Saturday, 21 June 2014 14:42

ጎል ለምን በዛ?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

20ኛው ዓለም ዋንጫ በጎል ብዛት የተንበሻበሸ ሆኗል፡፡ ትናንት ከምድብ 4 የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች በፊት በተደረጉት 23 ግጥሚያዎች ላይ 66 ጎሎች ከመረብ አርፈዋል፡፡ በአማካይ በአንድ ጨዋታ 2.87 ጎሎች ማለት ነው፡፡ ዓለም ዋንጫ በ32 ቡድኖች በሚደረጉ 64 ጨዋታዎች መካሄድ ከጀመረ ወዲህ በየውድድሩ አንድ ጨዋታ አማካይ የጎል ብዛት 2.5 ነው፡፡  በ2002 እኤአ ላይ 2.5፤ በ2006 እኤአ 2.3 እንዲሁም በ2010 እኤአ 2.3 ጎሎች በአንድ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ በአማካይ ሲመዘገብ ነበር፡፡  ለጎሎች መብዛት የተለያዩ ምክንያቶችም እየቀረቡ ናቸው፡፡ ብራዙካ የተባለችው ኳስ አመቺነት፤ የቡድኖች አጨዋወት በአመዛኙ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ መሆኑ፤ በርካታ ምርጥ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች በየብሄራዊ ቡድኖቻቸው አስገራሚ ብቃት ማሳየታቸውና የብራዚል ስታድዬሞች ማራኪ ድባብ ይጠቀሳሉ፡፡ ብራዚላዊ ዚኮ  በዓለም ዋንጫው ጎሎች የበዙት የየብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች ግብ እንዳይቆጠርባቸው ከመከላከል ይልቅ አስቀድመው በማግባት ለማሸነፍ በተከተሉት ታክቲክ መሆኑን አስተያየት ሰጥቷል፡፡ ብዙዎቹ አሰልጣኞች የቡድናቸውን አጨዋወት በማጥቃት ላይ እንዲመሰረት ማድረጋቸውን ታዝቢያለሁ ብሏል ዚኮ፡፡ የጎሎች መብዛት የዓለም ዋንጫውን የፉክክር ድባብ አድምቆታል፡፡ በበየጨዋታው አጓጊ ድራማዎችና ልብ ሰቃይ ትእይንቶች እየተፈጠሩ ናቸው፡፡
በኮከብ ግብ አግቢነቱ ፉክክር ሶስት ተጨዋቾች በሶስት ጎሎች ተያይዘዋል፡፡ የጀርመኑ ቶማስ ሙለር እና ሆላንዳውያኑ ሮበን ቫን ፕርሲ እና አርያን ሩበን ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው ሁለት ጎሎች ያስመዘገቡት 7 ተጨዋቾች ደግሞ   የብራዚሎ ኔይማር፣ የአውስትራሊያው ቲም ካሂል፣ የኮሎምቢያው ጀምስ ሮድሪጌዝ፤ የክሮሽያው ማርዮ ማንዱዚክ፣ የፈረንሳዩ ካሬም ቤንዜማ፤ የአይቬሪኮስቱ ጀርቪንሆ እና የኡራጋዩ ሊውስ ሱዋሬዝ ናቸው፡፡



የፊፋ  ሽልማትና ቦነሶች
ለሽልማትና ለክለቦች ክፍያ በፊፋ የተዘጋጀው 576 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በ19ኛው ዓለም ዋንጫ ከነበረው በ37% ጨምሯል፡፡  ተጨዋቾቻቸውን ለሚያሳትፉ ክለቦች  ፊፋ 70 ሚሊዮን ዶላር እንደየደረጃው የሚከፍል ሲሆን ይኸም ከ4 ዓመት በፊት ከነበረው በ75 % ጭማሪ ታይቶበታል፡፡ ፊፋ በዓለም ዋንጫው ለሚሳተፉ ብሔራዊ ቡድኖች ለዝግጅት የሚሆን አስቀድሞ  1.5 ሚሊዮን ዶላር  ከመስጠቱም በላይ በውድድሩ ተሳታፊነት ብቻ ለ32ቱ አገራት ለእያንዳንዳቸው 8 ሚሊዮን ዶላር ይከፍላቸዋል፡፡ በገንዘብ ሽልማቱ ዝርዝር አከፋፈል መሰረት ዋንጫውን የሚያሸንፍ 35 ሚሊዮን ዶላር ሲከፈለው  ፤ ለሁለተኛ 25ሚ ዶላር፤ ለሦስተኛ ደረጃ 22 ሚሊዮን ዶላር ለ4ኛ ደረጃቨ 20 ሚሊዮን ዶላር  ይበረከታል፡፡ በሩብ ፍፃሜ የሚሰናበቱ 4 ቡድኖች እያንዳንዳቸው 14 ሚ. ዶላር ፤በጥሎ ማለፍ የሚሰናበቱ 8 ቡድኖች ለእያንዳንዳቸው 9 ሚ ዶላር እንዲሁም ከምድብ ለሚሰናበቱ 16 ቡድኖች 8ሚ.ዶላር ይከፋፈላል፡፡
የማበረታቻ ቦነስ እና ሌሎች ክፍያዎችን ለመስጠት ላለፉት 6 ወራት በየአገሩ ቃል ሲገባ ነበር፡፡  የስፔን ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች  የሻምፒዮናነት ክብራቸውን ካስጠበቁ በነፍስ ወከፍ 979ሺ ዶላር እንደሚታሰብላቸው ቃል መገባቱ  ከፍተኛው ቦነስ ነበረ፡፡ በትልልቅ ውድድሮች ላይ ከፍተኛ ግምት እየተሰጠው ብዙ  ለማይቀናው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንም  ለዋንጫ ድል የቀረበው ቦነስ ለእያንዳንዳቸው 587ሺ ዶላር ነው፡፡
 በአዘጋጇ ብራዚል  448ሺ ዶላር ቦነስ እንደምትሰጥ ሲገለፅ ለፈረንሳይ ቡድንም በተመሳሳይ መጠን  ቀርቧል፡፡ በጀርመን  408ሺ ዶላር ፤  በአሜሪካ 405ሺ ዶላር  እንዲሁም በሆላንድ ደግሞ 371ሺ ዶላር ቦነስ ለእያንዳንዱ ተጨዋች በነፍስ ወከፍ  ለመስጠት ተዘጋጅቷል፡፡
በማበረታቻ የቦነስ ክፍያዎች ዙሪያ በተለይ ብሔራዊ ቡድኖች እና ፌደሬሽኖቻቸው ከፍተኛ ውዝግብ መግባታቸው የተለመደው በአፍሪካ ነው፡፡ የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች በፌደሬሽን በኩል ስለሚሰጣቸው ክፍያ ውዝግብ ገብተው የምንፈልገው ካልተሟላ ልምምድ እናቆማለን ብለው መነጋገርያ ሆነዋል፡፡ በመጨረሻም የካሜሮን እግር ኳስ ፌደሬሽን ለእያንዳንዱ ተጨዋች በዓለም ዋንጫው አጠቃላይ ተሳትፎ 91.5ሺ ዶላር በመመደብ ውዝግቡን ሲያበርድ የተጨዋቾቹ ፍላጎት እስከ 160ሺ ዶላር ነበር፡፡  የጋና ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች በበኩላቸው በየጨዋታው በሚያስመዘግቡት ድል የሚሰጣቸው የቦነስ ክፍያ 30% አስቀድሞ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል፡፡

Read 1505 times