Print this page
Saturday, 19 July 2014 11:52

መስፍን ሀብተማሪያምና ጥላሁን ገሠሠ

Written by  ከነቢይ መኮንን
Rate this item
(24 votes)

     ዛሬ የማስታውሰውን ያህል መስፍን ስለነገረኝ ነገር ልንገራችሁ፡፡ መስፍን ሀብተማርያም፤ ስለእሱና ስለጥላሁን ገሠሠ የፍቅር ልምድ፤ አንድ ቀን ሲያጫውተኝ፣ እንዲህ አለኝ፡፡ (መቼም አፉ እንዴት እንደሚጣፍጥ አይነገርም!)
“ድሮ ነው፡፡ አንዴ፤ አንዲት አዲስ ውስኪ ቤት የከፈተች ቆንጆ ሴትዮ ቤት ገብቼ ሳጫውታት፣ አምራኝ፣ ወዳኝ፣ ተሟሙቀን፣ ለፍቅር አንድ ሀሙስ ቀርቶናል፡፡ የማውቃቸውን አጫጭር ልብወለዶች ከነሐሚንግዌይ፣ ከነአላንፓ፣ ከነኦሄንሬ እየጨለፍኩ እያጣፈጥኩ እየነገርኳት፤ ልቧን አሳስቼዋለሁ.. ዐይኗ ይንከራተታል… ቆንጆ አቋመ - ውበቴ ላይ መላ ሰውነቷ በፍፁም ፈቃዷ ተደርቧል፡፡ አፏ ጆሮ የሆነ ያህል ተከፍቶ ያዳምጠኛል፡፡… በማህል ሲያቀብጠኝ ጥላሁን ገሠሠጋ ደወልኩ፡፡ (እንዲች ዓይነት ቆንጆ ማርኬያለሁ ብዬ ጉራዬን ልነዛበት ነው፡፡) ጥላሁን “የት አካባቢ ነው?” አለኝ፡፡ “ፓስተር አካባቢ” አልኩት፡፡ ከአንድ ከሃያ ደቂቃ በኋላ ከች አለ! ከዚያ መጣና አያት፡፡ ስገምት፣ የጦር መሳሪያ መርጧል “የህይወቴ ህይወትን” ጣዕመ - ዜማ!! አንድ ሁለት ደብል በኔው ሂሳብ ገጨና “የህይወቴ ህይወት አንቺ በመሆንሽ…” ማለት ጀመረ፡፡ ዘፈነ፡፡ መድረክ ላይ እንዲዚህ ሲዘፍን ሰምቼው አላውቅም!... አለቀ፡፡
እኔና ልጅቷ ተለያየን፡፡ ከጥላሁን ጋር የሆኑትን ሆኑ!” አለኝ መስፍን፡፡ የሚከተለው ግጥም የዚያ ስሜት ነው፡፡


======================

 


ፈጠራ እንደምችል ገብቶኛለ ያን ለታ!
ነ.መ

ስትነግረኝ --- ስትነግረኝ
ጥበብክን፣ ስትነግረኝ
“ተው ይረክሳል!” ስልህ
“ተወኝ ላውራ” ብለህ
ልታወራኝ መርጠህ
“ስማኝ ብቻ!” ብለህ …
ረከሰም ባልል፣ ምን ትተህልኝ ሄድህ
አንተን አላተረፍኩ፤ አልተረፈኝ ቃልህ፡፡
ትዝ ያለኝን ላትት፣ መኖር ጣሩ እሱ ነው
መግጠም ፍሬ ማፍራት፣ ሌላ ምን ፀጋ አለው?
በግጥም ላስቀምጠው፣ እንዲህ ነበር ያልከኝ:-
“ከድርሰት አብነት፣ ከፈጠራ ሥራ
ከሥነ-ፅሁፍ ወግ፣ ከሄኒንግዌ’ ሤራ
ከውበት አማልክት፣ የጥበባት ጎራ
ሳወራ ሳወራ፤
ጥላሁን ገሠሠ፣ በልጦ ከኔ ትምርት
በ“ህይወቴ ህይወት”፣ ቆንጆዬን ወሰዳት!”
ያልከኝን አልረሳም፡፡
ቃል ይሻል፣ ድምፅ ይሻል፣ አልገባኝም ዛሬም፡፡
መጻህፍት አብበው፣ ቢደምቁ ቢሰሙ
አጭር ልቦለዶች፣ ቢፈኩ ቢተሙ
እንዳንተም ያለ ሰው፣ በልባም ከንፈሮች
በለዛ መዐዛ፣ በወዙ ሐረጐች
ሺ ተረት ቢተርት፣ ሺ ቃላት ቢሞሽር
ያቺን ቆንጆ ሎጋ፣ ምን ምኗን ቢወድር
ያችን ውብ አለንጋ፣ ምን ገላዋን ቢያሾር
አፏን አከላቷን፣ ከፍታ ብታዳምጥ
ብታቅፍ፣ ብታግል፣ ሁሏን ብታተኩስ
ራሷም ብትነድ፣ ከላይ እታች ድረስ
… ዘፋኙ ሲመጣ፣ እንዲህ ሁሉም ሲሻር
ለካ ፍቅር የለም፣ ድምፅ ሳይጨመር
ያልከኝን አልረሳም…
ብዕሬን ሰበሰብኩ፣ ጥላሁን ሲመጣ
ለካ-ሥነ-ፅሁፍ፣ ቅላፄ ሳይሰንቅ፣ ዳገትም አይወጣ!
ድምፅ ሲስረቀረቅ፣ ቆንጆ አቅሏን ስታጣ
ተፈጥሮን አየሁት፣ ትምህርትን ሲቀጣ!
ያልከኝን አልረሳም…
ወዳጅህ ነው ጥሌ
ወዳጁ ነህ አንተም
ግን በዜማ ዝናብ፣ ያኔ መሸነፍክን
በመለኮት ቃና፣ ቆንጆ መነጠክን
አምነህ ነግረኸኛል፣ በኪነ-ጥበብ ሥን
ሰማይና መሬት፣ ያን ያህል መራቁን!!
ባማለልካት ቆንጆ፣ ባሞቅኸው ገበታ
ጥላሁን ሲከሰት፣ ባስረከብከው ቦታ
አንት ያበሰልከውን
የላቀህ መብላቱን
በነገርከኝ አፍታ፤
መስፍኔ ልንገርህ …
ፈጠራ እንደምትችል፣ ገብቶኛል ያን ለታ!
ፍፁም ደግነት ነው፣ በሚችል መበለጥ
ዘመንን ይልቃል፣ ዕውነትን የሚመርጥ!
ሐምሌ 10/2006 ዓ.ም
(ለመስፍን ሀብተማርያም እና ለጥላሁን ገሠሠ)

Read 7712 times