Tuesday, 08 July 2014 08:05

ዶክተሩ ስለፓርኪንሰን በሽታ ምን ይላሉ?

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ፓርኪንሰን የተባለው በሽታ ስያሜውን ያገነው ከተመራማሪው ሚስተር ፓርኪንሰን እንደሆነ ይነገራል፡፡ ቀደም ሲል በሽታው በአገራችን ብዙ ትኩረት ያላገኘና ብዙ ሰው የማያውቀው ነበር፡፡ ሆኖም ከጊዜ ወደ ጊዜ የታማሚዎቹ ቁጥር እየበረከተ በመምጣቱ ከሶስት ዓመት ወዲህ መጠነኛ ትኩረት ሊያገኝ ችሏል፡፡  በ32 ዓመታቸው በበሽታው የተጠቁት ወ/ሮ ክብራን፤
“የፓርኪንሰን ታማሚዎች ማህበር” መስርተው ታማሚዎችን ለመርዳት እየተንቀሳቀሱ
ይገኛሉ፡፡ ስለበሽታው ምንነት ህብረተሰቡ እንዲያውቅ፣ ለጤና ባለሙያዎች ለሚዲያ ሰዎችና ለበጎ ፈቃደኞች ስልጠና ይሰጣል፡፡ ማህበሩ የመድኃኒትና የገንዘብ እርዳታ በማፈላለግና ህብረተሰቡን በማንቃት በበሽታው ተይዘው እቤት የቀሩትን ሰዎች ወደ ህክምና ለማምጣት እየተጋም ይገኛል፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በብሄራዊ ሆቴል ለጋዜጠኞች በተሰጠው የግማሽ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ የማህበሩ በጎ ፈቃደኛ ከሆኑት ከዶክተር ዳዊት ክብሩ ጋር በፓርኪንሰን ህመም መንስኤዎችና መፍትሄዎች ዙሪያ ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡  

ፓርኪሰን የሚባለው በሽታ ምንድን ነው?
በሰውነት ውስጥ “ኒውሮ ዲጀነሬቲቭ” የሚባሉ በሽታዎች ይከሰታሉ፡፡ ዝግመታዊ በሆነ ሂደት አዕምሮ ውስጥ የሚገኝ “ባዛል ጋንግሊያን” የሚባል ክፍል ውስጥ የሚኖሩ የነርቭ ሴሎች አሉ፡፡ እነዚህ ሴሎች “ዱፓሚን” የሚባል ንጥረ ነገር ያመነጫሉ። እነዚህ ሴሎች ሲሞቱ ደግሞ ንጥረ ነገሩ መመረት ያቆማል፡፡ሰ የዚህ ንጥረ ነገር ማነስ ወይም አለመኖር ለፓርኪንሰን በሽታ ያጋልጣል፡፡
“ዱፓሚን” የተባለውን ንጥረ ነገር ዋነኛ ጥቅሙ ምንድን ነው?
ንጥረ ነገሩ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው፡፡ ዋነኛው ጥቅሙ ግን በሞተርነት የጡንቻዎችን እንቅስቃሴ ማቀላጠፍና ማነቃቃት ነው፡፡ ዱፓሚን ሲያንስ ግን የበሽታው ዋና ዋና ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ፡፡
ምልክቶቹን ቢጠቅሱልኝ?
ለምሳሌ መንቀጥቀጥ፣ የጡንቻ መገታተር፣ የእንቅስቃሴ ፍጥነት መፍዘዝና የራስን ሚዛን አለመጠበቅና የመሳሰሉት ዋና ዋና ምልክቶች ናቸው፡፡
ዱፓሚን የተባለው ንጥረ ነገር የሚያንሰው አምራች ሴሎች ሲሞቱ ነው ብለውኛል፡፡ ሴሎቹ የሚሞቱበት ምክንያትስ ምን ይሆን?
ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ “ኻዛል ጋንግሊያ” የሚባለው የአዕምሮ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ዱፓሚን አምራች ሴሎች ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ቀስ በቀስ ይሞታሉ፡፡ ከ80 በመቶ በላይ ሲሞቱ ደግሞ የንጥረ ነገሩ እጥረት ይከሰትና የበሽታው ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ፡፡
በሽታው በአብዛኛው በየትኛው የእድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን ያጠቃል?
እድሜያቸው ከ60 በላይ የሆኑ ሰዎች በብዛት በበሽታው ይጠቃሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን በ20 እና በ30 አመት ዕድሜ የሚገኙ ሰዎችም በበሽታው የሚጠቁበት ጊዜ አለ፡፡ ከ90 በመቶ በላይ ግን ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ላይ ይከሰታል፡፡
በሽታው በሴቶች ላይ ይበረታል ወይስ ወንዶችን ያጠቃል?
ከሴቶች በበለጠ ወንዶችን የሚያጠቃ ሲሆን ከተማ ከሚኖሩ ገጠር የሚኖሩት ላይ ይበረታል፡፡
በአገራችን ተላላፊ ያልሆኑት በሽታዎች የሚባሉት እንደ ስኳር፣ ኩላሊት፣ ደም ግፊትና የመሳሰሉት ውስጥ ፓርኪንሰን ሊመደብ ይችላል? በአገራችንስ በሽታው ምን ያህል ይታወቃል?
በቅርብ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ በፓርኪንሰን ላይ የጠተና ጥናት የለም፡፡ አንድ ጥናት ከ30 ዓመት በፊት በፕሮፌሰር ረዳ ተሰርቶ ነበር፡፡ ያኔ ጥናቱ ሲሰራ የኢትዮጵያ የእድሜ ጣሪያ 43 ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የኢትዮጵያዊያን የእድሜ ጣሪያ 65 ዓመት ደርሷል እየተባለ ነው፡፡ በመሆኑም የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ ነው የሚሄደው፡፡ ያደጉት አገራት በፓርኪንሰን የሚጠቁት የእድሜ ጣሪያቸው ትልቅ ስለሚሆን ነው፡፡ በአገራችን በሽታው እንደ በሽታ ትኩረት ማግኘት የጀመረው ከሶስት ዓመት ወዲህ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የፓርኪንሰን ተጠቂዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ይታወቃል? ከነርቭ ህመምስ በምን ይለያል?
ቀደም ሲል እንደነገርኩሽ በቅርብ የተጠና ጥናት ስለሌለ ቁጥራቸውን የሚያውቅ የለም። ታማሚዎቹም መራመድ፣ መናገር፣ መንቀሳቀስ ስለማይችሉ ወደ ህክምና አይመጡም፡፡ ስለዚህ ምን ያህል ናቸው የሚለው አይታወቅም፡፡ በእርግጥ አሁን አሁን የሰው ግንዛቤ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ሰዎች ምልክቱን ሲያዩ ወደ ህክምና እየመጡ ነው። ከነርቭ በሽታ በምን ያለያል ላልሽው ነርቭን የሚያጠቁ በርካታ በሽታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ስትሮክ የነርቭ በሽታ ነው፣ ኦሜንሺያ (የመርሳት ችግርም) እንዲሁ ነርቭን የሚያጠቃ በሽታ ነው፡፡
ስለዚህ አንድ ራሱን የቻለ የነርቭ በሽታ የለም፡፡ ፓርኪንሰንም ነርቭን ከሚያጠቁ በሽታዎች አንዱ ነው፡፡ በሽታው እንደነገርኩሽ የራሱ ምልክቶችና ባህሪዎች አሉት፡፡
በበሽታው ህክምና ላይ ስፔሻላይዝ አድርገው የሚሰሩ ባለሙያዎችና የጤና ተቋማት አሉ?
ባለሙያዎቹ የነርቭ ስፔሻሊስቶች ናቸው፤ ጤና ተቋማትም አሉ፡፡ ህክምናው በመንግስት ሆስፒታሎች የሚሰጥ ሲሆን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድና በዘውዲቱ ሆስፒታል ይሰጣል፡፡ ታማሚዎች በእነዚህ ተቋማት መታከም ይችላሉ፡፡
ፓርኪንሰን በህክምና ይድናል ወይስ አብሮ የሚኖር ነው?
በሽታውን የሚያጠፋ መድኃኒት የለም፤ የሚያስታግስ እንጂ፡፡ ለምሳሌ የስኳር ታማሚዎች ኢንሱሊን በተደጋጋሚ እንደሚሰጣቸው ሁሉ መድኃኒቱን እድሜ ልክ በቋሚነት በመውሰድ ረጅም ጊዜ ይኖራሉ፡፡ ፓርኪንሰን በራሱ ገዳይ አይደለም፡፡
ለሌሎች በሽታዎችስ ያጋልጣል?
አዎ ለሌሎች ጉዳቶች ያጋልጣል፡፡ ለምሳሌ ለመሰበር አደጋ ያጋልጣል፡፡ ሚዛን መጠበቅ ስለማይችሉ ይወድቃሉ፤ ያን ጊዜ ስብራት ይመጣል። በሌላ በኩል ለሳንባ ምች በተደጋጋሚ ያጋልጣል፡፡ የፓርኪንሰን ታማሚዎች በአብዛኛው ለሳንባ ምች ይጋለጣሉ፡፡
ህክምናው በምን መልኩ ነው የሚሰጠው? መድኃኒቱስ?
ዘርፈ ብዙ ህክምና ነው ያለው፡፡ የክኒን ህክምና አለ፣ የስራ ቴራፒ ይሰጣል፡፡ የንግግር ቴራፒና የቡድን ቴራፒ ይሰጣል፡፡ በሽታው ንግግር፣ መዋጥ ሁሉ ይከለክላል፡፡ የንግግር ቴራፒ፣ ምግብ የመዋጥ ቴራፒ ሁሉ ይሰጣል፡፡ አገራችን ውስጥ በዋናነት ያለው የፊዚዮ ቴራፒና የክኒን ህክምና ነው፡፡
በሽታው በጡረታ እድሜ ላይ ያሉትን ነው የሚያጠቃው፡፡ መድኃኒቶቹ የጡረተኞችን አቅም አይፈትኑም?
በአገራችን ሁለት አይነት ክኒኖች አሉ፡፡ 600 እና 700 ብር ናቸው፡፡ እንዳልሽው ለጡረተኛ ውድ ናቸው፡፡ ይከብዳቸዋል፡፡ ምንም የገቢ ምንጭ እንደሌላቸው ካስመሰከሩ በመንግስት ሆስፒታሎች በነፃ የሚታከሙበት እድል አለ፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ መድኃኒቱ ከአገር በሚጠፋበት ጊዜ የግድ ወደ ግል ፋርማሲዎች ሄደው ለመግዛት ይገደዳሉ፡፡
በሽታው የመጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ታማሚዎቹ ምን ይሆናሉ?
ይህ እንግዲህ ስቴጅ ፋይቭ (ደረጃ አምስት) ይባላል፡፡ ታማሚዎች እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ዊልቸር ላይ ይቀራሉ፣ ንግግር ያቅታቸዋል፣ ምግብ መዋጥ አይችሉም፤ የአልጋ ቁራኛ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
ታዲያ እዚህ ደረጃ ሲደርሱ በምን መልኩ ይረዳሉ?
የንግግር ቴራፒስቶች የንግግርና የአዋዋጥ ስልጠና ይሰጧቸዋል፣ ይህን ሲያደርጉ ብዙ ትንታና ሳል የሚይዛቸው ከሆነ በቀዶ ህክምና ሆዳቸው ላይ ቲዩብ ገብቶላቸው፣ ምግብ በዚያ በኩል እንዲያገኙ ይደረጋሉ፡፡ ይህ እንዲህ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው፡፡
የዚህ በሽታ ተጠቂዎች በአማካኝ ምን ያህል እድሜ ይኖራሉ?
ከዋናው የእድሜ ጣሪያ ሁለት ወይም ሶስት አመት ቢቀንሱ እንጂ በደንብ ይኖራሉ፡፡ እንደነገርኩሽ ፓርኪንሰን በራሱ ገዳይ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የኖርማል ሰው የእድሜ ጣሪያ 65 ዓመት ከሆነ እነሱ 62 ወይም 63 ዓመት መኖር ይችላሉ፡፡ ዋናው ችግር ግን ተጠቂዎቹ እድሜያቸውን ሙሉ መሥራትና ምርታማ አለመሆናቸው ነው፡፡
ዋናው የበሽታው መንስኤ እድሜ ነው ተብሏል አንዳንዴ በ30ዎቹ ውስጥም ያሉት ይጠቃሉ፡፡ ለምሳሌ የፓርኪንሰን ታማሚዎች ማህበር መስራች የሆነችው ወ/ሮ ክብራን በ32 ዓመቷ በበሽታው መጠቃቷ ከአኗኗር ዘይቤ ጋር ይገናኝ ይሆን?
በሽታው ለምን እንደሚከሰት አይታወቅም፡፡ ዋናው የዱፓሚን እጥረት ነው እጥረቱ የሚከሰተው አምራች ሴሎች ሲሞቱ ነው፡፡ ሴሎቹ ለምን እንደሚሞቱ አይታወቅም፡፡ ሴሎቹ የሰውየው እድሜ ሲጨምር ይሞታሉ ቢባል እንኳን በ30ዎቹ እድሜ ያሉትን ለምን እንደሚያጠቃ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡
እዚህ አገር ለፓርኪንሰን በሽታ ህክምና የሚሰጥ ራሱን የቻለ ስልጠና አለ?
የፓርኪንሰን ስፔሻሊስት ለመሆን የሚሰጥ ስልጠናና ትምህርት እዚህ አገር የለም፤ ነገር ግን አንድ ባለሙያ በነርቭ ህክምና ላይ ስፔሻላይዝ ካደረገ በኋላ “Movement disorder” ወይም የእንቅስቃሴ መታወክ ሰብስፔሻሊቲ ስልጠና አለ፡፡ እሱን ወስደን ነው የምንሰራው፡፡

Read 8837 times