Saturday, 19 July 2014 11:09

ዕለት ደራሽ የእርዳታ ትራንስፖርት ድርጅት ከውድቀት አፋፍ ተመልሶ በዕድገት ጎዳና ላይ ይገኛል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

           ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም በታተመው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “ዕለት ደራሽ የዕርዳታ ትራንስፖርት ድርጅት ብዙ ሚሊዮን ብሮች በሙስና ተመዝብሯል ተባለ” በሚል ርዕስ የድርጅቱ የሕግ አገልግሎት ኃላፊ፣ የድርጅቱ የስነ-ምግባር መኮንን እና የመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር ም/ሊቀመንበር ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል አቀረቡ የተባለውን ጥቆማ በተመለከተ የሰራችሁትን ዘገባ ለንባብ ማብቃታችሁ ይታወሳል፡፡
ጋዜጣው ለሕዝብ የወገነና ለሁሉም በእኩል አገልጋይነት የቆመ ነው ብለን ስለምናምን ጠቋሚዎች ላቀረቡት ጥቆማ በማስረጃ የተደገፉ ምላሾች ለመስጠት እንወዳለን፡፡
በቅድሚያ ከጠቋሚዎች መሀከል በተለይም የሕግ አገልግሎት ኃላፊውና የስነ-ምግባር መኮንኑ የተሻሻለውን በፌደራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 433/1997 አንቀታ 27/7 የተገለፀውን ድንጋጌ በመጣስ፣ ጠቋሚዎች ለፌደራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ያቀረቡት ጥቆማ በምርመራ ላይ መሆኑን እያወቁ፣ ምርመራውን ከያዘው ክፍል ፈቃድ ውጪ ስለሁኔታው መጻፋቸው ለሕግ የበላይነት ያላቸውን አነስተኛ ግምት ያሳያል፡፡ ይህም ሊሆን አይችልም ከተባለ የጥቆማቸውን ውጤት ቀድመው በመገመት የመጨረሻውን የስም ማጥፋት ዘመቻ በማካሄድ የድርጅቱን ስም፣ ክብርና ዝና በማጉደፍ ከድርጅታችን ጋር ጥሩ የስራ ግንኙነት ያላቸውን መንግስታዊም ሆኑ የግል ድርጅቶች ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገቡና ከድርጅቱ ጋር ቀጣይ ግንኙነት እንዳይኖራቸው በማድረግ ድርጅቱ ከዕድገት ጉዞው እንዲገታ ዛሬም ተኝተው እንደማያድሩ ያሳያል፡፡ ስለሆነም የድርጅቱ ማኔጅመንት ለሕግ ያለውን ክብርና ተገዥነት ግምት ውስጥ በማስገባት ለቀረቡት ጥቆማዎች ዘርዘር ያለ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቦ፣ ጠቋሚዎች ለጋዜጣው ባቀረቡዋቸው ጥቆማዎች ጠቅለል ያሉ ምላሾች ለመስጠት ተገዷል፡፡
ጠቋሚዎች በዚሁ ጋዜጣ እንደገለጹት ብዙ ሚሊዮን ብሮች በሙስና ተመዝብሯል በማለት ድርጅቱን በበላይት ለሚመራው የሥራ አመራር ቦርድ ያቀረቡ ሲሆን ቦርዱ በተቋቋመው ኮሚቴ ጥቆማው ተጣርቶ ውድቅ ሲሆንባቸው በቅርፅ ተመሳሳይነት ያላቸው በይዘት ተመሳሳይነት የሌላቸውን ጥቆማዎቻቸውን በፌደራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንና ሌሎች ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ላሉዋቸው መንግስታዊ ተቋማት አቅርበዋል፡፡
ጠቋሚዎች በሙስና ተመዝብሯል ብለው በዝርዝር የገለጹዋቸው ነጥቦች፡-
ድርጅቱ የበላይ ተቆጣጣሪ መስሪያቤት ማለት በግብርና ሚኒስቴር የተቋቋመና ሦስት አካላት ያሉበት የባለሙያዎች ቡድን የማጣራት ስራ አከናውኖ ውጤቱን /ሪፖርቱን/ በፌደራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አቅርቧል፤
በፌደራል የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሙስና መከላከል ዳይሬክቶሬት ባለሙያዎችን መድቦ የድርጅቱን የግዥ አፈፃፀም ስርአት በተመለከተ የማጣራት ሥራ ተከናውኖ የምርመራው ሪፖርት ቅጂ ለድርጅቱ ደርሷል፡፡ ይሁን እንጂ በምርመራው ሪፖርት ጠቋሚዎቹ እንዳሉት፤ ድርጅቱ የግዥ መምሪያ የለውም፣ በተሟላ የግዥ እቅድ አይመራም፣ ወዘተ… በማለት ለአንባቢ በቂ ስእል በማይሰጥና ግራ በሚያጋባ መልኩ አልተገለፀም፡፡
ድርጅቱ አዲስ ሰራተኞችን የሚቀጥርበት ግልፅ የሆነ መመሪያና ደንብ ያለው በመሆኑ በህገወጥ መንገድ የተቀጠረ አንድም ሰራተኛ የለም፡፡ ድርጅቱ ያሉት ሁለት የመለዋወጫ እና አንድ የፅ/መሣሪያዎች መጋዘኖች ሲሆኑ ወደመጋዘኑ ለሚገቡም ሆነ ለሚወጡ መለዋወጫዎችና የጽሕፈት መሳሪዎች ተገቢው የገቢና የወጪ ሰነድ እየተዘጋጀላቸው አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ በመጋዘኖቹ ውስጥ የሚገኙ ንብረቶችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ አመታዊ የንብረት ቆጠራ በማካሄድ ከሒሳብ መዝገብ ጋር እንዲታረቅ ይደረጋል፡፡
የሂሳብ ማወራረጃ ደጋፊ ሰነዶች እንደወጪው አይነት የተለያዩ በመሆናቸው፣ የትኞቹ አይነት ደጋፊ ሰነዶች እንዲጠፉ፣ መቼ ስራ ላይ የዋሉና የየትኞቹ ተሽከርካሪዎች የተጠቀሙበት የጭነት ማዘዣዎችና የነዳጅ መጠየቂያ ፓዶች ሆን ብለው እንዲጠፉ እንደተደረገ የቀረበልን ማስረጃ የለም፡፡ እነዚህ ሰነዶች ደግሞ የሂሳብ ሰነዶች በመሆናቸው ድርጅቱ በየዓመቱ ሂሳቡን በወጪ ኦዲተሮች ሲያስመረምር በኦዲተሮች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ምርመራ የሚደረግባቸው በመሆኑ በጠቋሚዎቹ እንደተገለፀው የሚሰወሩ አይደሉም፡፡
ድርጅቱ ያለጨረታ የገዛቸው የኢንጀክሽን ፓምፖች የሉም፡፡ ይሁን እንጂ የቺፕውድ ግዥና ከቆሙ የጭነት ተሸከርካሪዎች የተፈቱ አሮጌ መለዋወጫዎችን /ካኒባላይዜሽን/ በተመለከተ በፌደራል የስነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በተመደቡ ኦዲተሮች ተገቢው ምርመራ ተከናውኖ የምርመራው ሪፖርቱ ቀርቧል፡፡ ውጤቱ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡
የድርጅቱን የሂሳብ አያያዝ በተመለከተ በፌደራል የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና  ኮሚሽን በተመደቡ የውጭ ኦዲተሮች ተገቢው ምርመራ ተከናውኖ የምርመራው ሪፖርቱ ለኮሚሽኑ ቀርቧል፡፡ ከቀረበው የኦዲት ሪፖርት ቅጅ መረዳት እንደተቻለው ብር 25 ሚሊዮን የመንግስት ገንዘብ ስለመመዝበሩ፣ የሂሳብ ማወራረጃ ደጋፊ ሰነዶች በመጥፋታቸው ደግሞ ከብር 5 ሚሊዮን በላይ ስለመመዝበሩ በምርመራው ሪፖርት የተገለፀ ነገር የለም፡፡ ከምርመራው ሪፖርት ውጪ ተመዘበረ ተብሎ የተገለፀው ገንዘብ ጠቋሚዎች አእምሮ ውስጥ ብቻ የተፃፈ ወይም የተሳለ ስእል ነው ብለን እንገምታለን፡፡ ጠቋሚዎች እንዳሉት፤ በሂሳብ ምርመራ ወቅት በጉድለት የተመዘገበ ገንዘብ ተመርማሪው በፈለገበት ጊዜ የጎደለው ብር ተገኝቷል ብሎ ምርመራውን ላከናወነው የኦዲት ቡድን (ኦዲተር) ምለፁ ብቻ ያድነዋል ብሎ ማሰብ ጠቋሚዎች ስለኦዲት ሥራ ያለማወቃቸውን የማያውቁ መሆናቸውን የሚገልፅ ወይም እራሳቸውን እንደአዋቂ በመቁጠር ከሙያው ባለቤቶች ጠይቆ ለመረዳት ካለመፈለግ የመነጨ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባዋል፡፡
በአጠቃላይ ደርጅቱ ከ1997-2001 ዓ.ም በነበሩት 5 ዓመታት በኪሳራ ሲጓዝ የነበረና ለሰራተኛው ደመወዝ እንኳ ለመክፈል አቅቶት ለመውደቅ ሲንገዳገድ የነበረ መሆኑን የድርጅቱን ትክክለኛ ገፅታ ከሚያሳየውና በውጪ ኦዲተሮች ትክክለኛነቱ የተረጋገጠውን የሂሳብ መግለጫዎች ማየት ይቻላል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ በጠቋሚዎች የስም ማጥፋት ዘመቻ እየተካሄደበት የሚገኘው ማኔጅመንት፤ ከተቋቋመበት ከ2002-2005 ዓ.ም ድርጅቱ ይጓዝ ከነበረበት የቁልቁለት መንገድ በማውጣት፣ በውጪ ኦዲተሮች የተረጋገጠ ትርፍ በማስመዝገብና የአገልግሎት ዘመናቸውን የጨረሱ የጭነት ተሽከርካሪዎች በአዲስ ለመተካት በተደረገ ጥረት 400 ኩንታል የመጫን አቅም ያላቸው 15 ዘመናዊ የጭነት ተሽከርካሪዎች ባለቤት እንዲሆን ያደረገ ሲሆን ዛሬም መንግስት በሰጠው ምቹ ዕድል ከ560 ኩንታል በላይ የመጫን አቅም ያላቸው 20 የጭነት ተሽከርካሪዎች ባለቤት እንዲሆን በማድረግ ላይ የሚገኝና የድርጅቱ ሰራተኞች ከ2002 ዓ.ም በፊት አግኝተውት የማያውቁትን ከ2-3 ወር ደመወዝ ማበረታቻ /ቦነስ/ በየዓመቱ እንዲያገኙ ያደረገ ነው፡፡ ይህ ሊዋጥላቸው ያልቻሉ ከማስረጃ ይልቅ ለአሉባልታ ቅርብ የሆኑ፣ የማኔጅመንቱን ጥንካሬና ከስራ አመራር ቦርድ ጋር ያለው የጠበቀ የስራ ግንኙነት ያላስደሰታቸው ጠቋሚዎች በሚያናፍሱት ተጨባጭ ያልሆነ ክስ ተደናግጦ ማኔጅመንቱ ድርጅቱን ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ጥረት አይገታም፡፡
እነዚህ ግለሰቦች በድርጊታቸው በሰራተኛው የተተፉበት ወቅት ላይ ስለሚገኙ በማስረጃ ባልተደገፉ ጥቆማቸው ድርጅቱ በአዲስ መልክ እየተደራጀ ባለበት በዚህ ወቅት በመሯሯጥ በመገናኛ ብዙሀን የድርጅቱን ስምና ክብር በማጉደፍ የስልጣን ጥማቸውን /ፍላጎታቸውን/ ለማርካት ያላቸውን ፍላጎት ለማሳካት የማያንኳኩት የባለስልጣን በር፣ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡
ከጠቋሚዎቹ መሃል ህይወታችን ለአደጋ ተጋልጧል፣ ሁለት ጊዜ በጥይት ተስቻለሁ የሚሉት የቀድሞው የደርግ ሻምበልና የአሁኑ አቶ ያለው አክሊሉ የፈጠራ ወሬዎችን ሲያወሩና ሲያስወሩ ድፍን አንድ አመት ሞልቷቸዋል፡፡ የነፍስ ግድያ ሙከራ ተደረገብኝ ለሚሉት የሀሰት አሉባልታቸው ይረዳቸው ዘንድ እነሱ ባሰቡትና በፈለጉት መልኩ የማኔጅመንት አባላት ላይ የትንኮሳ ስራ እየሰሩ ያሉ ቢሆንም የማኔጅመንት አባላቱ ጉዳዩ በፍ/ቤት እንዲታይላቸው ከማድረግ ባለፈ ጠቋሚዎች ድርጅቱ ግቢ ውስጥ ብቻቸውን ውለው ቢያድሩ እንኳ ነብሳቸውን እስከማጥፋት የሚያደርስ ወንጀል ለመስራት ፍላጎት ያለው የማኔጅመንት አባል እንደሌለ ልቦናቸው እያወቀ፣ ከድርጅቱ ውጪ ባሉ ወገኖች ከንቱ ውዳሴና ተቀባይነት ለማግኘት የሚያደርጉት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻቸው አካል ነው፡፡
(ከ“ዕለት ደራሽ የእርዳታ
ትራንስፖርት ድርጅት” ማኔጅመንት)

Read 2795 times