Saturday, 12 July 2014 12:42

የማሌዢያው አውሮፕላን ፍለጋ አስርት አመታትን ሊፈጅ ይችላል ተባለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ 239 ሰዎችን አሳፍሮ ከኳላላምፑር በመነሳት ወደ ቤጂንግ በመብረር ላይ እያለ ድንገት የገባበት የጠፋውን የማሌዢያ አየር መንገድ አውሮፕላን ለማግኘት የተጀመረውና ይህ ነው የሚባል የተጨበጠ ውጤት ያልተገኘበት ፍለጋ አስርት አመታትን ሊፈጅ እንደሚችል የኩባንያው አንድ የስራ ሃላፊ መናገራቸውን ዘ ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
የአየር መንገዱ የንግድ እንቅስቃሴ ዳይሬክተር ሃግ ዳንሌቪ ከሳምንታት በፊት ከኢቭኒንግ ስታንዳርድ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ድንገት በተሰወረው ኤም ኤች 370 ቦይንግ 777 አውሮፕላን ላይ፣ የሆነ የማይገባ ድርጊት ተፈጽሞበታል ብለው እንደሚያስቡና ወደመነሻው ለመመለስ በሚሞክርበት ጊዜም ፈታኝ የሆኑ ነገሮች ተጋርጠውበት ሳይሳካለት እንደቀረ መናገራቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡
አውሮፕላኑ በደቡባዊ የህንድ ውቅያኖስ አካባቢ ሳይወድቅ እንዳልቀረ የገለጹት ዳንሌቪ፣ አወዳደቁ የከፋ ሊሆን እንደሚችልና ውቅያኖሱ ውስጥ ከሚገኙ ተራሮች ጋር ከተጋጨም ስብርባሪው ርቆ ሊሄድና ሊበታተን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አንጻርም የአውሮፕላኑን ስብርባሪ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት እጅግ ፈታኝ ሆኖ ሊቀጥልና ምናልባትም አስርት አመታትን ሊፈጅ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
አውሮፕላኑ ከጠፋ ከቀናት በኋላ፣ ፍለጋውን በተመለከተ ከአንድ የአገሪቱ ከፍተኛ ሚንስትር ጋር ቃለ መጠይቅ እንዳደረገ ያስታወሰው ዘ ቴሌግራፍ፤ ሚንስትሩ በወቅቱ በሰጡት ምላሽ፤ ፍለጋው ሳምንታትን ግፋ ቢልም ወራትን ብቻ ሊፈጅ እንደሚችል ነግረውኝ ነበር ብሏል፡፡

Read 1952 times