Tuesday, 08 July 2014 08:30

“የፀለይነው ተአምር እንዲሰራልን ነበር፤ ለዚህ ስላልታደልን ግን መከራ ወደቀብን”

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(2 votes)

         የገቡበት ሳይታወቅ የጠፉ ሶስት ወጣት ልጆቿን ፍለጋ ከሀሙስ ሰኔ 16 ቀን ጀምሮ ስትንጓለል የከረመችው የእስራኤሏ ሞዲን ከተማ ባለፈው ሰኞ ረፋዱ ላይ እጅግ አስደንጋጩን መርዶ ሰምታ እርሟን አወጣችና በሀዘን ተቆራምዳ ቁጭ አለች፡፡
በህይወት ይገኛሉ ተብሎ እንዲያ በእግር በፈረስ ሲታሰሱ የነበሩት ሶስት ወጣቶች ኢያል ይፍራህ፣ ጊላድ ሻርና ንፍታሊ ፍራንስል፤ እንደታሰበው በህይወት ሳይሆን ተገድለው አስከሬናቸው በእየሩሳሌም ከተማ አንድ ስርቻ ስር ተጥሎ ተገኘ፡፡
የወጣቶቹ አስከሬን እንደተገኘ በደቂቃዎች ልዩነት ሪፖርቱ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁም፤ “ለዚህ ስራው ሀማስ የእጁን ያገኛታል!” በማለት በከፍተኛ ንዴት በሀማስ ላይ ዛቻቸውን ሰነዘሩ፡፡
ይህ በሆነ በአንድ ሰአት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የእስራኤል አየር ኃይል ጋዛ ውስጥ የሚገኙና የሀማስ ይዞታዎች ናቸው በተባሉ ከደርዘን በላይ ቦታዎች ላይ ድብደባ ፈፀሙ፡፡
ሳሙ አቡዙህሪ የተባሉ የሀማስ ቃል አቀባይ በሰጡት ምላሽም፤     “ሀማስም ሆነ ማናቸውም የፍልስጤም ቡድን በልጆቹ ግድያ ላይ እጃቸው የለበትም፡፡ የእስራኤል ክስ ፈጽሞ የሚታመን አይደለም፡፡ እኛ ከደሙ ነፃ ነን፤ በሮመዳን ምድር ክፉ አታናግሩን!” በማለት ማስተባበያ ቢያቀርቡም ሰሚ ጆሮ አላገኙም፡፡
የሶስቱ ወጣቶች ቀብር በተፈፀመበት ባለፈው ማክሰኞ ንግግር ያደረጉት የእስራኤል ፕሬዚዳንት ሺሞን ፔሬዝ፤ “የፀለይነው ተአምር እንዲሰራልን ነበር፤ ለዚህ ስላልታደልን ግን መከራ ወደቀብን፡፡ ሽብር ከስር መሰረቱ ተነቅሎ እስኪጠፋ ድረስ ግን በሀይለኛው ክንዳችን ጠላቶቻችንን መደቆስ እንቀጥላለን፡፡” ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሺሞን ፔሬዝ ከቀብሩ በኋላ ለቀስተኛውን እያጽናኑ በነበረበት ሰዓትም የእስራኤል ወታደሮች ዌስት ባንክ ውስጥ ቦንብ ሊወረውርብን ሞክሯል ያሉትን አንድ ፍልስጤማዊ ሲገድሉ፣ ሄብሮን ውስጥ ደግሞ የገዳዮቹ ነው ብለው የጠረጠሩትን የአንድ ፍልስጤማዊ ቤተሰብ መኖሪያ ቤትን በፈንጂ አፈራርሰዋል፡፡
በአጠቃላይ ሶስቱ ወጣቶች ጠፉ ከተባለበት ሰኔ 16 ቀን ጀምሮ የእስራኤል ጦር ኃይል በአውሮፕላን ደብድባ ካወደማቸው የሀማስ ተቋማት በተጨማሪ አንድ ለጋ ወጣትን ጨምሮ አምስት ፍልስጤማውያንን ሲገድሉ፣ አብዛኞቹ የሀማስ አባላት የሆኑ አራት መቶ አስራ ዘጠኝ ፍልስጤማውያንን ደግሞ አስረዋል፡፡
የእስራኤልና የአሜሪካ ጥምር ዜግነት ያላቸው ሶስቱ ወጣቶች ኢያል ይፍራህ፣ ጊላድ ሻርና ንፍታሊ ፍራንከል በገዳዮቻቸው እጅ ውስጥ የወደቁት ሰኔ 16 ቀን ዌስት ባንክ በምትገኘው የፍልስጤማውያን ከተማ ሄብሮን ውስጥ የእግር ጉዞ በማድረግ ላይ ሳሉ ነበር፡፡ ጊላድ ሻርና ንፍታሊ ፍራንከል የአስራ ስድስት አመት፣ አያል ይፍራህ ደግሞ የአስራ ዘጠኝ ዓመት ወጣቶች ነበሩ፡፡

Read 3875 times