Saturday, 12 July 2014 12:44

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅሌት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    መንግስታት ከምንጊዜውም በበለጠ ቅሌት ውስጥ የሚዘፈቁበት ጊዜ አለ ከተባለ በምርጫ ወቅት ነው። የየሀገሮቻቸው ብሄራዊ የምርጫ ጊዜ ሲቃረብ ጀምሮ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ መንግስታት የማይሰሩት ቅሌት የለም፡፡ አንዳንዱ መንግስት ያሰጉኛል የሚላቸውን ተፎካካሪዎቹን እዚህ ግባ የማይባል ሰበብ አስባብ በመፍጠር ከያሉበት ለቃቅሞ ወህኒ ያጉራል፡፡
አንዳንዱ መንግስት ደግሞ ተቃዋሚዎቹን ብቻ ሳይሆን ጋዜጠኞችንም ጨምሮ ያስራል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ግንባር ቀደም ተፎካካሪያቸውን ብቻ ለይተው ከጨዋታ ውጭ የሚያደርግ ኮሚክ የምርጫ ህግ ያወጣሉ፡፡ ለምሳሌ የምያንማር (በርማ) ወታደራዊ ደርግ በ2008 ዓ.ም ያወጣው የምርጫ ህግ፣ የውጪ ሀገር ዜጋ ባል ያላቸው በርማውያን ፖለቲከኞች ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መወዳደር እንደማይችሉ ይደነግጋል፡፡
ይህ አስቂኝ የምርጫ ህግ ለየትኛው ፖለቲከኛ ተብሎና የትኛውን ፖለቲከኛ ከምርጫ ጨዋታ ውጭ ለማድረግ ታስቦ እንደወጣ በጣም ግልጽ ነው። በሚቀጥለው አመት በምያንማር በሚደረገው ምርጫ ከፍተኛ የማሸነፍ እድል ያላቸው ዝነኛዋ የነፃነትና የመብት ታጋይ ኦንግ ሳን ሱኪ ብቻ ናቸው። እንግሊዛዊ ባል ያላቸው ፖለቲከኛም ከእሳቸው ውጭ ማንም አልነበረም፡፡ እናም የምርጫ ህጉ ታቅዶና በሚገባም ታስቦበት የወጣው፣ ምርጫውን በቀላሉ እንደሚያሸንፉ የታመነውን ኦንግ ሳን ሱኪን ከጨዋታ ውጪ ለማድረግ ነው፡፡
እንደ ፖላንድ አይነት መንግስቶች የሚሰሩት ቅሌት ደግሞ ትንሽ ረቀቅ ያለ ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ፤ በሚቀጥለው አመት በሚደረገው ጠቅላላ ምርጫ ፓርቲያቸው “ሲቪክ “ፕላትፎርም” ፓርቲ ማሸነፍ እንዲችል የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን ይጠሩና ከወዲሁ አንድ ነገር እንዲያደርጉ ያዟቸዋል፡፡
ምኒስትሩም በጉዳይ ላይ ካሰቡበት በኋላ አሁን ባለው የፖላንድ የኢኮኖሚ ሁኔታ በሀገሪቱ የወለድ መጠን ላይ መጠነኛ ቅናሽ ማድረግ ከተቻለ፣ ገዢው የሲቪክ ፕላትፎርም ፓርቲ በቀጣዩ ምርጫ የተሻለ ድጋፍ ማግኘት እንደሚችል ይገምታሉ፡፡   
ከዚያም ቀጥ ብለው ወደ ፖላንድ ማዕከላዊ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ያመራሉ፡፡ የባንኩ ገዢ ከሆኑት ከማሪክ ቤልካ ጋር እንደተገናኙም ቀጣዩ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት በወለድ መጠኑ ላይ መጠነኛ ቅናሽ በማድረግ ገዢው ፓርቲ በምርጫው እንዲያሸንፍ የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ ጥያቄአቸውን ያቀርቡላቸዋል፡፡
የባንኩ ገዢ ማሪክ ቤልካም በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ የገንዘብ ሚኒስትሩን ከስልጣናቸው ካባረሩላቸው የተጠየቁትን እንደሚፈጽሙ ለሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ አረጋገጡላቸው፡፡ የጉዳዩ ዝርዝር ሪፖርት የቀረበላቸው ጠቅላይ ምኒስትር ዶናልድ ተስክም ለአፍታም እንኳ ሳያመነቱ ኢኮኖሚውን በወጉ መምራት ተስኖታል የሚል መናኛ ሰበብ በመፍጠር የገንዘብ ሚኒስትሩን ከስልጣኑ አባረሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ሁሉ ነገር የሰሩት በከፍተኛ ጥንቃቄና ምስጢር ነበር፡፡ ሆኖም ግን ባለፈው ሳምንት አንድ ጉድ ወጣ። የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከማዕከላዊ ባንክ ገዢ ጋር ያደረጉት ንግግር በምስጢር ቴፕ ተቀርፆ ይፋ ወጣ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክም ስልጣን እንዲለቁ ተጠየቁ፡፡ እሳቸው ግን ስልጣን መልቀቁን በጄ አላሉም፡፡ ይልቁንም የሀገሪቱን ርዕሰ መንግስት ንግግር በድብቅ መቅዳት ከመፈንቅለ መንግስት የማይተናነስ ወንጀል መሆኑን በመግለፅ ክስ ለመመስረት እንደሚገደዱ አስጠነቀቁ፡፡ የሌባ ዓይነ ደረቅ…ይሏል ይሄ ነው!!

Read 2799 times