Saturday, 21 June 2014 14:33

“አዞ ያስለቅሳል እንጂ አያለቅስም”

Written by 
Rate this item
(7 votes)

             በአርባ ምንጭ የአዞ እርባታ ጣቢያ ለጉብኝት ታድመናል፡፡ የጣቢያው አስጎብኚ ወ/ት ህይወት አሰፋ ትባላለች፡፡ ስለ አዞ አፈጣጠር ስታብራራ መስማት ያልፈለገን ሰው ሳይቀር በማራኪ አቀራረቧ እንዲያደምጣት ታስገድዳለች፡፡ አቀራረቧ እስከዛሬ በርካቶቻችን ስለ አዞ የምናውቀውን እውነታ አጥርቶ ትክክለኛ መረጃ እንድንይዝ የሚያደርግ ነው፡፡ ህይወት የተረከችውን የአዞ አፈጣጠር እንዲህ አቅርቤዋለሁ፡፡
“የአዞ ተፈጥሮ በህይወት አንደበት”
ሃይቅ ዳርቻ ላይ አዞ እናት ከውሃው ከ20 እስከ 30 ሜትር ትርቅና፣ 60 ሣ. ሜትር ያህል አሸዋውን ቆፍራ እንቁላሎቹን ትቀብራለች፡፡ እንቁላሎቹ አዞ ለመፈልፈል 90 ቀናት ይበቃቸዋል፡፡ ጫጩት አዞ ገና እንደተፈለፈለ አሸዋ ውስጥ ሆኖ ድምፅ ማሰማት ይችላል፡፡ አንድ አዞ ከ 3 ዓመት እስከ 6 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ለእርድ ይደርሳል፡፡ አዞ አናቱ ካልተመታ አይሞትም፡፡
የሚታረደውም እንደሌሎች የእርድ እንስሳት ከአንገቱ ስር ሳይሆን በጀርባው በኩል ነው፡፡ ምክንያቱም የስረኛው ቆዳ እጅግ ተፈላጊ ስለሆነ እንዳይጎዳ ነው፡፡
ቆዳቸው እስከ 400 ዶላር ይሸጣል፤ ስጋቸው ግን በማርቢያ ጣቢያው መልሶ ለራሳቸው ምግብነት እየዋለ ቢሆንም እየተገነባ ያለው ዘመናዊ ቄራ ሲጠናቀቅ፣ ሃገሪቱ የአዞ ስጋ ወደ ውጭ ትልካለች፡፡ አንድ ኪሎ የአዞ ስጋ በአሁኑ ወቅት እስከ 160 ዶላር ይሸጣል።
የአዞን ፆታ ለመለየት በሚገባ ስለ አዞ የሚያውቁ ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ማንም ሰው በእይታ ብቻ ይሄ ወንድ ነው፣ ይህቺ ሴት ነች ብሎ መለየት አይችልም። ባይን የሚታይ የፆታ መለያ አዞ ጨርሶ የለውም፡፡ የአዞዎች የፆታ ሁኔታ በባለሙያዎች የሚለየው የተፈለፈሉበትን አሸዋ ሙቀት በመለካት ነው፡፡ ሙቀቱ ከፍተኛ ከሆነ ወንዶች ይሆናሉ፤ ቀዝቀዝ ካለ ሴቶች ይሆናሉ፡፡
እናት አዞ፤ በአሸዋ ውስጥ የቀበረችውን እንቁላል በየጊዜው እየተመላለሰች ደህንነቱን ትከታተላለች። ከተፈለፈሉ በኋላ ድምፃቸውን ከአሸዋ ውስጥ ስትሰማ በአፏ እየያዘች ታወጣና ውሃ ዳር ሳር ውስጥ ታስቀምጣቸዋለች፡፡ ይህን የምታደርግበት ምክንያት ጫጩት አዞዎች ትናንሽ ነፍሳትን እንዲመገቡ ነው፡፡ በሌላ በኩል በውሃ ውስጥ የሚገኙ ትላልቅ አዞዎች እንዳይበሉባትም ለመከላከል ነው፡፡ እናት አዞ ልጆቿን ከአደጋ ለመጠበቅ ዛፍ ላይ ወጥታ 360 ዲግሪ እየተመለከተች በትጋት ቅኝት ታደርጋለች፡፡
ጫጩት አዞዎች ከጥርስ ጋር ስለሚፈጠሩ ገና ከአሸዋ ውስጥ ሲወጡ መናከስ ይጀምራሉ። የጥርሳቸው ብዛት ከ62 እስከ 66 ይደርሳል፡፡ አዞ በነዚህ ጥርሶቹ እየቆረጠ ዋጥ ማድረግ እንጂ ማኘክ፣ ማላመጥ የሚባል ጣጣ አያውቅም። ከስጋ ውጪም አዞ ሌላ ምግብ አያውቅም። አዞ ተንቀሳቃሽ ምላስ የለውም፤ ለዚህ ነው የማያላምጠው፡፡
አስጎብኚያችን ህይወት እዚህ ጋ ጥያቄ ልጠይቃችሁ አለች፡፡ የአዞ እንባ የሚባለው ምንድን ነው? አዞ ምግብ ሲበላ ያለቅሳል የሚባለውስ? ብላ ጠየቀችን፡፡ በርካቶች የመሰላቸውን ሞከሩ፤ አንዳቸውም ግን መልሱን አላወቁትም፡፡ እኔው መልስ ልስጥ አለችን፡፡
አዞ ቆዳው ጥቅጥቅ ነው፡፡ የላብ ማስወጫ የለውም። በብዛት ቆርጦ ሲውጥ ጉሮሮው ይጨናነቃል፡፡ ጎሮሮው ሲጨናነቅ ላብ ያልበዋል፡፡ ላቡ በአይኑ በኩል ይወጣል፡፡ ስለዚህ የአዞ እንባ ላብ ነው፡፡ አዞ ያስለቅሳል እንጂ አያለቅስም” አለችን፡፡
ስለ አዞ አንዳንድ እውነታዎች
አንዲት አዞ በአንድ ጊዜ ከ30-70 የሚደርስ እንቁላል ትጥላለች፣ በአመት አንድ ጊዜ ብቻ የምትጥል ሲሆን 85 በመቶው ይፈለፈላል። በአለም ላይ 25 ዓይነት የአዞ ዝርያዎች ሲኖሩ አራቱ በአፍሪካ ይገኛሉ፡፡ሰ በኢትዮጵያ የሚገኘው አደገኛው የናይል አዞ የሚባለው ብቻ ነው፡፡
አንድ ትልቅ አዞ ከ7-8 ሜትር ሲረዝም፣ ከ500-700 ኪ.ግ ይመዝናል፡፡ ከ120-150 አመትም ይኖራል፡፡ የአዞ ቆዳ በአለማቀፍ ደረጃ እጅግ ተፈላጊ ሲሆን ከ27-37 ሣ. ሜትር ስፋት ያለውና ሽንቁር የሌለው ንፁህ ቆዳ 1ኛ ደረጃ ተብሎ እስከ 400 ዶላር ይሸጣል፡፡





Read 7763 times