Saturday, 21 June 2014 14:31

የሥነ ልቦና ባለሙያው ስለውሸት ምን ይላሉ?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(10 votes)

ውሸት ራሱን የቻለ በሽታ ሳይሆን የበሽታ ምልክት ነው
ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ - መዋሸት ሳይሆን ማጭበርበር ነው
ውሸት ወደ ስብዕና ደረጃ ከተሸጋገረ፣ ግለሰቦቹ ችግር እንዳለባቸው አይቀበሉትም

ውሸት ምንድን ነው?
ውሸት ራሱን የቻለ የስብዕና መለያ ሊሆን ይችላል፡፡ የተለያየ እድሜ ላይ ሊከሰትም ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከጨቅላነት እድሜ የሚጀምር ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በጉርምስና ጊዜ ይጀምራል፡፡ ውሸትን ከልጅነት እድሜ ጀምሮ እየተሸለመ የመጣ (ሲዋሽ በቤተሰቡ ትኩረት እየተሰጠው ያደገ) ህፃን እድሜ ልኩን ውሸትን በልማድና በስብዕና መለያነት ይዞት ይኖራል፡፡
ሌላው የውሸት አይነት በስብዕና ቀውስ መዛባት የሚመጣ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ውሸት ለማህበረሰብ ጠንቅ የሆነ የስብዕና አይነትን ይፈጥራል፡፡ ሰዎችን ማታለል፣ ወዳልሆነ አቅጣጫ መምራት የመሳሰለው ተግባር እንደ አንድ መጥፎ የስብዕና መለያ ምልክት ይወስዳል፡፡ ስለሆነም እነዚህ የስብዕና መዛባት ችግር ያለባቸው ሰዎች ውሸት አንደኛው መለያቸው ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል የአዕምሮ ጭንቀት ህመም ለውሸት መነሻ ምክንያት ይሆናል፡፡ የጭንቀት ህመም በጉዳት ወቅትና ከጉዳት በኋላ የሚፈጠር ሲሆን ይህ ጭንቀት ሰዎችን ከእውነተኛው ስብዕናቸው እንዲያፈነግጡ ያደርጋቸዋል፡፡ ሰዎች በአንድ ምክንያት ከተጎዱ በኋላ ሚደርስባቸው የጭንቀት ህመም፣ ያንን ጉዳታቸውን እያስታወሱ ላለመሰቃየት ሲሉ ሌላ ያልሆነ ነገር በመፍጠር መዋሸት ይቀጥላሉ፡፡ እንዲህ አይነቱ ሰዎች ሆን ብለው በመዋሸት ሌላውን ለመጉዳት የሚታትሩ አይደሉም፡፡ ያንን ጉዳታቸውን ላለማስታወስና ወደ ጉዳታቸው ላለመመለስ የሚዋሹ ናቸው፡፡
ውሸት በሽታ ነው?
ውሸት ራሱን የቻለ በሽታ ሳይሆን የበሽታ ምልክት ነው፡፡ ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ውሸት የስብዕና መዛባት ችግር፣ የጭንቀትና ከፍተኛ የአእምሮ ጉዳት ምልክት ነው፡፡ ለምሳሌ የስብዕና መዛባት ችግር ያለበት ሰው ውሸት አንዱ ምልክቱ እንጂ ከዚያ በላይ በርካታ መለያዎች ይኖራሉ፡፡ በሌላ በኩል “Boarder light” የሚባል የስብዕና ችግር አለ፡፡ ሲሆን ይህ ችግር ስሜታቸው የሚቀያየርና ከሰዎች ጋር ያላቸው መስተጋብርና ከማህበረሰቡ ጋር ያላቸው ግንኙነት የሚለዋወጥ ግለሰቦች ላይ የሚታይ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ስሜታቸውን መቆጣጠር የማይችሉ፣ ግልፍተኝነት የሚያጠቃቸውና፣ በማህበራዊ ግንኙነታቸው ችግር ያለባቸው ሰዎች የሚያንፀባርቁት የስብዕና አይነት ነው - “ቦርደር ላይ የሚባለው፡፡ እነዚህ ሰዎች ስሜታቸው ለመቆጣጠር ጥረት የሚያደርጉ ሲሆን በዚህ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ስለሚዋሹ አንዱ የስብዕናቸው መለያ ይሆናል እንጂ ውሸት ራሱን የቻለ በሽታ አይደለም፡፡
ውሸትን ማንኛውም ሰው ይዋሻል፡፡ የማይዋሽ ማንም የለም፡፡ በየትኛውም የእውቀትና እድሜ ደረጃ እንዲሁም አኗኗርና ባህል ውስጥ ያለ ሰው ይዋሻል፡፡ ማንኛውም ሰው ትክክለኛነትን ማረጋገጥ ስለማይችል ህይወቱን ለማስተካከል፣ ስጋቶቹን ለመቅረፍ የሚዋሽበት ሁኔታ ይፈጠራል። ሰዎች ውሸትን እንዲዋሹ ከሚያተጓቸው ነገሮች አንዱና ዋናው የፍርሀት ስሜት ነው፡፡ ፍርሀት የሚከሰትባቸው በርከት ያሉ መሰረታዊ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን አንደኛው ትችትን ነቀፌታን ውርደትንና ሸንፈን ያለመቀበል ነው፡፡ ሌላኛው ምክንያት ደግሞ አንድ ግለሰብ በአንድ በቡድን ወይም ማህበረሰብ ውስጥ ራሱን የቻለ ማንነት ይኖረዋል፡፡ ይህን ማንነቱን የሚያጎድልበት ነገር ካለ ያንን ለመሙላት ሲል ሊዋሽ ይችላል፡፡
በሌላ በኩል ህልውናን ለማስጠበቅ፣ በስነ ልቦና ችግርና የተፈላጊነትን ስሜት ለመጨመር የሚዋሽበት ጊዜ አለ፡፡ ለምሳሌ እድሜን ቀንሶ መናገርን ማንሳት ይቻላል፡፡ እድሜያችን እየጨመረ ሲሄድ ተፈላጊነት እያጣን እንደምንመጣ ስለምናስብ ፍርሃት ይለቅብናል፡፡ ከዚህ ከፍርሀት ለመላቀቅ እንዋሻለን። በእነዚህና መሰል ምክንያቶች የማይዋሽ ሰው አለ ማለት ይቸግራል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ውሸት “reaction formation” ይባላል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው… እራሳችንን ከእውነተኛው ነገር በተቃራኒው የማሰብ ሂደት ላይ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ባሉብን ጉድለቶች የተነሳ አዕምሯችን ጭንቀት ላይ እንዳይወድቅ የማድረግ ሂደት ነው… ሪአክሽን ፎርሜሽን፡፡ ለምሳሌ አንዲት ሴት አንድን ወንድ አፍቅራው በሰው ፊት እንዳላፈቀረችው ትናገራለች፡፡ ይህ ምንድነው? ውሸት ነው፡፡ የምትዋሸው ደግሞ በምትኖርበት ማህበረሰብ ውስጥ ያላትን ዋጋ ላለማጣት ስትል ነው፡፡ የበታችነት ስሜት እንዳይሰማት ያደረገችው ትግል ነው፡፡ ማለት ይቻላል፡፡ ይህቺ ሴት በዋሸችው ውሸት ታማሚ ናት ወይም ትክክል አይደለችም ብሎ ለመደምደም ይቸግራል፡፡ ይህቺ ሴት ሌላውን ለመጉዳት፣ በሌላው ላይ ችግር ለመፍጠር አልተጋችም፡፡
ስንት አይነት ውሸታም አለ?
ውሸታሞች በሁለት ይከፈላሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ በማንኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ የሚዋሹ ሲሆን ሁለተኛዎቹ በተወሰነ ጊዜና ቦታ ብቻ የሚዋሹ ናቸው፡፡ እነዚህ ውሸቶች ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው የተለያዩ ናቸው፡፡
ሰሞኑን በትምህርት ማስረጃ ውሸት የፈፀሙት ግለሰብ የውሸት አይነት የትኛው ነው?
ሰሞኑን በተለያዩ ሚዲያዎች መነጋገሪያ የሆነው የአቶ ሳሙኤል ዘ/ሚካኤል ጉዳይ በቴክኒክ ደረጃ ስንመለከተው ውሸት አይደለም፡፡ እንደሚባለው ፈፅመውት ከሆነ አይን ያወጣ ማጭበርበር ነው። ውሸት ማለት ትርጉሙን ስንመለከት በዕለት ተዕለት የህይወት መስተጋብር ውስጥ ያልተገባ መረጃን መልቀቅ ማለት ነው፡፡ የእለት ተዕለት ማህበራዊ መስተጋብር የሚከወነው በጓደኛሞች፣ በስራ ባልደረቦች፣ በቤተሰብ አባላት፣ በጎረቤታሞች መካከል ነው፡፡ በነዚህ መካከል የሚካሄድ ትክክል ያልሆነ የመረጃ ዝውውር ነው ውሸት የሚባለው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ግለሰብ ድርጊት ግን ከውሸት አልፎ “ማጭበርበር” የሚለውን ደረጃ የሚዝ ነው፡፡ ማጭበርበር ደግሞ “ናርሲስት” የሚባለው የስብዕና አይነት ውስጥ ሊመደብ ይችላል፡፡ አለበለዚያም ለማህበረሰብ ጠንቅ የሆነ የስብዕና ምድብ ውስጥ ሊካተት ይችላል፡፡
ሆኖም ይሄ ከውሸት አልፎ ከፍተኛ የሆነ ራሱን የቻለ ምድብ ውስጥ ሊመደብ የሚችል ነው፡፡ የግለሰቡ ግን ከውሸት አልፎ ከፍተኛ የሆነ የማጭበርበርና የማታለል ተግባር ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ ይህ የማጭበርበር አይነት ለማህበረሰብ ጠንቅ የሆነ የስብዕና ባለቤቶች የሚያንፀባርቁት ነው ሌሎችን በማታለልና በመጉዳት ለራስ ጥቅም ብቻ መሮጥ ከውሸት በላይ ነው፡፡ ውሸት በማህበራዊ መስተጋብር ስሜታዊ በሆኑ ጉዳዮች ውስጥ የሚደረግ ስሜትን ያዘለና በአንደበት የሚነገር ነው፡፡ ማጭበርበር ግን ፍፁም ከውሸት ይለያል፡፡ የዓለም አይኖች ሁሉ እኔ ላይ ይረፉ፤ በዚህም ገንዘብ ላግኝ በማለት፤ በተቋማት፣ በአገርና በትልልቅ ግለሰቦች ስም መነገድ ማጭበርበር እንጂ መዋሸረት አይደለም።
ለምሳሌ አንዲትን ሴት ፍቅረኛው ለማድረግ የሚዋሽ ወንድ አሊያም ውርደትንና ሽንፈትን ላለመቀበል ጓደኛውን ወይም ፍቅረኛውን የሚዋሽ ግለሰብ፣ ህዝብን በጅምላ ከሚያጭበረብር ግለሰብ ጋር እኩል አይደለም፡፡ አገርን፣ መንግስትን፣ ህዝብን፣ በድፍረትና በማናለብኝነት የሚያጭበረብር ሰው ከፍተኛ የሆነ የግብረገብነት ችግር የተጠናወተው ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ የግብረገብነት ችግር ያለበት ሰው ደግሞ መቼም ቢሆን ከማጭበርበር የሚያግደው ስሜት አይኖረውም፡፡ የሞራል ልዕልናም የለውም። ስለዚህ የጤናማ መንፈስና አስተሳሰብ ድሀ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንደዚህ አይነት ሰው የኋላ ታሪኩ የጤንነቱ ሁኔታና ያለፈበት የህይወት መንገድ መጠናት አለበት፡፡   
ከፍተኛ የግብረ ገብነት ችግር ከጉርምስና ጊዜ ጀምሮ (ከ18-21 ዓመት ባለው) የሚከሰት ሲሆን ለማህበረሰብ ጠንቅ የሆነ ስብዕናን ያዳብራል፡፡ ለምሳሌ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም፣ ጠብ አጫሪነት፣ ድብድብ፣ ስርቆት፣ ማታለልና ማጭበርበር የግብረገብነት ችግሮች ሲሆኑ ለህብረተሰብ ጠንቅ የሆነ የስብዕና መዳረሻዎች ናቸው፡፡
የበላይነት ስሜት (ናርሲስት ፐርሰናሊቲ) የሚባለውም ከሰው በላይ ሆኖ ለመታየት ከሁሉም እበልጣለሁ ማለት፣ የሁሉንም ትኩረት ጨምድዶ ለመያዝ የሚደረግ የአምባገነንነት ስሜት የተጠናወታቸው ነገር ግን ከመጀመሪያውም የግብረ ገብነት ችግር አብሯቸው ያደገ ሰዎች የሚያሳዩት ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ይህን ፍላጎታቸውን ለማሳካት ብዙ ርቀት ይጓዛሉ፡፡ ከውሸትም በጣም ይዘላሉ፡፡ ለምሳሌ የሰሞኑ አጀንዳ የሆኑት ግለሰብ፤ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ አላቸው ከተባለ፣ ያጭበረበሩት ጓደኛቸውን፣ ጎረቤታቸውን ወይም የስራ ባልደረባቸውን አይደለም፡፡ ህዝብን፣ መንግስትን፣ አገርን ነው፤ ይህ ደግሞ ወንጀል ነው። ለምሳሌ ምንም ሳይኖራቸው በአንድ ዩኒቨርሲቲ ማህተም የተዘጋጀን ማስረጃ ማቅረብ ውሸት ተብሎ የሚታለፍ አይደለም፤ ማታለል ነው፡፡
መፍትሄው ምንድን ነው?
ችግሩ ሳይከሰትም ከተከሰተም በኋላ መፍትሄ አለው፡፡ በነገራችን ላይ ውሸት ወደ ስብዕና ደረጃ ከተሸጋገረ፣ ግለሰቦቹ ራሳቸው ችግር አለብን ብለው አይቀበሉም፡፡ ነገር ግን የመንግስትና የማህበረሰብ ተቋማት ይህንን ችግር የሚፈቱበት የራሳቸውን አሰራር በመዘርጋት መፍታት ይችላሉ፡፡ ተቋማቱ የውሸቱን አይነት ጥልቀትና የሚያደርሰውን ጉዳት በመመልከት በውሸቱ መጠን የተቃኘ መፍቻ ስልት ይነድፋሉ ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ቤተሰብ ራሱን የቻለ ተቋም እንደመሆኑ ልጆችን በማሳደግ ሂደት ውስጥ የራሱን ሚና ሊጫወት ይገባል፡፡ ይህ ማለት ልጆች በግብረ ገብ እንዲያድጉ፣ ሌላውን እንዲወዱ፣ ከሌላው ሰው ጋር ተግባብተውና ተስማምተው መኖርን እንዲለማመዱ፣ ለሌላው ሰው ትክክለኛ ነገርን በመስጠት ትክክለኛ ነገርን መሸለም እንዲችሉ አድርጎ ማሳደግ በወላጆች ላይ የሚጣል ኃላፊነት ነው፡፡
አንዴ በውሸት ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙትን ደግሞ በዚህ ችግር ውስጥ መኖራቸው ለእነሱም ሆነ ለሌላው ሰው ጎጂ መሆኑ ሊነገራቸው ይገባል፡፡ በትክክለኛ መንገድ ትክክለኛ ነገር ማግኘት እንደሚችሉ እንዲሁም ለራሳቸው ያላቸውን ግምት እንዲያስተካክሉ ተናግሯቸው በመረጃ ደረጃ ካወቁት በኋላ፣ የስነ-ልቦናና ሌሎች መሰል ድጋፎችን በማድረግ መፍትሄ መስጠት ይቻላል፡፡  

Read 9904 times