Saturday, 19 July 2014 12:51

“ውረድ ወይም ፍረድ!”

Written by  አላዛር ኬ.
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ኑሮአቸው የተጠቁና የተገፉ ሲመስላቸው ከሌላ ከማንኛውም አካል ይልቅ ስሞታቸውን የሚያቀርቡት ለአምላካቸው ነው። ጥቃታቸውንና መገፋታቸውን አይቶ መልስ እንዲሰጣቸው አምላካቸውን “ውረድ ወይም ፍረድ!” እያሉ ይማፀኑታል፡፡ አንዳንዴም ያዙታል፡፡
ልክ እንደ ኢትዮጵያዊያኑ ሁሉ በፍርደ ገምድል ኢ-ፍትሀዊ ውሳኔ እድሜ ልኩን በወህኒ እንዲማቅቅ የተፈረደበት የሰሜን ካሮላይና ግዛት ነዋሪው አሜሪካዊው ዳሪል አንቶኒ ሆዋርድም ያጋጠመውን ከፍተኛ የፍትህ መጓደል አይቶ መፍትሄ እንዲሰጠው “ውረድ ወይም ፍረድ!” ብሎ ኤሎሄ ያለው ለአምላኩ ብቻ ነው፡፡
በ1991 ዓ.ም በዱርሀም የመኖሪያ አካባቢ ነዋሪ በነበረችው ዶሪስ ዋሽንግተንና የ13 ዓመት ሴት ልጇ ኒሾንዳ ግድያ እጁ አለበት በሚል ያለ በቂ ማስረጃ በ1995 ዓ.ም የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ዳሪል ሆዋርድ ያለፉትን 19 ዓመታት ለአንድም ቀን ሳይሰለችና ፈጽሞ ተስፋ ሳይቆርጥ አምላኩን “ውረድ ወይም ፍረድ!” እያለ በመማፀን አሳልፏል፡፡
“ውረድ ወይም ፍረድ!” ተብሎ ተማጽኖ የቀ    ረበለት አምላክ አልወረደም፡፡ ግን ፍርዱን ፈረደለት። የመጀመሪያውን የፍርድ ውሳኔና የቀረበለትን አዲስ ማስረጃ የመረመረው የሰሜን ካሮላይና ግዛት የይግባኝ ፍርድ ቤት፤ ዳሪል ሆዋርድ የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ጨርሶ ባልፈፀመው ወንጀልና ምንም አይነት በቂ አሳማኝ ማስረጃ ሳይቀርብበት ነው በማለት ባለፈው ማክሰኞ በነፃ አሰናብቶታል፡፡
የግዛቲቱ የይግባኝ ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ የሆኑት ኦርላንዶ ኸድሰን፤ የዳሪል ሆዋርድን የመጀመሪያ ፍርድ አስመልክተው ሲናገሩ፤ “አቃቤ ህጎቹ ማስረጃዎቹን በሙሉ ደብቀዋቸዋል፡፡ ፖሊሱም የዳኞች ጉባኤውን አሳስቷል፤ ይህ በህግ ሙያ ባሳለፍኩት 34 ዓመታት ውስጥ አጋጥሞኝ የማያውቅ እጅግ አሳፋሪና ዘግናኝ የፍትህ ስህተት ነው፡፡” ብለዋል፡፡
የዳሪል ሆዋርድ ጉዳይ ዳግመኛ እንዲታይ ለይግባኝ ፍርድ ቤት ያመለከቱትና እውነተኛውን ወንጀለኛ የሚያሳይ የዲኤንኤና ሌሎች ማስረጃዎችን በማሰባሰብ በነፃ ጥብቅና ቆመው የተሟገቱለት “Innocence Project” የተባለ ምግባር ሠናይ የህግ ባለሙያዎች ድርጅት ጠበቆች ናቸው፡፡
የይግባኝ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለዳሪል ሆዋርድ በስልክ ያበሰረችው ጠበቃው ሲማ ሲያይፊ፤ “ለመሆኑ በነፃ መለቀቁን መጀመሪያ ስትነግሪው ዳሪል ሆዋርድ ምን አለሽ?” ተብላ ሰትጠየቅ የሰጠችው መልስ “ወህኒ ቤት ሄጄ በአካል በማግኘት ዜናውን ልነግረው አስቤ ነበር፡፡ ነገር ግን ጨርሶ አላስችል አለኝና ስልክ ደውየ ነገርኩት፡፡ ልክ ነገሩ እውነት መሆኑን ሳረጋግጥለት በከፍተኛ የደስታ ሲቃ “አምላክ ፈረደ! የእውነት አምላክ ፈረደ!” አለኝ፡፡ ዳሪል ሆዋርድ ይህንን ፍርድ ለመስማት ለ19 ዓመታት በትእግስት ጠብቋል፡፡ እሱ ፈጽሞ ተስፋ የማይቆርጥ ሰው ነው፡፡” የሚል ነው፡፡
ዳሪል ሆዋርድ በጥቁርነታቸው የተነሳ ከፍተኛ የፍትህ መጓደል ከተፈፀመባቸውና የዘረኝነት ሰለባ ከሆኑ በርካታ አሜሪካውያን አንዱ ነው፡፡ በ1995 ዓ.ም ያለ ትክክለኛና በቂ ማስረጃ የእድሜ ልክ እስራት የፈረዱበት ዳኛ ማይክል ኒፎንግ በጥቁር፣ ጠል አቋማቸው ባለ ሪከርድ ናቸው፡፡ ተከሳሹ ጥቁር ብቻ ይሁን እንጂ ስለሚቀርብበት ማስረጃ ግድ የላቸውም፡፡ ፍርዳቸውም ፍርደ ገምድል ነው፡፡
የሰሜን ካሮላይና ግዛት የፍትህ ቢሮ፤ እኒህን ዘረኛ ፍርደ ገምድል ዳኛ እንደነገሩ እያስታመመ እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ ታግሷቸው ነበር፡፡ በ2007 ዓ.ም በአስገድዶ መድፈር ወንጀል በሀሰት ተከሰው በቀረቡት የዱክ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር ተማሪዎች ላይ ያለ በቂና ትክለለኛ ማስረጃ ከባድ እስር ቅጣት ካስተላለፉ በኋላ ግን በዝምታ ሊታለፉ አልቻሉም። የዳኝነትና የጥብቅና ፈቃዳቸውን በመንጠቅ በሰሜን ካሮላይና ግዛት የፍትህ አደባባይ ዳግመኛ ዝር እንዳይሉ አባሯቸዋል፡፡

Read 1550 times