Saturday, 19 July 2014 11:32

“...እናቶችና ገጠመኞቻቸው...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ ruthebebo@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

በዚህ እትም ለንባብ ያበቃነው የሁለት እናቶችን የእርግዝና እና የወሊድ ገጠመኞች እና የህክምና ባለሙያዎችን አስተያየት ነው፡፡ አንዱዋ እናት ወ/ሮ ልእልና ይበልጣል ስትሆን ሌላዋ ደግሞ ወ/ሮ መቅደስ መሐሪ ናት፡፡ ወ/ሮ ልእልና እንደሰጠችው እማኝነት ልጁዋን የተገላገለችው በምጥ ሳይሆን በቀዶ ሕክምና ነው፡፡ ነገር ግን የህኪምዋም ሆነ የእርስዋ የመጀመሪያ ውሳኔ በምጥ እንደምትወልድ ነበር፡፡ እንደሚከተለው ሀሳቡዋን ትገልጻለች፡፡ “...እኔ የመተንፈሻ አካል ችግር ወይንም የብርድ አለርጂክ ስላለብኝ ወደ መውለጃዬ ቀን እየተቃረብኩ ስመጣ ምናልባት በምጥ መውለድ ያልቻልኩ እንደሆነ ወደ ኦፕራሲዮኑ መሄዴ ስለማይቀር ምን አይነት ማደንዘዣ ነው መውሰድ ያለብኝ በማለት ሐኪሜን ሳማክረው ሙሉ ማደንዘዣ ሳይሆን በጀርባ የሚሰጠውን ግማሽ መውሰድ እንዳለብኝ ነገረኝ፡፡ ይህንኑ ሀሳብ ይዤ ወደ ጽንስና ማህጸን ሐኪሙ ማለትም እኔን ሲከታተለኝ ወደነበረው ዶ/ር ሄድኩ፡፡ የሄድኩበት ዋና ምክንያትም እሱን ካነጋገርኩ በሁዋላ በተጨማሪም የሰመመን ሰጪዋን ለማነጋገር ነበር፡፡ ነገር ግን ምርመራው ሲደረግልኝ የስኩዋር መጠኔ ከፍ ብሎ ታየ፡፡ እንደገናም የልጄም የልብ ምት ጨምሮ ነበር፡፡ እኔም ባለቤቴም ተደናገጥን፡፡ ከዚያም ሐኪሙም በአስቸኳይ እንድተኛ እና እንድወልድ በማዘዙ ሳላስበው ምጡ ቀርቶ በኦፕራሲዮን እንድወልድ ተደረገ፡፡ ከቤተሰቦቼ እንደተነገረኝ ከሆነ ሐኪሙ ልክ እኔን አዋልዶ ሲወጣ... ...እንዴት ነች? እንዴት ነች?...ሲሉት “...እሱዋ ምን ትሆናለች... ወንድ ልጅ ተገላግላለች...እኔ ነኝ እንጂ... ይላል... በሁዋላም እናቴ... ውይ...አንተ ምን ሆንክ? ስትለው...ይህንን ጮማ ለማገናኘት (ለመስፋት) ስታገል ደከመኝ...አለ፡፡ እኔም ደግሞ ወደ አልጋዬ ተመልሼ ከሰመመኔ በደንብ ስነቃ... ቤተሰቦቼ ...እንዴት ነበር? ሲሉኝ... “...ሐኪሜ ብቻውን 50/ኪሎ ጤፍ በሆዴ ላይ እንደሚያቦካ አይነት ስሜት ይሰማኝ ነበር...” ብያለሁ፡፡ ዶ/ር ሰሎሞን ቁምቢ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምጥ መውለድን በሚመለከት የሚከተለውን ብለዋል፡፡ “...በምጥ መውለድ ያማል፡፡ ምጥ እንደሚያም ማንም ያውቃል፡፡ አንድ መጽሐፍ... ምጥ ምን ያህል እንደሚያም ሲጠቅስ በድንገት ሰዎች የሚሞቱበት የልብ ሕመም ብቻ ሲበልጠው በስተቀረ አቻ የሌለው ሕመም ነው፡፡ ነገር ግን ሕመሙ እንደሚኖር ታውቆ እና የስነልቡና ዝግጅት ተደርጎበት እንዲሁም ከዚያ የሚገኘው ውጤት እንደሽልማት የሚያስደስት ስለሆነ ያንን ሕመም የሚያስረሳ ይሆናል እንጂ ሕመሙ ሕመም ነው፡፡ ነገር ግን ተፈጥሮአዊ ሂደት ስለሆነ ማንኛዋም ሴት ችግር ካልገጠማት በስተቀር በምጥ እንድትወልድ ነው የሚመከረው፡፡...” ወ/ሮ ልእልና እንዲህ ትላለች፡፡ “...በእድሜዬ ወደ ሰላሳው አመት የገባሁ ስለሆነ ድጋሚ ልጅ መውለድ ስለምፈልግ ኦፕራሲዮኑን አልፈልገውም ነበር፡፡ ምክንያቱም ማራራቅ በሚባለው ፕሮግራም ሶስትእና አራት አመት መቆየት ለእኔ ከእድሜዬም አንጻር ስለሚከብደኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡ ኪሎዬ ወደ 100/ደርሶ ነበር፡፡ ምግቤን በተለይም ወደ ስምንትና ከዚያ በሁዋላ ባለው ጊዜ ስኩዋር ቴምር የመሳሰሉትን በጣም እወስድ ነበር፡፡ የእርግዝና ስሜት እንጂ ሌላ ነገር ነው ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ ነገር ግን በእራሴም ላይ የጤና ችግር አስከትሎ ልጄንም ላጣው ስለነበር ሐኪሜ ከእግዚአብሔር ጋር ከአደጋ አውጥቶኛል፡፡” ዶ/ር መብራቱ ጀምበር የጽንስና ማህጸን ሐኪም እና የብራስ የእናቶችና የህጸናት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር እንደሚሉት እርግዝና በተቻለ መጠን ከ24-35 አመት እድሜ ክልል ውስጥ ቢሆን ይመረጣል፡፡ እስከ 24 የሚቆይበት ምክንያት ለትምህርቱ እና ለእድገቱ መመቻቸት ሲባል ሲሆን ከ35/ አመት በሁዋላ አለማርገዝ የሚመረጥበት ምክንያት ደግሞ ለተለያዩ ችግሮች መጋለጥን ለማስወገድ ሲባል ነው፡፡” የሁለተኛዋ አስተያየት ሰጪ ወ/ሮ መቅድስ መሐሪ ገጠመኝ የሚከተለው ነው፡፡ “...ባለቤቴ እና እኔ ልንጋባ ስንል ሳላስበው ድንገት ነው ያረገዝኩት፡፡ እርግዝና ለእኔ ቀላል አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ከመጠን በላይ ወፍሬ ነበረ፡፡ ባረገዝኩበት ወቅት እድሜዬ 23 አመት/ ሲሆን ሱሪ የምለብሰው 28 ቁጥር ነበር፡፡ በዚህ ላይ ልክ እንዳረገዝኩ ስራ ተቀጥሬ አገር ለውጬ ወደ ሞቃታማ አካባቢ ሄጄ ነበር፡፡ ምንም እንኩዋን ሕመም ባይሰማኝም ብቻዬን ስለነበርኩ ጭንቀት ይሰማኝ ነበር፡፡ ዙሪያዬን የነበሩ ሰዎችም በየጊዜው ክብደቴ እየጨመረ ሲሄድ ያስፈራሩኝ ነበር፡፡ ባረገዝኩበት ወቅት ወደ ሰላሳ ኪሎ ግራም ክብደት በመጨመሬ በጣም እፈራ ነበር፡፡ ከማርገዜ በፊት እስፖርት እሰራ ስለነበር እና በእርግዝናው ወቅት እስፖርቱን ስላቋረጥኩኝ ምናልባትም ክብደቴን ከልክ በላይ ያደረገው እሱ ይሆናል የሚል ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ዶ/ር ሰሎሞን ቁምቢ እስፖርትን እና እርግዝናን በሚመለከት እንዲህ ብለዋል፡፡ “...አንዳንድ ሰዎች ተሳስተው ይሁን ወይንም ከልክ በላይ ጥንቃቄ ለማድረግ... ብቻ በራሳቸው ምክንያት በእርግዝና ወቅት እስፖርት ማድረግ አይመከርም ብለው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን አዲስ አይነት እና ከበድ ያለ አይሁን እንጂ ቀደም ሲል የተለመደውን የአካል እንቅስቃሴ እንዲሁም ውሃ ዋና የመሳሰሉት በእርግዝና ጊዜ አይከለከሉም፡፡ ጠዋትም ይሁን ወደ አመሻሹ የእግር ጉዞ ማድረግ የሰውነት ማጎልመሻ እንቅስቃሴን ለእርጉዝ ሴት በሚያመች መልኩ መስራት ይመከራል፡፡ ነገር ግን እንደ ቦክስ ወይንም ከበድ ያለ የአካል እንቅስቃሴ የሚፈልግ እስፖርት ለመስራት ግን አስቸጋሪ እንደሚሆን አይጠረጠርም፡፡” ወ/ሮ መቅደስ አመጋገብዋን በተመለከተ የሚከተለውን ብላለች፡፡ “...ምግብን በመመገብ በኩል ምንም ችግር አልነበረብኝም፡፡ በጣም በተከታታይ ይርበኝ ስለነበር ሌሊት ሳይቀር እመገብ ነበር፡፡ የተለያዩ ምግቦችን በየሰአቱ ሳይቀር ከጠረጴዛዬ ላይ አመቻችቼ እወስድ ነበር፡፡ በተለይም ከሰባተኛው ወር በሁዋላ የነበረውን ሁኔታ ማስታወስ ይከብደኛል፡፡ እናም ከመውለዴ በፊት 68/ኪሎ የነበርኩት ልወልድ አካባቢ ወደ 95/ኪሎ ገባሁ፡፡ ከዚያም በድንጋጤ መመገቤን አቆምኩ ማለት እችላለሁ፡፡ በዚያ ምክንያትም ከእናቴ ጋር ጭቅጭቅ ሆነ፡፡ ውሀ መጠጣት፣ ቅጠላ ቅጠል መውሰድ ጀመርኩ፡፡ ግን በዚያች ወቅት ምንም እንኩዋን እንደፈራሁት መቶ ኪሎ/ባልገባም ወደታች ግን ምንም አልቀነስኩም፡፡ ወ/ሮ ልእልና አመጋገብን በተመለከተ የምታስታውሰው እንደሚከተለው ነው፡፡ “...እኔ በጣም የምወስደው ጣፋጭ ነገር ነበር፡፡ በእርግጥ ሌላ ነገር አልመገብም ማለት አይደለም፡፡ የደሜ አይነት ኦ ስለሆነና ስጋ አያወፍርም ብዬ ስለማስብ ስጋ ...ጮማ የሆነ ሁሉ እመገብ ነበር፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ልክ እንደትንሽ ልጅ አይስክሬም አይቀረኝም ነበር፡፡ ባለቤቴ ይከፋታል ብሎ ስለሚያስብ ግዛልኝ ያልኩትን ነገር ሁሉ ገዝቶ ይገባል፡፡ ምግብ ሲቀርብ በእሱም እጅ በእራሴም እጅ ነበር የምመገበው፡፡ እንዲያውም አንድ ቀን እናቴ ይሄንን ታዝባ ...እባክህን ...አንተ ማጉረስህን ቀንስ እና በእራስዋ እጅ ትብላ፡፡ ወይንም ደግሞ በእራስዋ እጅ መብላትዋን ትተውና አንተ አጉርሳት ብላ ተናግራለች፡፡ ምክንያቱም ውፍረቴ እያደር ስለሚያሳስብ ነበር፡፡ በሁዋላም የልጄ የልብ ምት የመፍጠኑ ምክንያት ከዚህ ጋር ተያይዞ መሆኑን ባለሙያዎች ነግረውኛል፡፡ ወ/ሮ መቅደስ እንደምታስታውሰው ለመውለድ ወደሆስፒታል የገባች እለት የዋለችው ከቢሮዋ ነበር፡፡ “...ከቢሮዬ የምውልበት ምክንያት ከቤቴ እንዳልውል ብዬ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከቤቴ ስውል ይርበኛል፡፡ ከራበኝ ደግሞ እበላለሁ፡፡ ነገር ግን የዚያን እለት የተወከልኩበት ኃላፊነት ስለነበረኝ ስብሰባ መምራት ይጠበቅብኝ ነበር፡፡ ነገር ግን በድንገት የሽርት ውሀ ፈሰሰኝ፡፡ ለእናቴ ስልክ ደውዬ ሁኔታውን ስነግራት በጣም ተቆጣችኝ፡፡ ውሀው ይፈሳል እንጂ እኔ እኮ ደህና ነኝ... ስላት በይ አሁኑኑ ስብሰባ ሳትገቢ ለሐኪምሽ ደውይና መልሱን ንገሪኝ አለችኝ፡፡ ደነገጥኩና ለሐኪሜ ስደውልለት በይ ባስቸኳይ ነይ አለኝ፡፡ ...በቃ... ስብሰባውን ትቼ...ወደ ሆስፒታል ሄድኩ... ልጁም ኪሎው ከባድ ስለነበር በሲዘር..ኦፕራሲዮን.. ወለድኩ፡፡” ወ/ሮ ልእልና ይበልጣል እና ወ/ሮ መቅደስ መሐሪ በተለያዩ የግል ሆስፒታሎች የወለዱ ሲሆን ሁለቱም ተመሳሳይ ቅሬታዎች አሉዋቸው፡፡ በእርግዝና ወቅት በተለይም ለመውለድ በሚዳረሱበት ጊዜ የጡትን ጫፍ እንዴት ማውጣት እንደሚገባ ...እንዴት ልጅን ማጥባት እንዳለባት አንዲት እናት ተገቢውን ልምምድ የሚያደርጉባቸው ተቋማት የመኖራቸውን ያህል አንዳንዶቹ ደግሞ ጭርሱንም አይሞክሩትም፡፡ አንዲት እናት ያውም በኦፕራሲዮን ወልዳ ሕመሙ...መድሀኒቱ አድክሞአት ባለችበት ሁኔታ እንኩዋንስ ልጅዋን ልታጠባ አካልዋንም የምታንቀሳቅሰው በመከራ ነው፡፡ በዚህ ላይ የሰመመን መድሀኒቱ ከሰውነቷ እስኪወጣና ተፈጥሮአዊ ሁኔታዋ በትክክል እስኪመለስ ድረስ ህጻኑ ወተት በጡጦ ወይንም በክዳን የሚሰጠው ሲሆን ከዚያ በሁዋላ ገና ያልለመደውን ጡት ይዞ ጫፍ አውጥቶ ወተት ለማግኘት ልጁም ትእግስት አይኖረውም፡፡ በህመም ላይ ያለች እናት ደግሞ የልጁዋን ጩኸት ለመስማት ስለማትፈልግ ወደ ጡጦዋ ትሄዳለች፡፡ ስለዚህ ይህ መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው ብለዋል ሁለቱም እናቶች፡፡ በእርግጥ የጡትን ጫፍ ማውጣት እና ልጅን እንዴት ማጥባት እንደሚቻል በእርግዝናው የመጨረሻ ወቅት እናቶች የሚለማመዱበት ሁኔታ ከወለዱ በሁዋላ ለነገሩ እንግዳ እንዳይሆኑ ስለሚያደርጋቸው ልጆቹንና ለችግር የእናት ጡት ወተት ለመመገብ ያስችላል፡፡ ስለዚህ ይህንን ሁሉም ልብ ሊለው ይገባል፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ማንኛዋም እናት ከማርገዝዋ በፊት እና በእርግዝናዋ ወቅት እንዲሁም ከወሊድ በሁዋላ ከሐኪም ክትትል መለየት እንደሌለባት ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

Read 3466 times