Saturday, 12 July 2014 12:09

“የአገሬ ልጅ ሆዴ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ቅዝቃዜው እንዴት እያደረጋችሁ ነው!
እኔ የምለው…የዘንድሮ ‘መመዘኛዎችን’ ነገሬ ብላችሁ ታውቃላችሁ! አለ አይደል… ለሆነ ነገር የምትመረጡበት ወይም ‘ዓይን ውስጥ የማትገቡበት’ መመዘኛ እየበዛ ነው፡፡
እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ስሙኝማ…ዕድሜ መገመቻ ብዙ መንገዶች አሉ፡፡ በተለይም የትውልድ ዘመንም ከሆነ ክስተት ጋር ማገናኘት እኛ አገር የተለመደ ነው፡፡ ለእሱ መሰለኝ ደህና አድርገን ‘ሁለት ዲጂቷን’ ምናምን ለመገንደስ የሚያመቸን! (‘ሁለት ዲጂት’ ሌላ አገልግሎት እንዳላት ይታወቅልንማ!)
እናላችሁ… “የትሣስ ግርግር ጊዜ አንደኛ ክፍል ላስመዘገብው እየሄድን፣ ምን አለፋህ ጦር ሠራዊት መጣና ሜዳው ላይ ፈሰሰበት፣” ሲባልለት የነበረው ሰው ዘንድሮ ምን ይል መሰላችሁ… “አርባ ሲሞላኝ ጂ ፕላስ ዋን ካልሠራሁ ሞቻታለሁ!” ይላል፡፡
እናማ…ሰውየው ዕድሜውን ሲጠየቅ “ወደ ሠላሳ ሁለት ግድም ቢሆነኝ ነው…” ምናምን ሊል ይችላል። ሽማግሌ አባቱ ደግሞ እሱ በሌለበት ሲጠየቁ ምን ሊሉ ይችላሉ መሰላችሁ…“በሬዬ ጠቋር የሞተ ጊዜ ልጄ አሥራ ሰባት ዓመቱን ከደፈነ ሦስት ወር ከመንፈቅ ሆኖት ነበር፡፡” በሬው ጠቋር ከሞተ እኮ ሠላሳ አምስተኛ ዓመቱ’ ከናይጄሪያ ጋር ኳስ የተጠጫወትን ጊዜ አለፈ!
ልጄ…ዘንድሮ ምን ችግር አለው፣ ‘ለገበያ እስካመቸ’ ድረስ መገንደስ ነው፡፡
እኔ የምለው፣ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንድ ወዳጄን ጓደኛው ምን ይለዋል “የአንተን ዕድሜ ለመገመት’ኮ ችግር የለውም፡፡ ስንት አሮጌ ደበሎ እንዳለህ መቁጠር ነው፡፡”  ስሌቷ ስንት ለስንት መሰለቻችሁ…አንድ ደበሎ ለአሥር ዓመት! እንትና በቀደም ዕቃ ቤታችሁ እነኛ ጨርቃ ጨርቆች ተከምረው አይቼ “አንተ ብርድ ልብስ አከፋፋይ ሆንክ እንዴ!” ያልኩህ… ነገርዬዎቹ ደበሎዎች ናቸው እንዴ!  ካሽ ሬጂስተር ኤጅም ያሰላል!”ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ… አንዳንዱ እኮ ሲገነድስ ለነገ ብሎ ነገር የለውም፡፡ እናላችሁ…የሆኑ እሷና እሱ እንደ ቁጥር ችሎታቸው ከዋናው ላይ ይገነድሱታል፡፡ (አሥራ ስድስት አይበዛም! አራት የአሜሪካ ምርጫ ማለት እኮ ነው!) እናላችሁ…አንድ ላይ የሚገነድሱት እኮ ተደምሮ “አሁንማ አረጀህ!” ለሚባል ሰው ይሆናል፡፡
እኔ የምለው…የመመዘኛ ነገር ካነሳን አይቀር…ንግግር አዋቂነት መመዘኛ ሲሆን ታያላችሁ፡፡  ጨዋታው ዋናው ጉዳይ የማወቅ ያለማወቅ ሳይሆን ነገሩ ‘ማነው ምላሱ ጤፍ የሚቆላ!’ እየሆነላችሁ ነው፡፡
የምር ጨዋታም አይደል…ዘንድሮ ‘ጤፍ በሚቆላ’ ምላስ ምክንያት ለራሳችን ‘ያለፈልን’፣ ሌላው እንዳያልፍለት መንገድ የዘጋን መአት ነን፡፡
የበቀደሙ ሰውዬ በየመድረኩ ቲራቲር ሲሠራ የከረመው አንድም ንግግር በማወቁ አይደል! የምር ግን…እዚህ ደረጃ ድፍን አገርን ጦጣ ማድረግ የሚቻልባቸው ስፍራዎች ይጠኑልን፡፡ ቢያንስ ከታቸ በኩል አንሁለተኛ ምናመን መሆናችን ቀርቶ ለአንድ ጊዜ እንኳን ከላይ በኩል ተወዳዳሪ የሌላቸው እንባል እንጂ፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት መሀል ከተማ አካባቢ አንድ የምናወቀው ሰው ነበር፡፡ እናላችሁ… መቼም ‘ቂቅ ማለት’ ማንም ጋር የለችም! እናማ…በአካባቢው ባሉ መዝናኛዎች ያሉ እንትናዬዎች አስተናጋጆችና የቤቶቹ ደንበኞች  የሚያውቁት በፓይለትነቱ ነው። በመጣ ቁጥር እንደተከበበ ነው፡፡ ‘ምላሱ’… አለ አይደል…ወንድምና እህት ማጋባት ይችላል የሚሉት አይነት ነው። ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ.. ሰውየው ዳውንታውን ያለ አንድ ሆቴል አሰላፊ ነበር! ሆኖም በምላሱና ቂቅ በማለቱ በአስተናጋጅነት ሲታዘዝ ውሎ በፓይለትነት ሲያዝ ያመሻል፡፡ በመጨረሻ የሆነ ‘ምቀኛ ጓደኛ’ በቀልድ አስመስሎ ምስጢሩን አፈረጠውና አረፈው። ሰውዬውም በዛው ጠፋ፡፡ እንደ ዘንድሮ ቢሆን ኖሮ ቢያንስ፣ ቢያንስ  የውድድር ዳኛ ይሆን ነበር! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ… አንደበተ ርቱዕነት ዋና መመዘኛ እየሆነ ‘ብልጥ፣ ብልጡ’ ኮሮላ ኤክሲዩቲቭ ይዞ ‘ሲያሽከረክር’… አለ አይደል… ‘ሞኝ፣ ሞኙ’ በፈራረሰ መንገድ ላይ በተወደደ ጫማ ሶሉን ሲጨርስ ይውላል፡፡
ደግሞላችሁ…ዘር የነገሮች መለኪያ መሆኑ እየባሰበት ነው፡፡ ኮሚክ እኮ ነው…ሁላችንም ‘የወንዛችንን ልጆች ፍለጋ ላይ ያለን ይመስላል፡፡ አንዱ እግረ መንገዱንም ሆነ… “የተወለድኩ እንትን የሚባል የገጠር ከተማ ነው” ሲል…ከአድማጮቹ አንድ ወይም ሁለታችን “አንተማ የአገራችን ልጅ ነህ…” ማለት እየለመደብን ነው፡፡ እናላችሁ…“የአገራችን ልጅ ነህ…” ማለት  ‘ከትልቁ ስዕል ወደ ሚጢጢው’ እያወረደን ነው፡፡
የምር እኮ የሚገርም ነው… አሁን፣ አሁንማ ከክልል ወደ አውራጃ፣ ብሎም ወደ ወረዳ፣ ብሎም ወደ መንደር፣ ብሎም ወደ ጎረቤት እያለ በየቤተሰቡ መሀል ደግሞ ራሳቸውን የቻሉ ‘ራሰ ገዞች’ እየተቋቋሙ ነው፡፡
እናላችሁ…በዚሀ በሰለጠነ ዘመን (“በቀላል ባቡር ዘመን…” ማለትም ይቻላል!) ዘርና የአገር ልጅነት ለብዙ ነገሮች መለኪያ ሲሆኑ ስታዩ ያሳዝናል፡፡ በብዙ መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች የሥራ ክፍፍል የሚመደበው፣ ‘መውጣትና መውረድ’ የሚወሰነው…  “ማነው ለዚህ ቦታ ብቁ፣ ጎበዝ ሠራተኛ?” በሚል መመዘኛ ሳይሆን “ማነው የአገራችን ልጅ?” በሚል ሆኗል እየተባለ ነው። አሁን አሁንማ “እንትን መሥሪያ ቤት በእንትን አገር ልጆች የተሞላ ነው…” ሲባል መስማት እየለመደብን ነው፡፡ (እዛች የፈረደባት አማሪካን ቤተክርስትያኖች ሳይቀር “የእንትን አገር ልጆች የሚሰበሰቡበት ነው…” በሚል ይከፋፈላሉ ሲባል እንደምንሰማው ማለት ነው።)
ስሙኝማ… አንዳንድ ጊዜ በኪነ ጥበብ ውስጥም… አለ አይደል… የሚሰጡ ሙገሳዎች “የአገራችን ልጅ…” የሚል መንፈስ አላቸው ይባላል፡፡ የምር ያሳዝናል!
ታዲያላችሁ…የሆነ ቦታ ላይ ‘የአገር ልጅ’ የሚለው ውስጥ የማትካተቱ ‘የሌላ አገር ሰው’ ከሆናችሁ…የሚገባችሁን እንዳታገኙ ችላ መባል ብቻ ሳይሆን በሆነ ባልሆነው መከራችሁን የምትበሉት እናንተ ናችሁ። እናላችሁ…ቢሮ በር ተዘግቶ የምትብጠለጠሉት እናንተ ናችሁ፡፡ “ሊሰልል የተላከብን ይሆናል…” የምትባሉት እናንተ ናችሁ፡፡ የእድገት መብታችሁ ተነፍጓችሁ፣ ልትደርሱ የሚገባችሁ ቦታ አይደለም መድረስ እንዳትጠጉ ሆናችሁም…አለ አይደል…በልባችሁ “እሱ እንዳመጣው እሱ ይመልሰው…” ብላችሁ ‘ድምጻችሁን አጥፍታችሁ’ እንዳትቀመጡ የሚተዋችሁ የለም፡፡ ይህን ያህል ነገሮች እየተበላሹ ነው፡፡
ይቺን ስሙኝማ…ሰውዬው ንብረቱን ተሸክሞ ከአንዱ መንደር ወደ ሌላ ሲጓዝ ወንበዴዎች ይገጥሙታል፡፡ እናላችሁ…እስከ ለበሳት ድረስ ሁሉንም ነገር ወስደው መለ መላውን ያስቀሩታል። ከዛላችሁ…ትተውኝ ሄዱ ሲል ጭራሽ በዱላ ያራውጡት ገቡ። ቢቸግረው ምን አለ መሰላችሁ…“ምን አደረግኋችሁ! ንብረቴን ሁሉ ወሰዳችሁ፣ አሁን የምትደበድቡኝ አርፍዶ መጣ ብላችሁ ነው!”
ምን ያድርግ ያለውን ሁሉ ወስደው ምን አድርግ ነው የሚሉት!
ዘንድሮ ‘የአገር ልጅ’ ባለመሆናችሁ ብቻ “ምን አደረግኋችሁ!” የሚያሰኙ ነገሮች መአት አሉ፡፡ ‘የአገር ልጅነት’ ለመታየትና ለመመረጥ ዋና መመዘኛ እየሆነ ነዋ!
“ከማን ጋር ይውላል፣ ያመሻል?” መመዘኛ ሆኗል፡፡
“‘ፈራንካ’ አለው የለውም?” ዋና መመዘኛ ሆኗል።
“ለሰዎቹ ቅርብ ነው…የማይገባበት ቢሮ የለም…” ማለትም መመዘኛ ሆኗል፡፡
የሀብታሞች ስም እየተጠቀሰ “ከእነእንትና ጋር ነው የሚያመሸው…” ማለትም መመዘኛ ሆኗል፡፡ ኑሮን ወደ ኋላ መለስ ብሎ ላየው አለ ብዙ ነገር
ካሁን የሚለየው፣ ድሮማ ቢመለስ: እየገሰገሰ ትዝታው ተሽሮ ፍቅሩ በነገሰ፡፡
ተብሎ ተዘፍኖ ነበር፡፡ እናላችሁ…ሰዎች “ኑሮን ወደ ኋላ መለስ ብሎ ላየው…” እያሉ ቢቆዝሙ የማያስወቅስ ደረጃ እየደረስን ነው፡፡ ነገሮች እየተበላሹ ነዋ! ያለነው እትብታችን በተቀበረበት ‘አፈራችን’ ላይ ሳይሆን በመርከብ የመን ድንበር የተራገፍን እያስመሰሉን ነዋ! የሆነ ቦታ አገልግሎት ለማግኘት ከመሄዳችን በፊት “ሀላፊው የምን አገር ሰው ነው?” ብለን እንድንጠይቅ እየተገደድን ነዋ!
“የአገሬ ልጅ ሆዴ…” አይነት ወሬ የሚነሳው በቤተሰብ ጉባኤ አካባቢ ብቻ የሚሆንበትን ዘመን ያምጣልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4879 times