Saturday, 12 July 2014 12:00

የህትመት ዋጋ ጭማሪው ጋዜጦችን ስጋት ላይ ጥሏል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(7 votes)

ብርሃንና ሰላም ከ25-30 በመቶ ጭማሪ አድርጓል
“ጭማሪው የተደረገው የወረቀት ዋጋ በመናሩ ነው”
አሳታሚዎች የወረቀት ዋጋ ጨመረ መባሉን አልተቀበሉትም

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፤ ከሐምሌ ወር ጀምሮ በህትመት ዋጋ ላይ ያደረገው ጭማሪ የግል ፕሬሱን ከገበያ ሊያስወጣው እንደሚችል አሳታሚዎች ስጋታቸውን ገለፁ፡፡
በህትመት ዋጋ ላይ ከ25-30 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ ማድረጉን የገለፀው ማተሚያ ቤቱ፤ ጭማሪውን ያደረግሁት ከውጭ የሚመጣው ወረቀት ዋጋ በመናሩ ነው ብሏል፡፡
የ“ሰንደቅ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ፍሬው አበበ የህትመት ዋጋ ጭማሪውን አስመልክቶ ለአዲስ አድማስ በሰጠው አስተያየት፤ በአሁኑ ሰዓት በጋዜጦች ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ ያለው በጊዜ አለመውጣትና የህትመት ጥራት ችግር መሆኑን ገልፆ፤ ድርጅቱ እነዚህን መሰረታዊ ችግሮች ሳይቀርፍ ዋጋ መጨመሩ የኪሳራ ኪሳራ ነው ብሏል፡፡ የጋዜጣ በሰዓቱ አለመውጣት ችግር በገንዘብ የማይታመን መሆኑን የጠቆመው ዋና አዘጋጁ፤  በዚህ ላይ የህትመት ዋጋ ጭማሪ ማድረግ ጋዜጦችን ከገበያ ውጭ ያደርጋል ሲል ስጋቱን ገልጿል፡፡
ብርሃንና ሰላም፤ መሰረታዊ አገልግሎቱን ሳያሻሽል እንደውም እያሽቆለቆለ ባለበት ወቅት ዋጋ መጨመሩ በምንም መልኩ ፍትሃዊ አይደለም” ያለው ጋዜጠኛ ፍሬው፤ ድርጅቱ ዋጋ ለመጨመር ከመጣደፍ ይልቅ ለአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ በአፅንኦት ተናግሯል፡፡ ከአምስትና ከስድስት ወራት በፊት በሰዓታቸው ለአንባቢያን ይደርሱ የነበሩ ጋዜጦች፤ በአሁኑ ሰዓት በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት መልካም ፈቃድ ያለቀናቸው እየወጡ እንደሆኑ ጠቁሞ፤ አሳታሚዎች ለኪሳራ እየተዳረጉ ለህዝቡ መረጃ ለማቀበል ቢተጉም ማተሚያ ቤቱ ተደራራቢ ጫና እየፈጠረ በመሆኑ፤ የጋዜጦች ህልውና አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል ብሏል፡፡
ማተሚያ ቤቱ የጋዜጦቹ ኪሳራና ጉዳት ሳያስጨንቀው በዚህ ችግር ላይ ዋጋ መጨመሩ አፍ አውጥቶ “ማሳተማችሁን አቁሙ” ከማለት ተለይቶ የሚታይ እንዳልሆነም ጋዜጠኛ ፍሬው ተናግሯል፡፡ የህትመት ዋጋ ጭማሪው ጋዜጣቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉን የገለፀው ዋና አዘጋጁ፤ ጭማሪውን ለብቻቸው ለመሸከም ጫንቃቸው ስለማይችል አንባቢው ላይ ዋጋ ለመጨመር እንደሚገደዱ ተናግሯል፡፡ “አሁን ካለው የህዝቡ ተጨባጭ የኑሮ  ሁኔታ አንፃር አንባቢ ላይ ዋጋ መጨመር ጉዳቱ ከፍተኛ ስለሚሆን ለጊዜው ጭማሪውን አላደረግንም” ያለው ዋና አዘጋጁ፤ ጫናውን ሙሉ ለሙሉ ጋዜጣው መሸከሙን ጠቁሟል፡፡
በሳምንት ሶስት ቀን የሚታተመው የሪፖርተር ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ መላኩ ደምሴ በበኩሉ፤ የአለም የወረቀት ዋጋ ጨምሯል መባሉን አምኖ ለመቀበል እንደሚቸግረው ይናገራል፡፡ ብርሃንና ሰላም ወረቀት ከውጭ ማስገባቱ ላይ ጥርጣሬ አለኝ ያለው ማኔጂንግ ኤዲተሩ፤ “ድርጅቱ የውጭ ግዢ በወቅቱ ሳይፈፅም ቀርቶ ከአገር ውስጥ ገዝቶ ይሆናል እንጂ የውጭ ወረቀት ዋጋ ከ20 በመቶ በላይ ሊጨምር አይችልም” ብሏል፡፡
የዋጋ ጭማሪው በእኛ ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድርብናል ያለው መላኩ፤ “ሪፖርተር” በሳምንት ሶስት ጊዜ እየታተመ እንደሚወጣ አስታውሶ፤ የእሁዱ አማርኛ ሪፖርተር ከ148-160 ገፅ፣ የቅዳሜው እንግሊዝኛ “The Reporter” እስከ 40 ገፅ እንዲሁም የረቡዕ እትም ከ23-40 ገፅ እንደሚታተሙና እነዚህ ተደምረው 25 ወይም 30 በመቶ ጭማሪ ሲደረግ ጫናው ከፍተኛ እንደሚሆን ተናግሯል፡፡ “ይሄ ከፍተኛ ጫና እላያችን ላይ ሲወድቅ፣ እኛ ደግሞ ወደ አንባቢውና ወደ ማስታወቂያ ደንበኞቻችን እንሄዳለን” ያለው ማኔጂንግ ኤዲተሩ፤ የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ይጨመራል ከተባለ በኋላ በተለያዩ ቁሳቁሶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እየታየ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ “መንግስት በአንድ በኩል በደሞዝ ጭማሪ ሰበብ የሸቀጣሸቀጥ ጭማሪ የሚያደርጉ ህገ-ወጦችን ጠቁሙ እያለ፣ በሌላ በኩል እነ ብርሃንና ሰላም ጭማሪ ያደርጋሉ” ያለው ማኔጂንግ ኤዲተሩ፤ የእነብርሃንና ሰላምን የዋጋ ጭማሪ ለማን እንጠቁም? ሲል ይጠይቃል፡፡
“በአጠቃላይ ጭማሪው የግል ጋዜጦችን የሚጎዳ ነው፤ በመሆኑም ጋዜጦቹ አንባቢው ላይ ጭማሪ ያደርጋሉ፤ በአንባቢው በኩል ይህን የሚሸከም ትከሻ አለ ወይ? የሚለው ሌላ ጭንቀት ይፈጥራል” የሚለው መላኩ፤ “የዋጋ ጭማሪው ለግል ሚዲያው ትልቅ ሸክምና የህልውና ጉዳይንም የሚፈታተን ነው፤ በዚህም እጅግ እጅግ ተከፍተናል” በማለት አስተያየቱን ቋጭቷል፡፡
የካፒታል ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ግሩም አባተ በጉዳዩ ላይ በሰጠው አስተያየት፤ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የህትመት ዋጋ ጭማሪ ከሀምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚደረግ በደብዳቤ ከማሳወቁ ውጭ የጭማሪውን መጠን አለመግለፁን ጠቁሞ፤ ጭማሪው ከሁለት እስከ ስምንት በመቶ እንደሚሆን ጠብቀን ነበር ብሏል፡፡ “እንደተባለው 25 እና 30 በመቶ ጭማሪ ከተደረገ ግን የህትመት ሚዲያው ጫና ላይ ይወድቃል” ሲል ስጋቱን ገልጿል፡፡
የወረቀት ዋጋ በመናሩ ነው ጭማሪውን ያደረግነው የሚለው የማተሚያ ቤቱ ምክንያት ለጋዜጠኛ ግሩምም አሳማኝ አልሆነለትም፡፡ “በዓለም ላይ ቀርቶ ጎረቤቶቻችን ኬኒያና ታንዛኒያ ውስጥ የኢንተርኔት ተጠቃሚው በመብዛቱ የህትመት ወረቀት ዋጋ እየቀነሰ ነው” የሚለው ዋና አዘጋጁ፤ አሁን በየትኛውም ቦታ የኢንተርኔት ተጠቃሚው እየበዛ በመሆኑ ውጭ ያሉ የጋዜጣ ወረቀት አምራቾች በሚባለው መጠን ዋጋ ይጨምራሉ ብዬ አላምንም ብሏል፡፡
የብርሃንና ሰላም በየጊዜው ዋጋ መጨመር ግራ የሚያጋባና የሚያደናግር ነው የሚለው ጋዜጠኛ ግሩም፤ የህትመት ጥራት ቢጨምር፣ ጋዜጦች በሰዓታቸው ወጥተው ለአንባቢ ቢደርሱና ሌሎች እሴቶችን ጨምሮ ቢሆን ኖሮ በጸጋ በተቀበልነው ነበር ብሏል፡፡
“ብዙ ጊዜ ዋጋ ሲጨመር ዝም እያልን ነው ይሄ ሁሉ ነገር የመጣው” ያለው ግሩም፤ አሁንም አማራጭ ስለሌለን ለጊዜው ባንወስንም በማስታወቂያም ሆነ በጋዜጣ መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጋችን አይቀርም ብሏል፡፡ ከ25 እስከ 30 በመቶ የተባለው ጭማሪ እውነት ከሆነ ለግል ህትመት ሚዲያዎች ሁኔታው አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው በመግለፅም ችግሩ እስኪስተካከል ድረስ በተቋቋመው የአሳታሚዎች ማህበር በኩል ውይይት ተደርጎ አንድ ነገር ላይ መድረስ አስፈላጊ ነው፤ ያለበለዚያ የህትመት ሚዲያው ህልውና ያሰጋል ብሏል፡፡
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተካ አስፋው በበኩላቸው፤ የህትመት ዋጋ ጭማሪ የተደረገው ከውጭ የሚመጣው ወረቀት ዋጋ በመጨመሩ ነው ይላሉ፡፡ “ከአንድ ወር በፊት ያመጣነውና አሁን ያመጣነው ዋጋ ሲታይ ጭማሪው እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው” ያሉት አቶ ተካ፤ ከዚያ አንፃር ድርጅቱ የጨመረው የህትመት ዋጋ በጣም አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡ ጋዜጦች ያለቀናቸው እንዲሁም አርፍደው እየወጡና እንዲሁም የህትመት ጥራቱ እያሽቆለቆለ ባለበት ሰዓት ዋጋ መጨመሩ አግባብ ነው ወይ ተብለው የተጠየቁት ስራ አስፈፃሚው፤ የጋዜጦች በወቅቱ አለመድረስና የህትመት ጥራት ችግር መኖሩ የሚካድ አይደለም ብለዋል፡፡ የማተሚያ ማሽኖቹ ከ15 ዓመት በላይ ያገለገሉ መሆናቸውና የመለዋወጫ አለመኖር ለጥራት ችግሩ መንስኤ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቅርቡ ችግሮቹ ይቀረፋሉ የሚል እምነት እንዳለቸው ገልጸዋል፡፡
ዋጋቸው ቀለል የሚል የውጭ ወረቀት አምራች ድርጅቶችን በማፈላለግ በተመጣጣኝ ዋጋ ወረቀት አስገብቶ አሳታሚዎችን ለማገዝ ሙከራ እያደረጉ እንደሆነ የጠቆሙት ሥራ አስፈፃሚው፤ “በቅርቡ አንሞል” ከተባለ የህንድ ወረቀት ኩባንያ ጋር ተነጋግረን የጋዜጣ ወረቀት ናሙና  ልኮልናል፤ ለሙከራ የሚሆን ሀምሳ ቶን አዝዘናል፤ ወረቀቱ ጥሩ ከሆነና ጥራቱ አስተማማኝ ከሆነ የውጭ ምንዛሪን ከማዳኑም በላይ የህትመት ዋጋን ተመጣጣኝ ያደርገዋል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ሁለትና ሶስት ጊዜ ድርጅቱ የላከው ናሙና ጥሩ በመሆኑ ሙከራቸው ስኬታማ ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
የህትመት ዋጋን ለመደጎም መንግስት የራሱን ሚና ቢጫወት መልካም ነው ያሉት ኃላፊው፤ ወረቀቱ ሲገባ የሚከፈለው ቀረጥ እንዲቀንስ ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ጋዜጣ ሸቀጣ ሸቀጥ ሳይሆን የአዕምሮ ምግብ መሆኑን በመጠቆምም በቀረጡ ዙሪያ ከኢትዮጵያ አታሚዎች ማህበር ጋር  እንደሚወያዩ ገልፀዋል፡፡
“አንዳንድ አሳታሚዎች ገፅ መጨመር እየፈለጉ በዋጋ ምክንያት ይቀንሳሉ” ያሉት አቶ ተካ፤ ይሄ አሳታሚውን ብቻ ሳይሆን ብርሀንና ሰላምንም ይጎዳል፤ ምክንያቱም ኮፒ በጨመረ ቁጥር ድርጅቱም ይጠቀማል፤ ይህን ለማስተካከልና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማምጣት ጥረታችንን እንቀጥላለን፤ የዋጋ ጭማሪው ምክንያት ግን ከውጭ የሚመጣው ወረቀት ዋጋ በመናሩ ነው” በማለት የጋዜጣ አሳታሚዎች ይህን ግምት ውስጥ እንዲከተላቸው ጠይቀዋል፡፡  

Read 4683 times