Saturday, 24 December 2011 09:38

ዘመን አይሽሬው ቻርለስ ዲክሰን

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

እንግሊዝ በሥነ ፅሁፍና በቲያትር ጥበብ ዘርፍ ለአለም ህዝብ ብርሀን ይሆን ዘንድ አበርክቼላችኋለሁ እያለች ከምትኩራራባቸው ድንቅ የስነ ጽሁፍ ባለሙያዎቿ መካከል ዘመን አይሽሬው ቻርለስ ዲከንስ ግንባር ቀደሙ ነው፡ በእርግጥም ቻርለስ ዲከንስ ለአለማችን የስነ ጽሁፍ ጥበብ መዳበር አይተኬ ሚና ተጫውተው ካለፉት የጥበብ ሠዎች ውስጥ በሁለት እጅ ከማይነሱት ተርታ የሚመደብ ነው፡፡ በ19ኛው ክ/ዘመን ከተነሱት እጅግ ዝነኛ ደራስያን መካከል አንዱ የነበረው ቻርለስ ዲከንስ፤ በህይወት በቆየበት ዘመን ዛሬም ድረስ እንደ አዲስ የሚነበቡ በርካታ ድንቅ የስነ ጽሁፍ ስራዎቹን ትቶልን አልፏል፡፡ የዚህን ዝነኛ የጥበብ ሠው 200ኛ ዓመት የልደት በአል ለመዘከር እናት ሀገሩ እንግሊዝና በመላው አለም የሚገኙ የጥበብ አድናቂዎቹ ሽርጉዳቸዉን አጧጡፈውታል፡፡

ቻርለስ ዲከንስ ምንም እንኳ በዋናነት በድርሰት ስራዎቹ በአለም ደረጃ የከበረ ስምና ዝና ይጐናፀፍ እንጂ ያበረከታቸው የስነጽሁፍ ስራዎች ከስነ ጽሁፍም የላቀ ፋይዳ ያላቸው ናቸው፡፡ በበርካታ የጥበብ ስራዎቹ ያነሳቸው ሀሳቦች በዛሬው ዘመነኛ ባህል ውስጥም የራሳቸዉን ቦታ አላጡም፡፡ ቻርለስ ዲከንስ የኖረው በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን ህይወቱ ያለፈውም የዛሬ ሁለት መቶ አመት ገደማ ነው፡፡ ለዚህም ነው 200ኛ ዓመት የልደት በአሉ ሊከበር ዝግጅቱ የተጧጧፈው፡፡ የዚህ መጣጥፍ ዓላማ ግን የልደት በዓሉን የተመለከተ አይደለም፡፡ በእርግጥ ይልቁንስ የዚህ የጥበብ ሠው ህይወት ካለፈ ከሁለት መቶ አመት በሁዋላም እንኳ ጨርሰን ያልዘነጋነው፣ እንዲያውም ስራዎቹን ልክ እንደ አዳዲሶቹ የዘመናችን ስራዎች እያነሳን የምንደመመው ለምንድን ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ያጠነጥናል፡፡ ቻርለስ ዲከንስ በስነ ጽሁፍ ስራዎቹ ካነሳቸውና አሻራቸው በዛሬው ትውልድ ባህልና ማህበራዊ ህይወት ውስጥ ጨርሶ ካልደበዘዙ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ A white Christmas (ነጩ በረዷማው ገና እንደማለት) ነው፡፡ አንዳንድ ዘመናዊ የስነጽሁፍ ሃያስያን፤ ዲከንስን “ገናን የፈጠረው ሠውዬ” በማለት ያሞካሹታል፡፡ በእርግጥ የገና ፈጣሪ ሲሉ ቀጥተኛውን የገናን ሀይማኖታዊ በአል ማለታቸው ሳይሆን በገና በአል ዙሪያ ያሉትን ሠፊና ተወዳጅ ባህላዊ ሁነቶችን ፈጣሪ እንደሆነ ለማመልከት ነው፡፡ ስመ ጥሩው እንግሊዛዊ የስነ ጽሁፍ ሀያሲ ሌህ ሀንት ስለዚሁ ጉዳይ ሲናገር፤ “የገና በአል በቻርለስ ዲከንስ መጽሀፍ በድንቅ አቀራረብ ተገልጾ ከመቅረቡ በፊት፣ በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ማንም ነገሬና ጉዳዬ ብሎ ስሙን እንኳ የሚያነሳው ጉዳይ አልነበረም” ብሏል፡፡ የዚህን አባባል እውነትነት የሚያረጋግጥልን አንድ አብነት፣ በወቅቱ የእንግሊዝ ወግ አጥባቂ ፓርቲዎችን ያዘጋጅ የነበረው የካርልተን ክለብ ኮሚቴ፤ ገናን እንደ በአል ቀን ሳይሆን እንደማንኛውም የአዘቦት ቀን በመቁጠር ተራ የቢዝነስ ስብሠባዎችን ሲያካሂድ መኖሩ ነው፡፡ የገናን በአል በተመለከተ ነገሮች ሁሉ እንዳልነበር ያህል የተቀያየሩት ቻርለስ ዲከንስ The Christmas Carol የተሰኘውን መጽሀፍ ጽፎ ካቀረበ በሁዋላ ነው፡ የገና በአል አከባበር እንዲያንሠራራና በተለይም ደግሞ የገና ዛፉን በማስተዋወቅ ረገድ ልዑል አልበርት ባለውለታ ነው ተብሎ ቢወደስም በርካቶች ግን ቻርለስ ዲከንስ በመጽሀፍ ያቀረበው ተወዳጅ የገና ሠሞን የበአል አከባበር ሁኔታዎች ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ባለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ወደፊት በሚመጡት ትውልዶች ውስጥም አሻራው ሳይጠፋና ድምቀቱ ሳይደበዝዝ እንዲቀጥል አስችሎታል በማለት ይሟገታሉ፡፡ ቻርለስ ዲከንስ በመጽሀፉ ካነሳቸው የተለያዩ የገና ሠሞን ተወዳጅ የበአል አከባበር ሁኔታዎች ውስጥ በተለይ የነጩ ወይም የበረዷማው ገና ጉዳይ ትናንትም ሆነ ዛሬ ምናልባትም ወደፊት እንግሊዝ ውስጥ ተፈጽሞ የማያውቅ የተፈጥሮ ክስተት መሆኑ እየታወቀም ልክ በየአመቱ ሁሌ እንደሚያጋጥም የተፈጥሮ ክስተት ሆኖ በገና በአል መዝሙሮች ውስጥ በዋናነት እየተዘመረ ዛሬም ድረስ መኖሩ ከላይ ላነሳነው ሀሳብ ማረጋገጫ ይሆናል፡፡ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የተለያዩ ጽሁፍችን ካቀረቡ የተለያዩ ደራሲዎችና የስነጽሁፍ ተመራማሪዎች ውስጥ ፀሀፊና በዲከንስ ስራ ኤክስፐርት እንደሆነ የሚነገርለት ጂኬ ቸስተርተን ጉዳዩን በአንድ አረፍተ ነገር እንዲህ ሲል አጠቃሎታል:- “የቻርለስ ዲከንስ የገና በአል አከባበር ራዕዮች እኛን ግን በሚገባ ቀይሮናል፡፡”ሌላው ቻርለስ ዲከንስ በስነጽሁፍ ስራዎቹ ካነሳቸዉ በርካታ ዘመን ተሻጋሪ ጉዳዮች አንዱ ድህነት ነው፡፡ የጉዳዩ አጥኚዎች “Dickensian Poverty” ይሉታል፡ ቻርለስ ዲከንስ በህይወት በነበረበት ጊዜ አጥብቆ ይጨነቅላቸው ከነበሩትና በድርሰት ስራዎቹ ውስጥም አበክሮ ካነሳቸው ማህበረሠባዊ ጉዳዮች አንዱ የድሆች ጉዳይ ነው፡፡ እናም በቪክቶሪያን ለንደን ጊዜ ይኖሩ የነበሩትን ድሀ የዝቅተኛ መደብ አባላትን አሠቃቂ ህይወት በማይናወጥ አቋምና ግልጽነት ለአደባባይ በማብቃት የሚበልጠው ለዘር አንድ እንኳ አልተገኘም፡ ቻርለስ ዲከንስ ስለ ድህነትና ስለ ድሆች ህይወት ልበስብ የሆነው በእርግጥ እንዲሁ ያለ ነገር አልነበረም፡፡ እርሱም ሆነ ቤተሠቡ ድህነትን አሳምረው ያውቁት ስለነበር ነው፡፡ የቻርለስ ዲከንስ አባት በገንዘብ አጠቃቀም በኩል ቀሽም ነበሩ፡፡ ይህ ቅሽምናቸው ታዲያ እርሳቸውና መላ ቤተሠባቸውን በአራጣ አበዳሪዎች እስር ቤት ለስድስት ወራት እንዲማቅቁ አድርጓቸው ነበር፡፡ ያኔ ለጋ ወጣት የነበረው ቻርለስ ዲከንስ፤ ቤተሠቡን ለመርዳት በአጐቱ የጠርሙስ መሸጫ ሱቅ ውስጥ በስምንት ስድስት ሽልንግ እየተከፈለው ይሠራ ነበር፡፡ ከአመታት በሁዋላ በስነጽሁፍ ስራዎቹ ዝነኛ ሲሆን ድሆችና አቅመ ቢሶችን ለመጉዳት ባለስልጣኖች የሚጠቀሙበትን የተንዛዛ ቢሮክራሲያዊ አሠራር ለማጋለጥና ለማሳወቅ፣ ዛሬም ድረስ የተንዛዛ ቢሮክራሲ ለማመልከት የምንጠቀምበትን “red tape” የተባለ ቃል በመፍጠር በድርሰት ስራዎቹ ውስጥ ተጠቅሟል፡፡ “Dickensian” የሚለውን ከእሱ ስም ጋር የተቆራኘውን ቃልም አሠቃቂና ተቀባይነት የሌለውን ከፍተኛ የድህነት መጠንን ለመግለጽ መላው አለም ዛሬም ድረስ ይጠቀምበታል፡፡ በዘመኑ በኢንግላንድ የነበረውን ጐዶሎ ለማሳየት እንደቤንጃሚን ዲዝራኤልና ወይዘሮ ጋስኬል የመሣሠሉ ታዋቂና ስመ ጥር ደራሲዎች ባቀረቧቸው የተለያዩ የስነጽሁፍ ስራዎቻቸው የበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከዘመን ዘመን እየተሻገሩ ብርሀናቸዉን መስጠት ያላቋረጡት የቻርለስ ዲከንስ ስራዎች ብቻ ናቸው፡፡ ከቻርለስ ዲከንስ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች አንዱ ደግሞ የዘመናዊ ገፀባህሪ ኮመዲ ነው፡፡ የዲከንስን ስራዎች የመረመሩ ባለሙያዎች፤ ስራዎቹ በቀልድ የተዋዙና ሳቅ አይችል ኮስታራ የተባለውን ሠው ሳይቀር ሳይወድ በግዱ ፈገግ እንዲል የማድረግ ሀይል ያላቸው እንደሆኑ ምስክርነታቸውን ይሠጣሉ፡ ከሁሉም የሚገርመው ጉዳይ ደግሞ በስራዎቹ ያስተዋወቀው የሠዎች ንግግር ያለውን የኩምክና ሀይል ነው፡፡ በኮሜዲ ኢንዱስትሪው ያሉ ባለሙያዎች ቻርለስ ዲከንስ ትናንት ከነበሩት ኮሜዲያኖች ይልቅ አሁን ላሉቱ የበለጠ ስራ ሠርቶላቸው እንዳለፈ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ ፀሀፊና ኮሜዲያን የሆነው አርማንዶ ላኑቺ፤ ቻርለስ ዲከንስ የቪክቶሪያን ኢንግላንድ ካፈራቻቸው ኮሜዲያኖች እጅግ ምርጡ ነው፡፡ ዛሬ ያሉት የኮሜዲ ስራዎች ቻርለስ ዲከንስ በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን በፃፋቸው የኮሜዲ ስራዎች የተቃኙ ናቸው፡፡ እናም የዘመናችን የኮሜዲ ፀሀፊዎች የእርሱ እዳ አለባቸው በማለት የግል ምስክርነቱን ሠጥቷል፡፡ ስለ ሲኒማ ጥበብ ከተወራም የቻርለስ ዲከንስን ስም ሳይጠሩ ማለፍ ጨርሶ አይቻልም፡፡ ከግዌንዝ ፓልትሮው እስከ ሚስፒጊ ድረስ ያሉት የፊልም አክተሮች ከቻርለስ ዲከንስ ስራዎች የተወሠዱ የተለያዩ ሚናዎችን በተለያዩ ፊልሞች ውስጥ ተጫውተዋል፡ ዲከንስ የፊልምን ጥበብ በይዘቱ ያነሳሳውን ያህል የሲኒማ ጥበብ ኮንቬንሽንን በመፍጠሩ ረገድም ቁልፍ ሚና እንደተጫወተ ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ እንደ ሩሲያዊው የፊልም ዳይሬክተር ሠርጌይ ኤይዘንስቴይን የመሳሠሉት ባለሙያዎች ደግሞ፤ የተለያዩ የሲኒማ ጥበብ ገጽታዎች ሊፈጠሩ የቻሉት በቻርለስ ዲከንስ ተጽዕኖ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሁለት ታሪኮች በአንድነት የሚጓዙበትና Close-up የተሠኙት የፊልም አሠራር ጥበቦችን የፈጠረው ቻርለስ ዲከንስ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ የሲኒማ ጥበብን ታሪክ ለመረመረ በእርግጥም ለጥበቡ እድገት ቻርለስ ዲከንስ የተጫወተው ሚና እጅግ ከፍ ያለ እንደነበር በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ ድምጽ ያላቸው ሲኒማዎች ከመሠራታቸው በፊት በነበሩት ጊዜያት 100 የሚሆኑ የዲከንስ ሥራዎች በድምፅ አልባ ፊልሞች ተሠርተው ቀርበዋል፡፡ ከቻርለስ ዲከንስ የስነጽሁፍ ስራዎች ወደ ስክሪፕት እየተቀየሩ የሚቀርቡ ፊልሞች ዛሬም ድረስ አልቆሙም፡፡ ቻርለስ ዲከንስ በስነጽሁፍ ስራዎቹ ትቶልን ካለፋቸው ዘመን ተሻጋሪ ነገሮች አንዱ ደግሞ የገፀባህሪያት እድገት ነው፡፡ ይህ ችሎታው ከቻርለስ ዲከንስ የተለያዩ የጥበብ አበርክቶች እንደ ዋነኛው ሆኖ ይቆጠራል፡፡ The Dictionary of British Litrary characters በቻርለስ ዲከንስ ስራዎች ውስጥ የሚገኙ ዘጠኝ መቶ ሠማኒያ ዘጠኝ ገፀባህሪያትን መዝግቦ ይዟል፡፡ ከዲከንስ በፊት በነበሩ ደራሲያን የተፃፉ የልብወለድ ድርሠቶች ውስጥ ያሉ ገፀባህርያት አብዛኞቹ በወካይ ስሞች የቀረቡ ነበሩ፡፡ ቻርለስ ዲከንስ ይህንን ልማድ የገፀባህርያቱን ልዩ ባህርያትንና ሚናቸውን አቀናጅቶ እንዲይዝ በማድረግ በአንድ ደረጃ ከፍ እንዲል አድርጐ አሻሽሎታል፡፡ ይህንን የገፀባህርይ አወቃቀር ቴክኒክም ከሱ በሁዋላ ከጀምስ ጆስይና ፓይንቾን ጀምሮ እስከ ስኮት ፊትዝገራልድና ማርቲን አሚስ ድረስ ያሉ እውቅ ደራሲያን ለጥበብ ስራዎቻቸው ተገልግለውበታል፡፡ አብዛኞቻችን አሳምረን እንደምናውቀው ቻርለስ ዲከንስ ዳኛ ወይንም የህግ ጠበቃ አልነበረም፡፡ ነገር ግን በተለያዩ የስነ ጽሁፍ ስራዎቹ ውስጥ ያነሳቸዉ የህግና የህግ ነክ ጉዳዮች በሠዎች አመለካከት ላይ የፈጠሩት ተጽዕኖና ፋይዳቸው ዳኞችና የህግ ጠበቃዎች ከተጫወቱት ሚና በእጅጉ የላቀ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቻርለስ ዲከንስ ለአለማችን ካበረከታቸው በርካታ ድንቅ ስጦታዎች ውስጥ ከዋነኞቹ ተርታ ይመደባል፡፡ ቻርለስ ዲከንስ በስነጽሁፍ ስራዎቹ የሀገሩን የህግ ስርአት ጉድፍ ነቅሶ በማውጣት በግልጽ ነቅፏል፡ የማሻሻያ እርምጃ ሊወሠድባቸው ይገባል ባላቸው ጉዳዮች ላይም የግሉን ሀሳብ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡ ይህ ጥረቱም በእንግሊዝ የህግ ስርአት ላይ የራሱን ጥላ እንዲያጠላና እንግሊዝ በ1870ዎቹ ለወሠደቻቸው የህግ ስርአት ማሻሻያዎች እንደዋነኛ ግብአት ማገልገል ችሏል፡፡ ቻርለስ ዲከንስ በህግ ስርአት ጉዳዮች ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ እርሱ በነበረበት ዘመን ብቻ ተገድቦ የቀረ ሳይሆን ዛሬም ድረስ መቀጠል የቻለ ነው፡፡ ትናንት እንደነበሩት ተማሪዎች ሁሉ የአሁኑ ዘመን እንግሊዛውያን የህግ ትምህርት ተማሪዎች፣ ለቻርለስ ዲከንስ መጽሀፎች የሚሠጡት ግምትና አትኩሮት ከሌሎች የተለየ ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የዲከንስ መጽሀፎች ከህግ ትምህርት ማጣቀሻ መጽሀፎች ውስጥ ዋነኞቹ ስለሆኑ ነው፡፡ ይህን እውነታ በይበልጥ ለማብራራት ዘካሪያ ቻፊ የተባለ የህግ ምሁር በአንድ ወቅት በሀርቫርድ የህግ መጽሄት ላይ እንዲህ ብሎ ጽፎ ነበር:- “ከቴክኒካዊ ህግ ማዕቀፍ ውጭ ፒክዊክ ፔፐርስና ብሊክ ሀውስ ከተባሉት ሁለት መጽሀፎች ሌላ አንድ የህግ ተማሪ ሊያነባቸው የሚችል መጽሀፎች የሉም፡፡ የሠለጠነ ጠበቃም እንኳ ቻርለስ ዲከንስ በስራዎቹ ውስጥ ባነሳቸው አንዳንድ የህግ ነጥቦች በአድናቆት መገረሙ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ያነሳቸው የህግ ነጥቦችና ሀሳቦች ከነባራዊው የህግ አድማስ ውጭ ተሻግረው ለሁሌም ይኖራሉና”እንደ ዘካሪያ ቻፊ ሁሉ ሌሎች የህግ ባለሙያዎችና ምሁራን የዲከንስን አስተዋጽኦ በማድነቅ የየግል ምስክርነታቸውን ለመስጠት ጨርሶ ወደ ሁዋላ አላሉም፡፡ እውቁ እንግሊዛዊ የህግ ታሪክ ተመራማሪ ሰር ዊልያም ሆልድስወርዝ፤ “የእንግሊዝን የህግ ታሪክ ካነሳህ ቻርለስ ዲከንስን ማንሳት ምርጫ ሳይሆን ቸል ብለህ የማታልፈው ግዴታ ነው፡፡ ቻርለስ ዲከንስ በስራዎቹ ያነሳቸው በርካታ የህግ የዳኛና የጠበቃ ጉዳዮች አሁን ላለን የህግ ስርአት የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በእንግሊዝ የህግ ታሪክ ውስጥ ቻርለስ ዲከንስ የያዘው ቦታ ሠፊ መሆኑን ማንም ቢሆን ሊያስተባብለው የሚችለው ነገር አይደለም” በማለት የበኩላቸውን ምስክርነት ሠጥተዋል፡፡ እንግዲህ ከዚህ በላይ በመጠኑም ቢሆን ዘርዘር አድርገን ያየናቸው ጉዳዮች ዘመን አይሽሬው ቻርለስ ዲከንስ፤ በበርካታ ዘመን ተሻጋሪ የስነጽሁፍ ስራዎቹ ለአለማችን ካበረከታቸው በርካታና ፈርጀ ብዙ አስተዋጽዎቹ ውስጥ ለቅምሻ ያህል ተጨልፎ የቀረበ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ቻርለስ ዲከንስ እንዴት ያለ ድንቅ የስነ ጽሁፍ ጥበብ ባለሙያና ወደር የለሽ ሀሳብ አፍላቂ የእውቀት ባላባት እንደነበር ማስረዳት ይችላሉ፡፡ ከላይ የቀረቡት ጉዳዮች በመጠኑ ይቅረቡ እንጂ የአለም ህዝብ ቻርለስ ዲከንስን ከሞተ ከሁለት መቶ አመት በሁዋላም እንኳ ለመርሳት የሚችል ደንዳና ልብና ድርብ አንጀት ለምን እንዳጣ መመስከር ይችላሉ፡፡ ቻርለስ ዲከንስ ስጋው አፈር ከቀመሠ ድፍን ሁለት ክፍለ ዘመን ተቆጥሯል፡፡ ነገር ግን ዛሬም ድረስ አብሮን ይኖራል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በአስማት ወይም በተአምር አይደለም፡፡ እንደ ወንዝ ውሀ እየተከታተለ የሚነጉደውን ትውልድንና ዘመንን በጥንካሬአቸው እንዲሻገሩ አድርጐ በሠራቸው በርካታ የጥበብ ሥራዎቹ ብቻ ነው፡፡ ከቻርለስ ዲከንስ በፊትም ሆነ ከሁዋላ ተከታትለው የመጡና ተከታትለው ያለፉ በርካታ ታዋቂ የስነ ጽሁፍ ሰዎች ባቀረቧቸው ስራዎች ውስጥ የህብረተሠባችንን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ኑሮ የተለያዩ ጉዳዮችን በማንሳት የየራሳቸውን ተጽዕኖ ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ መፍጠር በቻሉት ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ ተጽዕኖ ሚዛን ከቻርለስ ዲከንስ ጋር ሲቆሙ ግን ስፍራቸው ለየቅል ነው፡፡ ሌሎቹ አብረውን የዘለቁት ምናልባት ትናንትና ከትናንት ወዲያን፣ በጣም ከፍ ካለም ዛሬን ብቻ ነው፡፡ ቻርለስ ዲከንስ ግን በግልጽም ይሁን በወል በፈጠረብን ፈርጀ ብዙ ተጽዕኖ አብሮን የኖረው ትናንትናን፣ ከትናንትና ወዲያንና ዛሬን ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ነገንና ከነገ ወዲያን ምናልባትም ቀኖች ሁሉ እስከሚያልቁበት እስከወዲያኛው ድረስ አብሮን ይኖራል፡፡ በዚህ ጽሁፍ መግቢያ ላይ ዝነኛው ቻርለስ ዲከንስ የስነ ጽሁፍ ጥበበኛ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ነው ያልነው በዚህ ፈርጀ ብዙ ታሪካዊ ገድሉ መነሻነት ነው፡፡ ይህን ድንቅ የጥበብ ሠው ያፈራችው የትውልድ ሀገሩ እንግሊዝ ለአለም ያበረከትኩላችሁ ድንቅ ስጦታዬ ነው እያለች በኩራት ስትሸልል በመንፈሳዊ ቅናት እየቀናንም ቢሆን “አበጀሽ ይገባሻል” የምንለውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

 

 

 

 

Read 3436 times Last modified on Saturday, 24 December 2011 16:04