ ከታተመበት ጊዜ ጀምሮ በአድናቆትና በትችት ሀሳብ እየቀረበበት ለዛሬ ደርሷል፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር “ብሌን” ቁጥር አንድ መጽሔትን በ1982 ዓ.ም ሲያሳትም “አደፍርስ” የታተመበትን 20ኛ ዓመት እያከበረ ነበር፡፡ የብሌን መጽሔትን ደረጃና ክብር ከፍ ካደረጉ ነገሮች አንዱ በሐያሲ አብደላ ዕዝራ አወያይነት፣ ታዋቂ የኢትዮጵያ ደራሲያን ስለ አገራችን ሥነ ጽሑፍ ዕድገት የሰጡትን አስተያየት የያዘ በመሆኑ ነው፡፡ በዚያ ውይይት ላይ ሰፊ ክርክር ከተካሄደባቸው መፃሕፍት መሐል የዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ” ይገኝበታል፡፡ መጽሐፉ በታተመ በ40ኛ ዓመቱም በአነጋጋሪነት መቀጠል መቻሉም በሚዩዚክ ሜይዴይ መድረክ ታይቷል፡፡ የመወያያ ሐሳብ አቅራቢው ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም ስለ “አደፍርስ” ሲናገር፤ “ታሪኩ በጥቂት ቀናት የተከናወነ ነው፡፡ ዘመኑ የፊውዳሉ ሥርዓት ማክተሚያ አካባቢ ሲሆን ታሪኩ የሚንቀሳቀስበት ቦታ ይፋትና ደብረሲና ዙሪያ ነው፡፡ ፊውዳል ቤተሰቦች፣ አገልጋዮቻቸው፣ የሃይማኖት አባት፣ ነጋዴ፣ ዳኛ፣ ወታደር፣ ምሁሩን የሚወክሉ ሰዎች በገፀ ባሕሪነት የያዘው መጽሐፉ፤ በቋንቋ አጠቃቀሙ የበለፀገ፣ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን አብዝቶ የሚጠቀም፣ አተራረኩ ከመንገርና ከስብከት ይልቅ በድርጊት ለማሳየት የሚሞክር፣ የምልሰት ቴክኒክን አብዝቶ የሚጠቀም፣ ገፁ ባሕሪያት በውስጣቸው የሚያስቡትን አውጥቶ ለማሳየት የሚሞክር መሆኑንና በዘመኑ ይታተሙ ከነበሩ መፃሕፍት አንፃር ሲታይ ባልተለመደና ወጣ ባለ መልኩ የቀረበ ሥራ ነበር ብሏል፡፡

መጽሐፉን ባነበቡት፣ ብዙ ሰዎች ዘንድ “ከባድ ነው” የሚል ቅጽል ለመጽሐፉ እንዲሰጥ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ፣ በከተማ አካባቢ ብዙም ያልተለመዱ የአማርኛ ቃላትን በመጠቀሙ ነው ያለው ደራሲው፤ በሌላው ጐን “በአማርኛ ቋንቋ እንዲህ መፃፍ ይቻላል ለካ” ብለው የዳኛቸው ወርቁ ሥራን መነሻ በማድረግ የራሳቸውን መጽሐፍ ያዘጋጁ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉም አመልክቷል፡፡

“አደፍርስ” ታሪኩ ይህ ነው ብሎ ለመግለጽ ያስቸግራል ያለው ደራሲ መስፍን፤ “ሆኖም ሃይማኖትን ያሳያል፣ ታሪክን ይዳስሳል፣ ተፈጥሮን በፊልም እንደምናየው አድርጐ ይቀርጽናል፣ ገፁ ባሕሪያቱን አጉልቶ መቅረጽ ከመቻሉ ባሻገር በቅርብ የምናውቃቸው ሰዎችን መስለው ይታዩናል፣ አተራረኩ ግጥም የማንበብ ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል” ሲል ተናግሯል፡፡ ደራሲ መስፍን በማጠቃለያውም፤ የመጽሐፉን የመጀመሪያ ሁለት ገጽ ስታነቡ ኢትዮጵያን መቼት አድርጐ ኢትዮጵያንና የአገሪቱን ብሔር ብሔረሰቦች ሰብስቦ ማሳየት መቻሉን ትረዳላችሁ ብሏል፡፡ በመቀጠል ከታዳሚዎች የተለያዩ አስተያየትና ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡

ከዳኛቸው ወርቁ ጋር በደረጃዎች መዳቢ አብረን ሰርተናል፡፡ በደረጃዎች መዳቢ በኮንትራት ሥራ የጀመረው በዩኒቨርሲቲ የነበረውን ሥራ ከተወ በኋላ ነው፡፡ በኋላ ላይ ቅጥሩ ቋሚ ሆኖለታል፡፡ በጣም የሥራ ሰው ነው፡፡ ሥራ ከሌለው ስለሚነጫነጭ ሥራ እንዲያጣ ይደረግ ነበር፡፡ ጽፎ ካሳተማቸው ውጭ “The Door man” በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ያዘጋጀው መጽሐፍ ነበረው፡፡ ጽሑፉ ዳኛቸው ወርቁ በአሜሪካን አገር ተማሪ እያለ በገጠመው ክስተት ላይ ተመስርቶ ያዘጋጀው ነበር፡፡ አብረውት ይማሩ ከነበሩ ተማሪዎች መሐል አንዱ ጃፓናዊ ተማሪ መለመረቂያ የተሰጠውን ሰርተፍኬት መኝታ ቤቱ በር ላይ አንጥፎ የጫማውን አቧራ ጠርጐበት ወደ አገሩ መሄዱን ያው ዳኛቸው፤ ያ መነሻ ሆኖት ነበር ጽሑፉን ያዘጋጀው፡ ብዙ ጓደኞች አልነበሩትም፡፡ ከጥቂት ጓደኞቹ አንዱ መንግሥቱ ለማ ነበሩ፡፡ በጣም ሰው አክባሪ፣ ጨዋና የሥርዓት ሰው ነበር፡፡

የዳኛቸው ወርቁ ሥራ በቋንቋ የበለፀገ ነው እየተባለ በሌላ በኩል ደግሞ ሃሳቡ አይገባም፤ ከባድ ነው ይባላል፡፡ እንዲህ የሚያነጋግር መጽሐፍ ኪነ ጥበባዊ ፋይዳው ምንድን ነው? የዳኛቸው ወርቁ የአስተሳሰብ ዘይቤ ምን ነበር? ጋሽ መስፍን በሁለት ዘመን መሐል ካሉ ሰዎች አንዱ ነህ፤ የቀድሞውንና የአሁኑን ዘመን ስታነፃጽር ሥነ ጽሑፋችን እያደገ ነው ወይ? ለዳኛቸው ወርቁ ግሪምቢጣን የሚል ቅጽል ሥም የሰጡት ሰዎች አሉ፡፡ ትርጉሙ ወጣ ያለ አፈንጋጭ እንደማለት ነው፡፡ መንግሥቱ ገዳሙም የተለየ ባሕርይ እንደነበረው ይነገራል፡፡ እኔ በእንዲህ ዓይነት የውይይት መድረኮች ላይ ሰዎቹን ትተን ሥራዎቻቸው ላይ ብንነጋገር የሚል አቋም ያለኝ ቢሆንም ስለ ዳኛቸው ወርቁና መሰል ሰዎች የምሰማቸው ነገሮች ስለ ሰዎቹ ማንነት መነጋገሩ ይጠቅማል እንድል አድርጐኛል፡ ዳኛቸው ወርቁ ማተሚያ ቤት በፈጠረበት ስህተት ምክንያት ለሥራው የሚደርሰውን 40ሺህ ብር አልወስድም ያለ አስገራሚ ሰው ነው፡፡ “አደፍርስ”ን አሳትሞ በደረሰበት ነቀፌታ ምክንያት መፃሕፍቱን ከየመደብሩ ሰብስቦ ቤቱ ከቆለፈበት በኋላ መጽሐፉን ማንበብ ለሚፈልጉ ሰዎች የ10ብሩን መጽሐፍ እስከ 15 ብር ይሸጥ እንደነበር ይነገራል፡፡ የዳኛቸው ወርቁ ሥራ በብዙ መልኩ ተትንትኖ መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ “ፍቅር እስከ መቃብር” እና “አደፍርስ” ያላቸው አንድነት ምንድነው? ጉዱ ካሣና አደፍርስ ጉደኛ ገፀ ባሕሪያት ሊሆኑ እንዴት ቻሉ? የዳኛቸው ወርቁ መጽሐፍ ዋና ገፀ ባህሪ ማንነት የሚያንፀባርቀው የተማረውን ትውልድ ነው ወይስ ለብዙ ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች የተጋለጠውን የሰሜን ሸዋ ሕዝብ? ዳኛቸው በመጽሐፉ ብዙ ነገር ነው ያለው፡፡ በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመጠቀምን አዎንታዊ ጐን አመላክቷል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ቢያንስ ሦስት ብሔራዊ ቋንቋ እንዲኖራት አሳስቧል፡፡ እኔ ዳኛቸው ወርቁን የማየው እንደ ፖለቲካ ሳይንቲስ ነው፡፡

ለቀረቡት አስተያየትና ጥያቄዎች ምላሽና የራሱንምአስተያየት የሰጠው ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም፤ የዳኛቸውን አፈንጋጭነት ካልተቀበሉት አንዱ የነበረው ደራሲ አቤ ጉበኛ ለእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ምላሽ ለመስጠት አስቦ “ጐብላንድ አንድ አጭበርባሪ ጦጣ” በሚል ርዕስ መጽሐፍ አዘጋጅቶ ማሳተሙን አስታውሷል፡፡

በፈጠራ ጽሑፍ አፃፃፍ በአሜሪካ አገር ተምሮ የመጣው ዳኛቸው ወርቁ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማስተማሩን ከተወ በኋላ “አደፍርስ”ን ጽፎ ሲያሳትም ቀድሞት የታተመው “ፍቅር እስከ መቃብር” በተወሰነ መልኩም ቢሆን ተጽእኖ ሊያሳድርበት እንደሚችል የገለፀው ደራሲ መስፍን፤ ከቀድሞ ዘመን በተለየ መልኩ አዲስ ቴክኒኮችን ማምጣቱን መስክሯል፡፡

በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት አብረን እንሰራ ነበር ሲል ዕውቂያቸውን የጠቆመው አወያዩ በበኩሉ፤ “ዳኛቸው በብዙ ነገር ፈጣን ነው፡፡ ሌሎች ልብ የማንለውን ነገር እሱ በትኩረት ያያል፡፡ ሰውን ስትመለከቱ አነጋገሩን ጭምር ቅረፁ ይለን ነበር፡፡ የዳኛቸውን መጽሐፍ ስታነቡ ያለ ምክንያት የገባ ሥርዓተ ነጥብ አታገኙም፡፡ ይህንን ያስተዋለ አንድ ሰው፤ የዳኛቸው ፀሐፊ መሆን እንዴት ከባድ ነው“ ማለቱን አስታውሷል፡፡

የአሁኑንና የቀድሞውን ዘመን ጽሑፍ ማወዳደር ይከብዳል ያለው ደራሲ መስፍን፤ ሁሉም ዘመን የራሱን ደራሲ ይፈጥራል፡፡ ደራሲው ያየውን፣ የሰማውን በሚያውቀው ቋንቋ ይጽፋል፡፡ ደራሲ እንደዚህ ነው መፃፍ ያለበት ተብሎ መስመር ማበጀት አይቻልም፡፡

አንባቢያን ናቸው ወደ ደራሲው ዘመን ሄደው ለመረዳት መሞከር ያለባቸው፡፡ ዳኛቸው ወርቁ በዚህ ዘመን ቢኖር “አደፍርስ”ን ላይጽፈው ይችላል፡፡

ዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ”ን ያሳተመው በራሱ ገንዘብ ነበር፡፡ ለመጽሐፉ 10 ብር ዋጋ ሲያወጣ ጉድ አሰኝትዋል፡፡ ዋጋውን ከፍ ያደረገበት ዋነኛ ምክንያት መጽሐፍ ክብር እንዲሰጠው ለማድረግ ነበር ያለው ደራሲ መስፍን፤ በመጽሐፉ ዋጋ ውድነት ላይ ጋዜጠኞችም ሥራውን እያጥላሉ በመፃፍ ጠምደው ሲይዙት መጽሐፉን ሰብስቦ ቤቱ ወስዶ ቆለፈበት፡፡ ዳኛቸው ወርቁ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ መጽሐፉ በ50 ብር ይሸጥ ጀመር፡፡ አሁን በአሮጌ መፃሕፍት ተራም ፎቶ ኮፒው 200 ብር እየተሸጠ እንደሆነ መስፍን ጠቁሟል፡፡

“አደፍርስ” ይህ ነው የሚባል ታሪክ የለውም ይባል እንጂ አንዳንዶች አንብበው ትርጉም በመስጠት የፊውዳሉ ሥርዓት እንዳበቃለት፣ ወታደራዊ መንግሥት እንደሚመጣና ሕዝቡም ወደ ቤተ ሃይማኖት አብዝቶ እንደሚሄድ ያመለከተ መጽሐፍ ነው እንደሚሉትና ይህም ትርጓሜ ከገፁ ባሕሪያቱ የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ ጋር በተያያዘ የተገኘ መሆኑን በመተንተን አቅርቧል፡፡ እንግዲህ ከዕለቱ ውይይት መረዳት የምንችለው “አደፍርስ” ዘመን ተሻግሮም እያነጋገረ ያለ መጽሐፍ መሆኑን ነው፡፡ አነጋጋሪነቱ በጥልቀቱ ወይስ ከባድ በመሆኑ? ሌላ ውይይት ይፈልጋል፡፡

 

 

Read 8191 times Last modified on Saturday, 17 December 2011 11:14