Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 December 2011 09:24

ባህላዊ እሴቶች ላይ ያተኮሩ ፊልሞች ከወዴት አሉ? ያልፈለግነው የሚያስፈልገንን ነው!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሠራዊት ፍቅሬ ያሰናዳውን “ሠካራሙ ፖስታ” የተሰኘውን ፊልም ካየሁ በኋላ ገና ከአዳራሽ ሳንወጣ አጠገቤ ለነበረው ጌጡ ተመስገን “በመዳብ የተለበጠ ወርቅ” አልኩት፤  ምክንያቱስ ብትል ሃሳቡ ትልቅ ነው ርዕሱ ግን ፍሬ ነገሩን የመሸከም ጉልበት የለውም፡፡ መዳብ በወርቅ ይለበጣል እንጂ ወርቅ በመዳብ አይለበጥም፤ የወርቅ ዋጋና ክብር ከመዳብ ዋጋና ክብር ይልቅ እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ ሁለገብ ተሰጥኦ ያለውን ስመ ጥሩውን፣ ልበ ብሩህ አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬን በጣም በትሁት ሆኖም ቆራጥ በሆነ አቀራረብ “አድዋ”ን ካልሠራህ በቀር ፊልም ሠራሁ እንዳትል ብዬዋለሁ፡፡

ይሁንና አድዋን ለመሥራት ብዙ ገንዘብ ብዙ እውቀት ብዙ ጉልበት ብዙ አርቲስት ብዙ ጊዜ ይጠይቅሃል፡፡ አድዋን  በምን ያህል ውበትና ይዘት እንደሠራው አላውቅም እንጂ በፊልም ጥበብ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር፤ ኃይሌ ገሪማ እንደሠራው አቃለሁ፡፡ አሸናፊ ከበደ በሙዚቃ ጥበብ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር፤ እስክንድር ቦጐስያን በስዕል ጥበብ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር፤ ፍቅሬ ቶሎሣ በሥነጽሑፍ ጥበብ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ PHD (ዶክተር) እንደሆነ ሁሉ ኃይሌ ገሪማ በፊልም ሙያ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር ነው፡፡ ዛሬ ፕሮፌሰር ኃይሌና ዶክተር ፍቅሬ በመሃከላችን አሉ፤ እስክንድርና አሸናፊ አሜሪካን አገር እቤታቸው ውስጥ ህይወታቸው አልፎ ነው የተገኙት፡፡በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በረጅም የጊዜ ልዩነት “አሥቴር”፣ “ጉማ”፣  “ሂሩት አባቷ ማነው?” የተሰኙት ሶስት ያህል ኢትዮጵያዊ ፊልሞች ከተሰሩ በኋላ፤ የኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ በዚህ በዛሬው ዘመን ነው ማበብ ማደግና መጐልበት የጀመረው፡፡ በኢትዮጵያ በያመቱ ከሃያ የሚልጡ (በ2003 ዓ.ም ገደማ) ኢትዮጵያዊ  ፊልሞች መሠራት ከጀመሩ ከአሥር ዓመታት በላይ ሆኖአል፡፡ ከንጉሱ ዘመን አንስቶ በመንግሥት መዋቅር ሥር ሲተዳደር የነበረውና በፊልም አምራች ኩባንያነት ብቻውን (እያዘገመም ቢሆን) ሲንቀሳቀስ የኖረው የኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽን፤ በዚህ በዛሬው  ዘመን ከአሥር ባላነሱ ትጉህ የግል የፊልም ጥበብ ተቋማት ተተክቷል፡፡ በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ፊልሞች ለፍሬ በቅተዋል፡፡ በቅርብ አሥርት ዓመታት የፊልም ጥበብ በኢትዮጵያችን እያበበ እያደገና እየጐለበተ ቢመጣም በጽሑፍ ጥበብ፣ ውበትና ይዞታ፤ በተውኔት አመራር Directing እና Acting ትወና፤ በአቀራረብና በአቀራረጽ ቴክኒክ የሚቀሩን ነገሮች አሉ፡፡ ሲኒማ ቤቶችን በማስፋፋት፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ሲኒማ የማየት ባህልን በማዳበርና በማበልፀግ ረገድ እንኳ ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡  ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል ያላትና ቅኝ ያልተገዛች ጥንታዊ ሥልጣኔ የፈነጠቀባት አገር ነች፤ ከሃምሣ ዓመታት በፊት ከቅኝ አገዛዝ ነፃ በወጣችውና የራሷ ፊደል በሌላት ናይጄሪያ በየዓመቱ ከስምንት መቶ በላይ ፊልሞች ይሠራሉ፡፡  በዛሬው ዘመን ጥቁር አፍሪቃዊቷ ናይጄሪያ በፊልም አምራችነት ከታወቁት አራት የዓለማችን አገሮች አንዷ ነች፡፡ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት በ1905 ዓ.ም በኤዢያዊቷ ህንድ የፊልም ጥበብ ሲጀመር የህንድና የፓኪስታን ቢሊዮን ህዝቦች በእንግሊዞች ቅኝ አገዛዝ ሥር ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1947 ህንዶች ከአውሮጳ ቅኝ ገዢዎች ነፃ ከወጡም በኋላ የቀጠለው የፊልም ጥበብ፣ ዛሬ የህንዱን የፊልም ሥራ ማዕከል  ቦሊውድን ከአሜሪካ ሆሊዉድ ቀጥሎ በዓለም ላይ ታዋቂው የፊልም ማምረቻ ማዕከል አድርጐታል፡፡ የፊልም ሥራ ጥበብን ያበለፀገች ሌላኛዋ የዓለማችን አገር ከአንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ህዝብ በላይ የሚኖርባት ሩቅ ምሥራቃዊቷ ቻይና ነች፡፡  የኢትዮጵያ የፊልም ጥበብ ባለሙያዎች በቅጡ ያልፈለግነው ሆኖም በጣም የሚያስፈልገን የፊልም ሥራ አላባ (Element) አለ፡፡ እርሱም በኢትዮጵያና በህዝቦቿ ታሪካዊና አሁንታዊ፤ ነባራዊና ዘመናዊ፤ የከበሩና የበለፀጉ፤ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶች ላይ ማተኮር በሚገባን መጠን በቅጡ ያለማተኮራችን ነው፡፡ ቁርጥ ቁምጥ ባለ የፊልም ጥበብ ቋንቋ እንደሚገባው ያላየነው ይዘት ወይ ይዞታ (Content) በፊልሞቻችን ውስጥ  ሳይሆን በኅብረተሰባችን ህይወት ውስጥ አለ፡በእርግጥ ይሄን መወሳት ተጠቅመው ኢትዮጵያዊ ይዞታን አሟልተውና ተሟልተው የተሰሩ የአገራችን ፊልሞች አሉ፡፡

 

ለምሳሌ :-

“ጉዲፈቻ”፤ “ዓባይ ወይስ ቬጋስ”፤ የጥላሁን ታፈረ እና የሠሎሞን አስመላሽ “ኃየሎም አርአያ”፤ እንዲሁም ማን እንደሠራው ባላውቅም “አሸንጌ” እና ሌሎችም ብዙዎች አሉ፡፡ ከአሥራ አምስት ዓመታት በፊት በ1988 ዓ.ም ወይም በ1989 ዓ.ም ከብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት አራተኛ ፎቅ የወደቀ ጋዜጣ አግኝቼ ኃየሎም አርአያ ስለመራው በሺህ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እሥረኞችን ከመቀሌ እሥር ቤት ለማስለቀቅ ወይም ለማስመለጥ የተደረገውን “Operation Agazi” (አጋዚ ኦፕሬሽን) ካነበብኩ በኋላ፤ አሜሪካ አገር ለኖረው ወዳጄ ዳዊት አማኑኤል ፊልም አድርጐ እንዲሠራው አጥብቄ ነግሬዋለሁ፡፡ ይሄንን ክንውን ፊልም አድርጐ መሥራት በታሪክና በትውልድ ውስጥ ለአገር ስለሚጠቅም(ም) ነው እንዲሠራው የነገርኩት፡፡  ሠራዊት ፍቅሬን ታላቁን የአድዋ ጦርነትና የጥቁር ህዝቦች ድል እንዲሠራው አበክሬ መንገሬ አድዋ የዓለም ታሪክ የተለወጠበትና የተገለበጠበት፤ የኢትዮጵያውያን እና የመላው አፍሪቃውያን እንዲሁም የመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦች ተከታታይ ትውልዶች መኩሪያና መታፈሪያ ስለሆነ ነው፡፡

በፊልም ሥራ፤

በኢትዮጵያዊ ይዞታ (Content) ላይ ይበልጡን ማተኮር ለትውልድ የሚተርፍ አገራዊ ጥቅም የሚያስገኝ ከመሆኑም በላይ የዛሬውን ኢትዮጵያዊ ልብና አእምሮ በጠንካራ ጽኑ መሠረት ላይ ለማነጽ ይረዳል፡፡ በሰው ልጅ አእምሮ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ከሚያሳድሩ የኅብረተሰብ ውጤቶች አንዱ ኪነጥበብ ነው፤ የፊልም ሥራ ደግሞ አንደኛው የኪነ ጥበብ አካል ነው፡፡  ሥራህን እየሠራህ የግል ህይወትህን መምራት ወይም መኖር ብቻ ሳይሆን፤ በምትችለው መጠን ጠንካራና ሥልጡን ኢትዮጵያዊ ትውልድ የመገንባት አገራዊና  ህዝባዊ ኃላፊነት ጭምር አለብህ፡፡ አንድ ኅብረተሰብ ለመጪዎቹ ትውልዶች ሊያወርስ የሚገባው የበለፀገና የታመነ በጐ  ማኅፀን አለው፡፡ ይሄ ማህፀን የከበሩ ማኅበራዊ እሴቶች ማፍሪያ ነው፡፡ እነዚህ የከበሩ ማኅበራዊ እሴቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ ከሚተላለፉባቸው መንገዶች አንዱ የጥበብ ቧንቧ ነው፡፡ ልክ የኤሌክትሪክ ኃይል [እሳት (Current)] በሽቦ ውስጥ እንደሚያልፍ እንደሚተላለፍ ሁሉ፤ የኅብረተሰብ የከበሩና የበለፀጉ ማኅበራዊና ባህላዊ እሴቶችም በጥበብ ቧንቧ ውስጥ ከትውልድ ትውልድ በክብር ይተላለፋሉ፡፡

ይህንን የጥበብ ቧንቧ ከሠሩት አንዱ የፊልም ሥራ (ሙያ) ጥበብ ነው፡፡

አንድ ምሣሌ ላንሳ፤

ከአምስት ዓመታት በፊት ይመስለኛል፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ባዘጋጁት የመድረክ ቲያትር ላይ አምስት ኪሎ ቴክኖሎጂ ፋኪልቲ አዳራሽ በተጋባዥነት ተገኝቼ ተመልክቻለሁ፡፡ ቲያትሩ ወሎ ውስጥ ከትውልድ ትውልድ ሲወራረስ ስለኖረ አንድ የከበረ ማኅበራዊ ሥርዓትን መነሻና መድረሻው አድርጐ የተሠራ ነው፡፡ ወሎ፤ አማርኛ ኦሮምኛ ትግርኛ አገውኛ አፋርኛ የሚነገርበት፣ እሥልምናና ክርስትና በአንድ የልብ ጽላት የሚኖር የሚያድርበት ራሱን የቻለ ውብና ክቡር ዓለም ነው፡፡ ደሴ ከተማ ውስጥ ቢለን የሚገኘው ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች በአንድነት የሚጠቀሙበት ሼህ ዓሊ ጅሩ ጠበል ለዚህ ገለፃ አንዱ ምሥክር ነው፡፡   ቲያትሩ መሠረት ያደረገው ባህላዊ ሥርዓት፤ የተጋጩ ሰዎች ወይም የገዳይና የሟች ቤተሰብ በሠላማዊ መንገድ የሚዳኙበትና እርቀ ሠላም የሚወርድበት የሰለጠነ ማኅበራዊ ክንዋኔ ነው፡፡ በመድረኩና ከመድረኩ ማዶ የሙስሊም ሃይማኖት አባቶች እና የክርስትና ሃይማኖት ካህናት ብቻ ለብቻ ተሰብስበው ሠላማዊ ዳኝነቱን አበጅተው፣ የተበደለው እንዲካስ አድርገው፣ ለዳግመኛ ስህተትና ጥፋት የሚጋብዙ ሁናቴዎችን በፍቅር በመሸምገል በፍትህና በሠላም ፈውሰው እርቀ ሠላም ሲያወርዱ ይታያሉ፡፡ ከዚህ በኋላ የሚኖረው የአካባቢው ማኅበረሰብ ህይወት ከቀድሞው ይልቅ፤ በዳይና ተበዳይ ከመከሰታቸው በፊት ከነበረው ጊዜ ይልቅ፤ ገዳይና ሟች ከመገዳደላቸው በፊት ከነበረው ጊዜ ይልቅ፤ ፍቅርና መተሳሰብን… ያሸመ ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ የከበረ የህዝቡ ሀብት በሆነ ማኅበራዊ እሴት የሚፈወሱት በዳይና ተበዳይ፣ ገዳይና ሟች ብቻ ሳይሆኑ፤  ወጣቶችና ህፃናት ይሄንን የወላጆቻቸው ማህበራዊ ማህፀን ያፈራውን የከበረ ባህላዊ እሴት እያዩ ያድጋሉ፡፡ ይሄ እሴት አንደኛ በጐ ጠቃሚና ሥልጡን ነው፤ ሁለተኛ ደግሞ ከትውልድ ትውልድ ሊወራረስ የሚገባው የኛ ህዝብ ሀብት ነው፡፡ ይሄ የኖረ ያለና የሚኖር፤ መኖርም የሚገባው አንዱ የሰለጠነ የህዝባችን የግጭት አፈታት ዘዴ ነው፡፡

ይሄን የመሰሉ የከበሩ ማኅበራዊ እሴቶች በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦችም ውስጥ በበለፀገ መልኩ አሉ፡፡ በበለፀገ መልኩ ሲባል በሚያስደንቅ ይዞታና ስፋት መጠን ማለት ነው፡፡ በጦርነት ጊዜ ህዝቡ የራሱ የሆኑ የከበሩ የማኅበራዊና ባህላዊ ማህፀኑ ውጤቶች የሆኑ እሴቶች አሉት፡፡ በመከራ ጊዜ አባቶችና እናቶች፣ ሊቀ ካህናት ካህናትና ልሂቃን ወደ  ላይ ይጮሃሉ፤ ድምፃቸውም ወደ ላይ ወደ ሰማያት ይወጣል፡፡ በሠርግ ጊዜ … በሀዘን ጊዜ… በደስታ ጊዜ… በልደት ጊዜ… በቀብር ጊዜ… በበዓል ጊዜ… በበረከት በተድላና በደስታ ጊዜ… እንደዚሁ፤ በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ የሚኖረው የአገራችን ህዝብ በመደነቅ የምንሞላባቸው የራሱ የሆኑ ማኅበራዊና ባህላዊ ክቡር እሴቶች አሉት፡፡…

ከቀድሞው ነባራዊ ነገራችን የምንጥለው የምናስወግደው የሚጐዳ (ጐጂ) ወይም እና የማይጠቅም ነገር አለ፡፡ ለሚቀጥለው ትውልድ መዳረስ ያለባቸው የሚያኮሩ ክቡር እሴቶችም አሉ፡፡በኦሮሞ ህዝብ ውስጥ አንዱ የግጭት አፈታት ሥርዓት ጉማ ነው፡፡ ሠባት ያህል የበዳይ ወይም የገዳይ ቤተዘመድ አባላት ሁሉም ፊታቸው ሊታይ በማይችልበት አኳኋን ነጫጭ ልብስ ለብሰው ከተበዳይ ሟች ቤተ ዘመድ አባላት ጋር በጋራ በመረጡት ስፍራ በሽምግልና ለመዳኘት ይቀመጣሉ፡፡ ነጫጭ ልብስ ከለበሱት ከሰባቱ አንዱ ገዳይ ወይም በዳይ ነው፤ ፊታቸው እስከማይታይ ድረስ ኩታቸውን የሚከናነቡት በተበዳይ ወይም በሟች ቤተ ዘመድ አባላት ዘንድ የበዳይ ወይ የገዳይ ማንነት በውል እንዳይታወቅ እና ቁጣን እንዳይቀሰቅስ ነው፡፡

ኢቫንጋዲ:-በፈንጠዚያ በጭፈራና በድንግል ድሪያ የተመላ “የጋምቤላ ህዝብ የተከበረ ባህል አንዱ መታያ ነው ሊባል ይቻላል፡፡

ገዳ System of God ደግሞ አያሌ የከበሩ (አሥራ ሁለት ሺህ ዘመናት የዘለቁ) ኅብረተሰባዊ መተዳደሪያ እሴቶች ያሉት እና የኦሮሞ ህዝብ አባቶች ሥረ መሠረት ያለው በዚህች ዓለም ላይ ከተከሰቱ ጥቂት ታላላቅ የኅብረተሰብ አኗኗር ፍልስፍናዎች አንዱ ምናልባትም ዋናው ነው፡፡

እነዚህ መወሳቶች ለምሳሌ ማሳያነት የቀረቡ ሦስት ዘለላዎች ናቸው፡፡ ከጋምቤላ ከወሎና ከኦሮሞ፡፡ ወደ መላው ህዝባችን ከገባን እና ካጠናን እነዚህ እሴቶች በይዞታቸውም ሆነ በብዛታቸው የተለያዩና በርካታ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ እነዚህ የህዝብ ሀብቶች ያልተነካኩ ድንግል Original ናቸው፤ በዚህ የከበረ እሴት ሥርዓተ ክንውን ሂደት ውስጥ የምናየው የምንሰማው… ሁሉም ነገር ያልተነካካ ድንግል (ፍፁም ኢትዮጵያዊ የሆነ) እንደገናም በተለይ የዚያን ህዝብ ድንግል የማንነት አካል የሚያሳይና የሚገልጥ ነው፡፡ ህዝቡ ውስጥ ገብተህ እነዚህን ማኅበራዊ ፋይዳዎች በደንብ ብታይ በክብራቸውና በሥልጡንነታቸው ከመደነቅ አልፈህ፤ ኢትዮጵያን በቅጡ የማላውቅ ኢትዮጵያዊ ነኝ እስከ ማለት ትደርሳለህ፡፡  አዲሱና በአጭር ጊዜ ወስጥ ቀልጣፋ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለው የኢትዮጵያ ፊልም  ኢንዱስትሪ እነዚህን እጅግ የከበሩ ነባራዊ፣ ሥልጡን፣ ማኅበራዊና ባህላዊ አገራዊ እሴቶቻችንን ለማየት የቻለው በጣም በትንሹ ቆንጠር አድርጐ ነው፡፡ ነገር ግን በደንብ ብናየውና ብንሄድበት ከአገራችን ህዝቦች ባህላዊና ታሪካዊ፤ ተፈጥሮአዊና ሃይማኖታዊ፤  ሰብአዊና ማህበራዊ… ማህፀን ውስጥ ብንዝቀው ተዝቆ የማያልቅ ውድና ክቡር፤  ስልጡንና የሚደነቅ የበለፀገ ድንግል ሀብት እናገኛለን፡፡ …በፊልም ሥራ ጥበብ ውስጥ በዚህ ይዘት ላይ ተመስርተን ስንሰራ የምናገኛቸው ጥቅሞች ቢያንስ ከአምሥት በላይ ናቸው፡፡ እንደ ሙያ ራሳችንን እንጠቅማለን ጥበብን እናጐለብታለን፤ ለአዲሱ ኢትዮጵያዊ ትውልድ ነባራዊውን የወላጆቹን በጐ እሴት እንዲወርስ እናስችላለን፤ ለህዝባችን ያለንን ክብር በማሳየት ለሺህ ዘመናት አፅንቶ ያቆያቸውን ብርቅ እሴቶችን እናበለፅጋለን፡፡ ለውጭ አገር ሰዎች ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የማያውቁትን እንዲያውቁ እናደርጋለን፤ አዳዲስ የአንትሮፖሎጂ የምርምር በሮችን እንከፍታለን፡፡ ይሄ ሁሉ በአንድነት ሲታሸም በአካሉ በአእምሮውና በመንፈሱ የተሟላ ጠንካራና ሥልጡን ኢትዮጵያዊ ዜጋ (ትውልድ) ለማነፅ እና ለማፍራት ጉልህ ሚና ይጫወታል፡የትኛውንም ጥበብ ስትሰራ (ለአንተ ከሚሰጠው ጥቅም በተጨማሪ) ለህዝቡ ለሀገርህ እንዲጠቅም ለማድረግ ትችላለህ፤ የህዝቡን ድንግል ሀብቶች ታከብራለህ ታስከብራለህ፤ ይሄን ክቡር እሤት ከትውልድ ወደ ትውልድ ታዳርሳለህ፡፡ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከተሰሩ ፊልሞቻችን ውስጥ የኛ ባልሆኑ የውጪ አገር ይዞታና አቀራረብ ቅኝት የተኳሉ… ፊልሞቻችን ጥቂት አይደሉም፡፡ በጭራሽ እነዚህ መሠራት የለባቸውም የሚል አቋም የለኝም፡፡ ነገር ግን በይበልጥ ማተኮር ያለብን በራሳችን ላይ ነው፤ ያ ደግሞ በጥድፊያ የሚሰራ ሳይሆን ጥናትና ማጤን የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ አጭርና ቆራጥ አነጋገር፤ ይሄንን ማድረግ በአንድ ድንጋይ ብዙ  ዒላማ (በአንድ ጊዜ) እንደ መምታት ያለ ነው፡፡ ይሄ ክቡር እሴት በፊልም ጥበብ ሥራ ውስጥ እንዳይጐሳቆልና የክብር ደረጃውም ዝቅ እንዳይል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ድንግልናው እንደተጠበቀ መቅረብ ወይ መሠራት አለበት፡፡ይሄንን ለማድረግ የመጀመሪያው ተግባር መፈለግ ነው፤ ያልፈለግነው የሚያስፈልገንን ነው የምለው ስለዛ ነው፡፡

ሰላምዎ ይብዛ! በፍቅር!

Soli. Deo.Gloria!

 

 

 

Read 2960 times Last modified on Saturday, 24 December 2011 09:34