Saturday, 05 July 2014 00:00

ቪያግራና ‘ምስር’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(10 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…መቼም ምዕራባውያኑ እንደ ሩስያዎች መቀለጃ ያላቸው አይመስልም፡፡ ይቺን ስሙኝማ…በአንድ ወቅት የሩስያ መሪ የነበሩት ብሬዥኔቭ አንድ ስነ ስርአት ላይ ረዘም ያለ ንግግር ያደርጋሉ፡፡ ከዚያ ንግግሮችን የሚጽፍላቸውን ሰው ይጠሩና “ጻፍልኝ ያልኩህ የአሥራ አምስት ደቂቃ ንግግር ነበር፡፡ ለምንድነው የአርባ አምስት ደቂቃ ንግግር የጻፍክልኝ?” ሲሉ ያፈጡበታል፡፡ ንግግር ጸሃፊውም “ጌታዬ፣ የአሥራ አምስት ደቂቃ ንግግር ነው የሰጠሁዎት…” ይላል፡፡ ብሬዥኔቭም “ታዲያ ለምን አርባ አምስት ደቂቃ ፈጀብኝ?” ሲሉት ሲፈራ፣ ሲቸር ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…“ጌታዬ የንግግሩን ሦስት ቅጂ ነው የሰጠሁዎት፡፡”
ልቤ ጠረጠረ…የምር ልቤ ጠረጠረ! እኛ ዘንድ አንዳንድ ተናጋሪዎች አምስቱንም ቅጂ ነው እንዴ የሚያነቡልን! እንዲህ አይነት ነገር መኖሩን መች አወቅንና!  ለነገሩ ያንን ሁሉ ለማንበብም ‘አቅም’ ያስፈልጋል፡፡
ክፋቱ ዘንድሮ አቅም ጠፋ፡፡ አቅም ሲጠፋ ደግሞ ‘ጉልቤ’ በዛ!
ስሙኝማ…ሆሊዉድ እስከዛሬ ‘ኸልፕለስ’ ምናምን የሚል ፊልም አልሠራ ከሆነ እነስፒልበርግ እኛ ዘንድ ቢመጡ አሪፍ ነው፡፡ አምስት መቶ ምናምን ክፍሎች ያሉት…አይደለም የፈጠራ ሥራ፣ ‘ሪያሊቲ ሾው’ ምናምን የሚሉትን ሊሠሩ ይችላሉ፡፡
የምር…አቅመ ቢስነት ጨረሰንማ! ምን አቅመ ቢስ ያልሆንንበት ነገር አለ! ለነገሩ ሰባ ስድስት ሚሊዮናችንን አይደል “ድሆች ናቸው” ያሉን፡፡ አቅም ብናጣ ምን ይገርማል! ኮሚክ እኮ ነው…በድሆች ብዛት የሚቀድሙን አምስት አገሮች ናቸው አሉ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ ክሊኒኩና የባህል መድሀኒት አዋቂው ሁሉ “ለስንፈተ ምናምን’ መፍትሄ አለን…” የሚሉት…አለ አይደል… በነገርዬው በኩል ያለው ‘አገር አቀፍ’ አቅም ይሄን ያህል ወርዷል ማለት ነው!
እኔ የምለው…ነገርን ነገር ያነሳዋል አይደል የሚባለው…ይሄ ቪያግራ የሚሉት ነገርዬ መጀመሪያ የታሰበው ለ‘ሲኒየር ሲቲዘንስ’ አልነበረም እንዴ! (ለነገሩ ምን መሰላችሁ…ይሄ ‘ጂም’ የሚሉት ነገር በዛና ‘ሲኒየሩ’ን ሁሉ ‘ጁኒየር’ እያደረገው ነው አሉ! እነሆ በረከት ምነው አይበዛሳ! ስሙኝማ…እንትናና እንትናዬዎች ፍለጋ በየሁለትና በየሦስት ወሩ ‘ጂም’ የሚለዋውጡ አሉ የሚባለው እውነት ነው እንዴ!) በአንድ ወቅት “ረጅም ዘመን ያገለገለ አሮጌ ካሚዮን ሞተር በማኖቬላ ነው የሚነሳው…” ያልከኝ ወዳጄ…ጥሬ ሥጋ በሚጥሚጣ ሞክረሀል፡ ያው እሱም የማኖቬላ (ጣልይንኛውን ምናምነኛ አደረግሁት እንዴ!) አገልግሎት ይሰጥ እነደሁ ብዬ ነው፡፡
እናላችሁ…የከተማው ወጣት ሁሉ (ከአንዳንደ ‘ጩጬዎች’ ጭምር)  ‘ቪያግራ’ ቃሚ ሆነና አረፈው!
ስሙኝማ...እንደው ‘የፈረንጅ ነገር’ ሆኖብን እንጂ አሁን ቪያግራን የሚተካ አገር በቀል ብልጠት ጠፍቶ ነው! ደግሞ ላልጠፋ ምስር፡፡ ከነተረቱ እኮ “ምስር…ይቀስር” ይባላል! ቂ…ቂ…ቂ….
በሁሉም ነገር አቅም የሚጨምር ‘ምስር’ ይላክልንማ!
የምር ግን፣ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ጥያቄ አለን…በተለምዶ ምስር ከምግብነት ውጪ “አለው” የሚባለው ጥቅም ያው የታወቀ ነው፡፡ ምን ግርም ይልሀል አትሉኝም… እንደው አንድ እንኳን ተመራማሪ “ይህ ነገር እውነት ይሆን እንዴ!” ብሎ ምርምር አደረገ ወይ እያደረገ ነው ሲባል የማንሰማሳ!! ልክ ነዋ…እንዲሀ አይነት ‘ወሬ’ እኮ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ የሚመጣው ዝም ብሎ (‘ከመሬት ተነስቶ’ እንደማለት) አይደለም፡፡
እኔ የምለው… ቪያግራ የደም ዝውውርን አፋጥኖ ምናምን (‘ደም አፍልቶ’ እንደማለት) ‘ቁልቁል’ ይሰደዋል አይደል የሚባለው?
ልጄ፣ ዘንድሮ በሌላ ሌላ ‘ብሮባጋንዳችንን’ ያፍርሱብን እንጂ ‘ደም በሚያፈሉ’ ነገሮች እጥረት እንኳን አንታማም፡፡ አይደለም ለእኛ ለእነሱም እንተርፋለን፡፡ ክፋቱ ‘ደማችን ሲፈላ’ የሚወጣው ሽቅብ ሆነ እንጂ! ቢቻል ‘መንገዱ ዝግ ነው’ የሚል ለጥፎ ወደ ቁልቁል የሚመለስበትን ዘዴ ቢፈጥሩልን አሪፍፈ ነበር፡፡  እሱን ዘዴ ብንደርስበት የቪያግራ ገበያ በዘጠና አምስት በመቶ ይቀንስ ነበር፡፡
ደግሞላችሁ… ጠጅ አለ…ደግሞ ዳግም አረቄ አለ…ደግሞ የሆነ ስራ ስርም አለ አሉ…ደግሞ አዋቂ ዘንድ ሄዶ ማስተበተብ አለ…ምን የሌለን ‘መፍትሄ’ አለ! እኔ የምለው…መፋቂያና ነገርየውን ምን እንደሚያገናኛቸው የመፋቂያውን ጥቅም የሚያብራሩልን ሻጮቹ ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ ‘መፋቂያ’ን እንሰማ የነበረው እንደ ‘መስተፋቅር’ ነው እንጂ እንደማይዋጠው ቪያግራ አልነበረም! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ… ‘በስንፈተ ምናምን…’ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ነገር አቅም አነሰን፡፡
ባለገንዘቦች፣ ባለጊዜዎች፣ ባለወንበሮች የስሙኒ ኳስ ነገር ሲያደርጉን… “እንዲህ ልታደርጉኝማ አትችሉም!” ለማለት አቅም አነሰን፡፡ “…አገር ይሸፍታል እንኳን ሰው ሲበደል…” የሚለው አትንኩኝ ባይነት ከታሪክነት ወደ አፈ ታሪክነት እየተለወጠ ነው፡፡
የተሰመረላቸውን ድንበር አልፈው፡ በግምጃ ቤትነት ሹመት የንጉሠ ነገሥትነት ስልጣን ሲያሳዩን “እንዲህ የመወሰን ስልጣን የላችሁም…” ለማለት አቅም እያነሰን…መጫወቻ ሆነን ቀረን!
በሁሉም ነገር አቅም የሚጨምር ‘ምስር’ ይላክልንማ!
የፈራንካና የወንበር ‘ጉልቤዎቹ’ በስንት ልፋት ያገኘናቸውን (ቂ…ቂ…ቂ…) እንትናዬዎቻችንን ከዓይናችን ስር ‘ነጥቀው’ ሲወስዱብን…“በህግ አምላክ፣” “ወድቃ በተነሳችው ባንዲራ፣” የማለት አቅም እንኳን አነሰን፡፡ “በአባት አገርና በሚስት የለም ዋዛ…” የሚለው በዘመኑ አገር ያቀና አባባል ቀርቶ…አለ አይደል… አሁን ነገርዬው “ከብት እነዳ በዬ፣ ልጅ አሳድግ ብዬ… ሚስቴን ዳርኩለት እህቴ ናት ብዬ፣” ሆኗል፡፡ አቅመ አነሰና! “አደባለቀውና እርጥቡን ከደረቅ…” አይነት መብት ማስከበር ‘የአባቶች ታሪክ’ ብቻ ሆነኣ!
በሁሉም ነገር አቅም የሚጨምር ‘ምስር’ ይላክልንማ!
…“መብቴንማ ስትንዱ አላይም…” አይነት ነገር…አፍ አውጥቶ መናገር እንኳን እየፈራን ነው፡፡ አቅመ አነሰና! ለ‘ስንፈተ እንትን’ እንደሚሆነው ቪያግራ ከአጠቃላይ አቅመ ቢስነት የሚያወጣን ‘አገር በቀል ምስር እንኳን አጣና! (ቂ…ቂ…ቂ…) ዘንድሮ…አለ አይደል… ካለመናገር ከሚቀር ደጃዝማችነት ይልቅ ነገርዬው “በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ…” እየሆነ አቅም አነሰን፡፡
ስሙኝማ…የፈረደባት ሩስያ ነው አሉ፣ ሰውዬው በቀቀኗ፣ ማለት ሰው የሚናገራቸውን ነገሮች ደግማ የምትናገር ወፍ፣ የት ትግባ የት ትሰወርበታለች፡፡ እናላችሁ…ትንፋሽ እያጠረው ኬ.ጂ.ቢ. ቢሮ ይሄዳል፡፡ እዛም ሲደርስ “ተናጋሪ ወፌ ጠፋችብኝ፣” ሲል ያመለክታል፡፡ የኬጂቢ ሰዎችም “ይሄ እኛን አይመለከትም፣ ሄደህ ለፖሊስ አመልክት” ይሉታል፡፡ እሱ ሆዬም “እሺ ለፖሊስ አመለክታለሁ፣ ግን ለእናንተ ልናገር የምፈልገው ነገር አለ፣” ይላል፡፡ እንዲናገርም ይፈቅዱለታል፡፡ እሱም “እዚህ የመጣሁት ተናጋሪ ወፏ በምትናገረው ማንኛውም ነገር እንደማልስማማ ለማሳወቅ ነው፣” ብሎ አረፈላችሁ፡፡
በቀቀን ባይኖረንም… አይደለም የተናገርነው ያሰብነው እንኳን በ‘ሹክ፣ ሹክ’ ጣጣ ያመጣል በሚል “መከበር በከንፈር” እያልን ነው፡፡ አቅም አነሰና!
በሁሉም ነገር አቅም የሚጨምር ‘ምስር’ ይላክልንማ!
መብራት እንዳሰኘ ሲጠፋ “ግብሬን እየከፈልኩ፣ ወርሀዊ ግዴታዬን እየተወጣሁ እንዲህማ ልታደርጉኝ አትችሉም!” ማለት እንኳን እያቃተን ነው፡፡ አቅም አነሰና!
የመሥሪያ ቤት ዘበኛ ያለምንም ምክንያት…አለ አይደል… ስላሰኘው ብቻ “መግባት አይቻልም…” ከማለት አልፎ ቆመጡን ሲወዘውዝብን “ቀጠሮ እያለኝ ማስገባትና ያለማስገባት የአንተ ሀላፊነት አይደለም…” ማለት እንኳን እያቃተን ነው፡፡ አቅም አነሰና!
በሁሉም ነገር አቅም የሚጨምር ‘ምስር’ ይላክልንማ!
እናላችሁ… ባነሰን አቅም የራሳችንን መፍትሄ እንኳን መፈለግ አቅቶናል፡፡ ነገርዬው ‘በምስር ፈንታ ቪያግራ’ ነገር ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ምስር የሀበሻ ቪያግራ ነዋ!
እንግዲህ ጨዋታም አይደል… መቼም እንደ ዘንድሮ ለፈረንጅ ‘ጀርባችን የጎበጠበት’ ዘመን የነበረ አይመስለኝም፡፡ ኮሚክ እኮ ነው…እኛስ ሰፊ ህዝቦች ፈረንጅን አይደለም ብቻህን ከእነቤተሰብህና ሚጢጢ ውሾችህ ጋር እንኮኮ ላድርግህ የምንለው ቢሞረሙረን፣ ጉሮሯችን ቢደርቅ ይሆናል፡፡ በኦፊሴል “የእንትን ቱሪስቶች አደነቁን…”  “የስብሰባው ተካፋዮች ነፍስ የሆነች አገር ነች አሉ…”  “የእንትን መንግሥት መቶ ምናምን ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ሊሰጡን ነው…” ምናምን ማለት ሁሉ የሚበዛው ያው ‘ጀርባ ሲጎብጥም’ አይደል! እና ጀርባ ሲጎብጥ ምስርን ትቶ ቪያግራ መቃም ይበዛል፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…እንደ ዓቢይ ብሔራዊ ጉዳይ ሆኖ ቪያግራ ወደ መሠረታዊ ፍላጎትነት ለመለወጥ ሲንፏቀቅ…አለ አይደል… ቪያግራው እንኳን ቀርቶብን በሁሉም በኩል አቅም የሚጨምር ‘ምስር’ ይላክልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 9331 times