Saturday, 19 July 2014 11:27

የኢዴፓ አባላት ታስረው ዋሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

ለዛሬ የጠራውን ህዝባዊ ስብሰባ ሰርዟል

     የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ባለፈው ዕረቡ ታስረው ካደሩ 6 አባላቱ በተጨማሪ ትላንት 8 አባላቱ ታስረው እንደዋሉ ገልፆ፤ ዛሬ ለማካሄድ ያቀደውን ህዝባዊ ስብሰባ እንደሰረዘ አስታወቀ፡፡ ህዝቡ ሳይቀሰቀስና መረጃ ሳይደርሰው የሚካሄድ ስብሰባ ግቡን መምታት አይችልም ያሉት የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ አባላቶቻችን ታስረው ቅስቀሳ ማድረግ ስላልተቻለ ስብሰባው ተሰርዟል ብለዋል፡፡ ፓርቲው በመጪው አገር አቀፍ ምርጫ፣ በሰብአዊ መብት አያያዝ፣ በወቅታዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ከህዝብ ጋር ለመወያየት ነበር ስብሰባውን የጠራው ተብሏል፡፡
ለህዝባዊ ስብሰባው ከሚመለከተው አካል የዕውቅና ወረቀት ከተቀበሉ በኋላ ባለፈው ረቡዕ ቅስቀሳ መጀመራቸውን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ “የስብሰባ እንጂ የቅስቀሳ ፈቃድ የላችሁም” በሚል በቂርቆስ ክ/ከተማ ቄራ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ስድስት ያህል የፓርቲው አመራሮችና አባላት ታስረው ሐሙስ ዕለት በዋስ መፈታታቸውን ገልፀዋል፡፡ አባላቱ ከተለቀቁ በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቅ ክፍልና የስብሰባ ፈቃድ ኃላፊ ለሆኑት አቶ ማርቆስ ብዙነህ፤ ለቅስቀሳ ሌላ ፈቃድ ይሰጥ እንደሆነ በአካል ቀርበው መጠየቃቸውን የጠቆሙት የፓርቲው የስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ኤርሚያስ ባልከው፤ በመስተዳደሩም ሆነ በሌላ አካል የቅስቀሳ ፈቃድ እንደማይሰጥና ቅስቀሳ ማድረግ እንደማይቻል እንደነገሯቸው ጠቁመዋል፡፡
“እውቅና ለተሰጠው ህዝባዊ ስብሰባ ቅስቀሳ ማድረግ መብት ነው” በሚል በትላንትናው እለት እንደገና ቅስቀሳ መጀመራቸውን የገለፁት አቶ ኤርሚያስ፤ በቅስቀሳ ላይ የነበሩ 8 አባላቶቻቸው እንደገና በፖሊስ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ማምሻው ላይ መፈታታቸውን ተናግረዋል፡፡ “ገዢው ፓርቲ የሚያካሂደው ኢ-ሰብአዊ ተግባር ለሰላማዊ ትግሉ እንቅፋት እየፈጠረብን ነው” ያሉት የፓርቲው ፕሬዚዳንት ስራ አስፈፃሚው አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ የአቋም መግለጫ እንደሚያወጣ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማስታወቂያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ማርቆስ ብዙነህ በበኩላቸው፤ ፓርቲው የህዝባዊ ስብሰባ የማሳወቂያ ደብዳቤ አስገብቶ ፈቃድ ማግኘቱን ገልፀው፣ ለቅስቀሳ ፈቃድ ይሰጥ አይሰጥ ግን እንደማያውቁ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

Read 2976 times