Saturday, 21 June 2014 14:39

ያልተጋበዙ እንግዶች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

            እነዚህ እንግዶች አውቀንና ፈቅደን፣ ቄጠማ ጎዝጉዘንና ፈንዲሻ ቆልተን፣ ቡና አፍልተን፣ ምግብ አዘጋጅተን፣ … “ቤት ለእንቦሳ” ሲሉን “እንቦሳ እሰሩ” በማለት በደስታና በፌሽታ የምንቀበላቸው አይደሉም፡፡ ካለእኛ ፈቃድና እውቅና ውስጣችን ገብተው በመኖር ምግባችንን የሚጋሩንና (በአብዛኛው ሕፃናትን ለሞት) የሚዳርጉ አደገኛና አስጠሊታ ተውሳኮች ናቸው፡፡
እንግዲህ እኛ የሰው ዘሮች በዚህች ምድር ከማንኛውም በላይ እጅግ የተሳካልን እንስሳም አይደለን?! ስለዚህ በርካታ አደገኛና አጥቂ (ትላትሎች) ከእኛ ጋር በጥገኝነት ለመኖር ይወሩናል። በዚህ የተነሳ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ቫይረሶች፣ ባክቴሪያዎች፣ ፈንገሶች፣ ፕሪቶዟና አርትሮፓድስ የመሳሰሉ በርካታ ባለአንድ ህዋስ ጥገኛ ፍጡሮች (ሴል) መኖሪያ ነን፡፡
እነዚህ በዓይን የማይታዩ ባለ አንድ ሴል ደቂቅ ነገሮች ከተፈጠሩ በኋላ በመጀመሪያ ቫይረሶች ባክቴሪያን ይመርዛሉ ወይም ኢንፌክት ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ሂደት ባለ አንዱ ሴል ወደ ባለ ብዙ ሴሎች (መልቲሴሉላር) ፍጡር ከተለወጡ በኋላ፣ በእነሱ እግር የበለጠ ውስብስብ የሆኑ ፍጡሮች ይተካሉ። በምድር ላይ ከሚገኙ 100 ሚሊዮን ወይም ከዚያ በላይ ከሚሆኑ ፍጡራን መካከል ግማሽ ያህሉ ጥገኛ ህዋሳት ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡
ዲክሰን ደስፖሚየ፤ በዓይን የሚታዩ ጥቃትን ህዋሳት (ትላትሎች) ተመራማሪ (ሜይክሮባዩስት ዮሎጂስት) ናቸው፡፡ ተመራማሪው እነዚህን ያልተጋበዙ እንግዶች ለይተን አውቀን በውስጣችን መኖሪያቸውን እንዳይሰሩ ጥንቃቄ እንድንናደርግ፣ በሚያደርሱት የጉዳት መጠን ከ1ኛ እስከ 10ኛ ደረጃ ያሉትን ጎጂ ጥገኛ ትሎች ለይተው አቅርበዋል፡፡ ጉዳቱ አነስ ከሚለው እንጀምር፡፡
10ኛ. ቦት ፍላይት (Botfly-Dermatobia hominis)፡- እነዚህ ጥገኛ ትሎች ከባድና ትላልቅ ሲሆኑ መገኛቸውም የመካከለኛ አሜሪካ የባህር ዳርቻ መዝናኛዎች ናቸው፡፡ ሰዎች እነዚህን ትላልቅ ጥገኛ ትሎች ሰውነታቸው ላይ ሲያዩ ወዲያው እንቁላሎቻቸውን ሳይጥሉባቸው ጠርገው ስለሚያስወግዷቸው እቅዳቸው አይሰምርም፡፡ እነሱ ምናቸው ሞኝ ነው? የመጀመሪያው ዘዴ ካልሰራ፣ ሌላ ረቀቅ ያለ ዘዴ ይቀይሳሉ፡፡ ሁለተኛው ዘዴ ዕንቁላል መጣያቸውን በቀላሉ የማይታወቅ (የማይጠረጠር) ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ተልዕኮ የተመረጠችው ደግሞ ሴቷ የወባ ትንኝ ናት፡፡ ዕንቁላሉ ሳይፈለፈል ዕጫቸውን ሴቷ የወባ ትንኝ ሆድ ላይ ይጥላሉ፡፡
ዕጩን የተሸከመችው የወባ ትንኝ ሰው ነድፋ ደም ስትመጥ፣ ዕጩ፣ ከተጠቂው ሰውነት በሚያገኘው ሙቀት ይፈለፈልና ተጠቂው ሰውነት (ቆዳ) ላይ ይወድቃል፡፡ ከዚያም ቆዳውን ሰርስሮ ወደ ውስጥ በመግባት፣ ከቆዳ ስር ባሉት ሕዋሳት (ሴሎች) ውስጥ ሆኖ ለእድገት የሚያስፈልገውን ምግብ እያገኘ፣ ከ5 ሳ.ሜ በላይ ርዝመት እስከሚኖረው ድረስ ለበርካታ ሳምንታት እዚያው ይቆያል፡፡ ጥገኛ ትሎቹ የሚፈልጉትን ዕድገት ካገኙ በኋላ፣ በገቡበት አኳኋን ከቆዳ ውስጥ ወጥተው መሬት ላይ ይወድቁና ዕጭ ይፈጥራሉ፡፡ ከቀናት ቆይታ በኋላ ከዕጩ ውስጥ ቦትፍላይ ትሎች በመውጣት፣ አዲስ የሕይወት ዑደት (ላይፍ ሳይክል) ይጀምራሉ፡፡
9ኛ. ወስፋት (Ascaris Lumbricoides)፡- ይህን የእርሳስ መጠን ያለውንና መኖርያው ትንሹ አንጀት ውስጥ የሆነውን ሞላላ ጥገኛ ትል ብዙዎቻችን እናውቀዋለን፡፡ ይህ ጥገኛ ትል በሆድ ውስጥ ሆኖ ምግብ ስልቀጣን ወይም መፈጨትን በማስተጓጎል፣ ምግብ ለማግኘት አንቲትራፕሲን የተባለ ኬሚካል ያመነጫል፡፡ በዚህ አይነት የምግብ መተላለፊያ በመዝጋት ምግብ ያገኛል፡፡
ሴቶቹ የወስፋት ትሎች ከሶስት እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ሲኖራቸው፣ በየቀኑ 200ሺ ዕንቁላሎች ይጥላሉ፡፡ እነዚህ ዕንቁላሎች ከሰገራ ጋር ወጥተው አፈር ላይ ያድጋሉ፡፡ ዕንቁላሎቹ እድል አግኝተው እስኪፈለፈሉ ድረስ ለዓመታት እዚያው ይቆያሉ፡፡
ይህ ሞላላ ጥገኛ ትል በመላው ዓለም በዓመት ሁለት ቢሊዮን ሰዎችን የሚያጠቃ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ህፃናት ናቸው፡፡ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ትናንሽ ህፃናት ይቀጭጫሉ፤ የማሰብ፣ የማመዛዘንና የመረዳት ችሎታቸው ይቀንሳል፡፡
ወስፋት በሰውነት ውስጥ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሰው ከመጠን ያለፈ ትኩሳት፣ ለምሳሌ ከፍተኛ የወባ ትኩሳት ሲኖር ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከተለመደው ከሰገራና ከአፍ ውጪ በሌላ መንገድ ሊሰደዱ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ጉበት፣ ጣፊያ ወይም የሐሞት ከረጢት ከተወረሩ፣ የወስፋት ጉዳት ወይም ኢንፌክሽን በጣም አጣዳፊና አደገኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በስተቀር የወስፋት ህክምና ቀላል ነው፤ መበንዳዞል የተባለው መድኃኒት ከተወሰደ ድራሻቸው ይጠፋል፡፡
8ኛ. ዊፕ ዎርም (richuris trichiura) ይኼኛው ጥገኛ ተውሳክ ሞላላ ነው፡፡ መኖሪያው ትልቁ አንጀት ውስጥ ሲሆን፣ መገኛው ደግሞ ምድር ወገብ አካባቢ ነው፡፡ አንድ ህፃን አፈር ላይ የወደቀ ነገር አንስቶ ወደ አፉ እስኪከት ድረስ እንደ ሌሎች ሞላላ ትሎች ሁሉ፣ የዚህም ትል ዕንቁላል፣  ያለአንዳች እንቅስቃሴ አፈር ላይ ይቆያል፡፡
ይህ ጥናት ትል አብዛኛውን ጊዜ በህፃናት ላይ የሚያስከትለው ተቅማጥ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙ ማማጥ ፊንጢጣ ወደ ውጭ እንዲወጣ ያደርጋል፡፡ ወደ ውስጥ ለመመለስ ደግሞ የፊንጢጣ ጡንቻዎች ስለሚላሉ ጥረቱን ከባድ ያደርገዋል፡፡ ወደ ውጭ የወጣውና የረጠበው የፊንጢጣ ዙሪያ ባደጉ የጥገኛ ትሎች መወረር ደግሞ በጣም አስጠሊታና አዕምሮን የሚረብሽ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ሆኖም ግን በሽታው በጊዜ ከታወቀ ሕክምናው ቀላል ነው፡፡ ይህ አስቀያሚ ትል 50 ሚ.ሜ ሊረዝም ይችላል፡፡
7ኛ. የቻጋስ በሽታ (Trypanosoma Cruzi)፡- ይህ ባለ አንድ ሴል አጥቂ መገኛው ደቡብና መካከለኛው አሜሪካ ሲሆን መተላለፊያው ደግሞ ደም የምትመጥ “Kissing bug” የተባለች በራሪ ነፍሳት ናት፡፡
የዚህች ነፍሳት መጥፎ ባህርይ በምትመገብበት ጊዜ (ደም ስትመጥ) ሰውን መመረዟ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ጥገኛ  ትሉ ወደ ተጠቂው የደም መዘዋወሪያ ገብቶ ቻጋሲ ዲዝስ ለመፍጠር በጣም የሚፈልገው አጋጣሚ ነው፡፡
ይህ ጎጂ አውሬ ወደ ሰውነት ክፍል ይጓዝና በአቅራቢያው ያገኛቸውን ሴሎች በመውረርና በተጠቃው አካባቢ የፍቅር ምልክት (Roman’s sign) የተባለ እብጠት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
የዚህ አውሬ ጥቃት በጣም አደገኛ የሚሆነው፣ ወደ ልብና የነርቭ ሲስተም ወይም ወደ ትንሹና ትልቁ አንጀት ከሄደ ነው፡፡ በነርቭ ሴሎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የሰውነት ብልቶቻችን (ልብ፣ ሳንባ፣ ኩላሊት፣…) ተግባራቸውን እንዲያቋርጡና ከነበራቸው መጠን በላይ እንዲያድጉ ያደርጋል፡፡ የዚህ አውሬ ጥቃት ብዙ ጊዜ ከቆየ የፊንጢጣ (ሜጋ ኮብሎን) የምግብ መተላለፊያ (ሜጋ ኤሶፋጋስ) እንዲጎዳና ልብ ከመጠን በላይ እንዲያድግ ያደርጋል፡፡
6ኛ. ጊኒ ዎርም (Darcunculus medinesis):- እነዚህ ሞላላ ጥገኛ ትሎች፣ ዕንቁላላቸውን ለማስተላለፍ የሚጠቀሙት ብዙ ጊዜ የረጋ ኩሬ ውሃ አካባቢ የሚገኙትን የውሃ ትንኞች ነው፡፡ እነሱን በመንደፍ ዕጮቻቸውን ወደ ትንኞቹ ያስተላልፋሉ፡፡ ትንኞቹ ደግሞ የጊኒ ዎርም ዕጮች እንደያዙ ውሃው ላይ ይሞታሉ፡፡
አንድ ሰው የጊኒ ዎርም ያለበት የረጋ ውሃ ከጠጣ፣ ሰውነት፣ ዕጮቹን የያዘውን ትንኝ ሲፈጭ ወይም ዳይጀስት ሲያደርግ ትሎቹ ነፃ ይወጣሉ፡፡ ነፃ የወጡት ሴትና ወንድ ትሎች ከጥቂት ወራት በኋላ ግንኙነት ይፈጥራሉ፡፡ ወንዶቹ ግንኙነቱን ካደረጉ በኋላ ከሰውነት ጋር ይዋሃዳሉ፡፡ ሴቶቹ ግን ወደ እግርና ወደ እግር መዳፍ ይጓዛሉ፡፡ እዚያ ከደረሱ በኋላ ዕንቁላላቸውን የሚጥሉበትን ስፍራ ያሳብጣሉ፡፡ እብጠቱ የሚያቃጥል ኃይለኛ ሕመም ስለሚፈጥርበት፣ ሰውዬው ፈውስ ፍለጋ ወደ ውሃ ስፍራ ይሄዳል፡፡ በዚህ ጊዜ እብጠቱ ይፈነዳና ዑደቱ እንደገና ይጀመራል፡፡
ብዙ ጊዜ ህክምናው የትሉን ጭንቅላት ቀጭን ነገር ላይ ጠቅልሎ ትሉ ተነቅሎ እስኪወጣ ድረስ ቀጭኑን ነገር ማዞር ነው፡፡ እስካሁን የተመዘገበው የጊኒ ትል ርዝመት 78 ሴ.ሜ ነው፡፡
5ኛ. ዝሆኔ ወይም ሞላላ ትል (wicheria bancrofti)፡- የዚህ ሞላላ ትል መኖርያ፣ ሰውነታችን ተጠቅሞ የሚያስወጣውን ተረፈ ምርት ለማስወገድ በሚጠቀምበት ነጭ የደም ሴል በሆነው ንፁህ የሰውነት ፈሳሽ (ሊፍም-Lymph) ውስጥ ነው፡፡ እነዚህ ትሎች ካደጉ በኋላ ለዓይን የማይታዩ ጥቃቅን (Microfilariae) ህዋሳት እየፈለፈሉ ለ10 ዓመታት ይኖራሉ፡፡ ጥቂት ህዋሳት ደግሞ ደም ውስጥ ይገቡና የወባ ትንኝ ሰው ሲነድፍ፣ ከደም ውስጥ ወደ ትንኟ ይገቡና ወደ በሽታ ፈጣሪ ዕጭነት ይቀየራሉ፡፡
የተመረዙ ዕጮችን የተሸከመችው የወባ ትንኝ በሌላ ጊዜ እንደገና ሰው ስትነድፍ፣ ዕጮቹ፣ የወባዋ ሰለባ ወደሆነው ሰው ይተላለፋሉ፡፡ ከዚያም ተነድፎ ወደቆሰለው ቦታ ይዋኙና መኖርያቸው ወደሆነው ነጭ የደም ሴልና ንፁህ ሰውነት ፈሳሽ መያዣ ይገቡና እስከ እርጅናቸው እዚያው ይኖራሉ፡፡
ያረጀው ሞላላ ትል ሲሞት፣ የፈሳሹ መተላለፊያ ቀልቶ ያብጥና የፈሳሹን ፍሰት ይቀንሳል፡፡ ሁሉም ያረጁት ትሎች ሲሞቱ፣ የፈሳሽ መተላለፊያው ሙሉ በሙሉ ይዘጋል፡፡ ከዚያም እብጠቱ ይቀጥልና እግሮች ትልቅ ይሆናሉ፣ የሰውነት ቆዳ ደረቅ ይሆንና ይተጣጠፋል፡፡
4ኛ. ኤስፖንዲያ (Leighmania braziliensis)፡- ይህ ባለ አንድ ሴል ጥገኛ ትል ወደ ሰውነት የሚገባው የአሸዋ ዝንቦች (sand fly) በነከሱት ቀዳዳ ነው፡፡ ጥገኛ ትሎቹ ሰውነትን ከመረዙ በኋላ፣ በሰውነት ውስጥ በመዘዋወር የበሽታ መከላከያ አቅም የሚፈጥሩትን ህዋሶች (ሴሎች) ወርረው ይመርዛሉ፡፡ እነዚህ የተመረዙ ሴሎች ወደ አፍ፣ ፊንጢጣና ወደ ሽንት ቧንቧ ይጓዛሉ፡፡ ጥገኛ ትሎቹ እዚያ አምሳያቸውን አዲስ ትሎች ፈጥረው፣ ህዋሳቱ ተመርዘው እንዲያመረቅዙ (አልሰር) እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ጥገኛ ትል ካልታከመ በስተቀር አደገኛና አጣዳፊ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡
በዚህ ጥገኛ ትል የተመረዘ አፍ ካልታከመ በስተቀር በከፍተኛ ደረጃ ያመረቅዝና የላይኛው የአፍ ሪያ ሊናድ ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ ‹ኤስፓንዲያ› የሚባል ሲሆን የሚገኘውም የሕክምና ሰዎች አዘውትረው በማይገኙበት ጭልጥ ያለ ገጠር ነው፡፡ አንዴ ህክምና ካገኘ የሚድን ሲሆን የአፍ መተላለፊያውን በቀዶ ህክምና ወደ ቀድሞው ደረጃ መመለስ ይቻላል፡፡
3ኛ. የአሳማ ኮስ ትል (Taenia Solium)፡- በትንሷ አንጀት የሚኖረው የአሳማ ኮሶ ትል 4 ሜትር ሊረዝም ቢችልም በአንፃራዊነት ሲታይ አይጎዳም ማለት ይቻላል፡፡ ሰዎች በዚህ ትል የሚያዙት ትሉ ያለበትን ጥሬ ወይም በደንብ ያልበሰለ የአሳማ ስጋ በመብላት ነው፡፡
ወጣት የሆነው የዚህ ኮሶ ትል በህብረ ህዋስ ውስጥ ካለው ቅርፊት ይወጣና በሶስት ወር ሙሉ ትል እስከሚሆን በሚቆይበት ትንሹ አንጀት ግድግዳ ላይ ይጣበቃል፡፡ ዕንቁላሎቹ ናቸው ትንሽ የበለጠ አደገኛ የሆኑት፡፡ ዕንቁላሎቹ ከተበሉ በጣም ጥቃቅን ዕጮች ከደም ጋር እየተዘዋወሩ፣ መኖሪያቸውን የልብ፣ የአንጎልና የዓይን ህብረ ህዋሳት በማድረግ እስከ ወጣትነት ያደርጋሉ፡፡ ከእነዚህ አደገኛ ጥገኛ ትሎች መገላገል የምንችለው መድኃኒት ወስደን ከሰገራ ጋር በማስወጣት ብቻ ነው፡፡
2ኛ. የውሻ ኮሶ ትል (Echinococcus granulosus)፡- ይህ ውሾችን የሚያጠቃ ትንሽ ትል ሲሆን ወደ ሰውም ሊተላለፍ ይችላል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የዚህ ትል አስተላላፊ በጎች ናቸው፡፡ ይህ ትል ያለበት በግ ሲታረድ፣ ወጣቶቹን ትሎች የያዘውን ጉበቱን ውሾች ይበሉታል፡፡        
አንዴ ውሾቹ ከበሉትና ትሉ መኖሪያ ካገኘ በኋላ፣ ወጣቶቹ ትሎች ከቅርፊታቸው ውስጥ ይወጡና በውሻው አንጀት ላይ ተጣብቀው እስከ አዋቂነት ያድጋሉ፡፡ በኮሶ ትሉ የተጠቁት ውሾች በሺዎች የሚቆጠሩ አዋቂ የኮሶ ትሎች ማኖር ይችላሉ፡፡ አዋቂዎቹ ትሎች እንቁላል ሲጥሉ እንቁላሎቹ ከውሻው ሰገራ ጋር ይወጣሉ፡፡ በጎች ደግሞ እንቁላል ያለበትን ቅርፊት በመብላት ትሉን ወደ ውስጣቸው ያስገባሉ፡፡
የበግ አርቢዎችም ከቅርፊቱ ጋር ንኪኪ ሲያደርጉ በኮሶ ትሉ ሊያዙ ይችላሉ፡፡ ቅርፊቱ ከተሰነጠቀ ኢንፌክሽኑ አንጎልና ሳንባ ወደ መሳሰሉ ሌሎች ብልቶች በመሰራጨት ሞት ሊያስከትል ይቻላል፡፡
1ኛ. የዓይን ትል (Loa Loa)፡- አብዛኛውን ጊዜ ሞላላ ትሎች የሚኖሩት ከቆዳ ስር ሲሆን በሰውነት ውስጥ ሲዘዋወሩ የሚያደርሱት ጉዳት ቀላል ነው፡፡ ሴቶች ትሎች የሚጥሏቸው ዕጮች ከደም ጋር ይቀላቀሉና በአጋዘን ዝንቦች ይበላሉ፡፡ ዕጮቹ መርዛማ እስኪሆኑ ወደ አፍ አካባቢ ጡንቻ ከመሸጋገራቸው በፊት በዝንቦች የክንፍ ጡንቻዎች ላይ ያድጋሉ፡፡ በትሉ የተጠቃው የአጋዘን ዝንብ፣ ሰውን ሲነክስ ዕጮቹ እየዳኹ ወደ ቆዳና ዝንቡ ወደነከሰው ቁስል ይሄዳሉ፡፡ በበሽታው የተጠቃ ሰው በመስታወት ዓይኑን ሲያይ፣ ትሉን ዓይኑ ውስጥ  ሊያይ ይችላል፡፡ ትሎች ዓይን ውስጥ ከገቡ በቀዶ ህክምና መውጣት አለባቸው፡፡   

Read 6280 times